የሶሪያ የኬሚካልን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ ሩሲያ አስጠነቀቀች

A picture taken on April 8 2018 shows Syrian Army soldiers gathering in an area on the eastern outskirts of Douma Image copyright Getty Images

ሩሲያ ሰሞኑን በሶሪያ ተከስቶ የነበረውን የኬሚካል ጥቃት አሜሪካ በወታደራዊ አፀፋ ምላሽ እንዳትሰጥ አስጠነቀቀች።

"አሁን ከያዛችሁት ዕቅድ እንድትቆጠቡ አሁንም ደጋግሜ እመክራለሁ፤" ያሉት የሞስኮ የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልዕክተኛ ቫሲሊ ኔቤንዚያ ናቸው።

የዋሽንግተንን ባለስልጣናትም ፣"ለማንኛውም ህገወጥ ወታደራዊ ምላሽ ሃላፊነት ይከፍላሉ፤" ብለዋል።

ነገር ግን ምዕራባውያን መሪዎች በሶሪያዋ ግዛት ዱማ ላይ የተፈጠረውን የኬሚካል ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት አብረው እየሰሩ ነው።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ምዕራባውያን አገሮች በሚሰጧቸው ምላሽ የሶሪያ መንግሥትና የኬሚካል ማምረቻ` ቦታዎችን ኢላማ ሊያደርግ እንደሚችል ገልፀዋል።

ከሞስኮ የተሰጠው ይህ ማስጠንቀቂያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ድርጅት በሶሪያ ላይ በደረሰው ጥቃት ላይ አዲስ ምርመራን ለመክፈት ያስያዘው ዕቅድ በተከፋፋለ ድምፅ ሳያልፍ ከቀረ በኋላ ነው።

ሩሲያ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ አሜሪካ ያቀረበችውን ሰነድ ውድቅ ያደረገች ሲሆን ፣ቻይና ድምፅ ከመስጠት ተቆጥባለች። ሞስኮ አቅርባው የነበረውም ሀሳብ ብዙም ድምፅ ሳያገኝ ውድቅ ተደርጓል።

አሜሪካ ነፃና ገለልተኛ በሆኑ አካላት የሶሪያው ፕሬዚዳንት ባሽር አል-አሳድ በምስራቃዊዋ ጉታ ቀጠና በምትገኘው ዱማ ላይ የኬሚካል ጥቃት ማድረሳቸውን በመወንጀል ምርመራ እንዲደረግ የሚጠይቅ ሰነድ እንዳቀረበች ተዘግቧል።

በሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ የሚደረግለት የሶሪያ መንግሥት ''ምንም አይነት የኬሚካል ጥቃት አላደረስኩም፤'' በማለት ይክዳል።

የኬሚካል መሳሪያዎችን ከሚቆጣጠረው ድርጅትም አንድ ቡድን በቅርቡ እንደሚላክና በዱማ ላይ ክልከላ የተደረገባቸው መሳሪያዎች መጠቀማቸውን ምርመራ ያደርጋሉ። ይህ ድርጅት ግን ለጥቃቱ ''ማን ተጠያቂ ነው?'' የሚለውን አይወስንም።

በተባበሩት መንግሥታት የተደረገው የአሁኑ ስብሰባ በሩሲያና በአሜሪካ ተወካዮች መካከል የቃላት ጦርነትን ያስተናገደ ነው።

ኔቤንዚያ ጨምረውም፣" አሜሪካ እነዚህን ሰነዶች ያቀረበችው ወታደራዊ ጥቃት ለማድረስ እንዲመቻት ነው፤'' ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች