ዓረና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር ይፈልጋል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ Image copyright ZACHARIAS ABUBEKER

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ከሲቪክ ማሕበራት ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ውይይቱ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ሙሉ ዝርዝር ይፋ አልሆነም።

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ዛሬ ምሽት ተገናኝተው ይወያያሉ ተብለው ከሚጠበቁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አንደኛው የሆኑት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ- መንበር አቶ በቀለ ገርባ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተጨባጭ እርምጃዎችን በተመለከተ መነጋጋር እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ፓርቲያቸውን በመወከል ከእርሳቸው በተጨማሪ ዶክተር መራራ ጉዲናም ጥሪ እንደቀረበላቸው በስልክ መስማታቸውን የሚናገሩት አቶ በቀለ ከማህበራዊ ግንኙነት የዘለለ ፋይዳ ያለው ውይይትን መኖር አለበት ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የሰዎች ግድያ መቆም አለበት። እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ነው እንጅ ስብሰባዎች እና ከሰዎች ጋር የሚጠፋ ጊዜ ብዙም ዋጋ አለው ብለን አናምንም፤"በማለት አቶ በቀለ ተናግረዋል። ኃሳባቸውን የማስረዳት ዕድሉን የሚያገኙ ከሆነ እነዚህን ጉዳዮች እንደሚያነሱም አቶ በቀለ ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ከጀመሩ አንስቶ ያላቸው እንቅስቃሴ በተመለከተም ላነሳንላቸው ጥያቄ ፣"በየቦታው እየዞሩ ማረጋጋት በሚመስል መልኩ ሳይሆን በተጨባጭ ህዝቡን ሊያረጋጉ የሚችሉ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፤" ይላሉ።

ጨምረውም ፣"በስብሰባ የሚጠፋ ጊዜ የስራ ጊዜ ነው ብለን አንወስድም፤" ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደልብ ተንቀሳቅሶ ህዝብን መሰብሰብ አዳጋች እንዳደረገባቸውም አልሸሸጉም። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋም በበኩላቸው ፣ግብዣው እንደደረሳቸው ሆኖም የመርኃ ግብሩን ዝርዝር ይዘት እንደማያውቁ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበራት ቅንጅት ዳይሬክትር የሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገብረመድህንም ጥሪውን እንደደረሳቸው ገልፀው፣ ሆኖም የስብሰባው ይዘት ምን እንደሆነ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ለቢቢሲ ያስረዳሉ።

በትግራይ ክልል ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አረና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መቀሌን በሚጎበኙበት ወቅት የፓርቲያቸውን ተወካዮች ሊያነጋግሯቸው እንደሚሹ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማነጋገሩ ዕድል እንዲመቻችላቸው ለትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ድብረፂዮን ደብዳቤ ማስገባታቸውንም የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደብዳቤዉን ለትግራይ ክልል መስተዳደር ቢሮ ዛሬ ማስገባታቸውን የተናገሩት አቶ አምዶም ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተስፋ ያደርጋሉ። የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በተለይም በትግራይ አንድም የፖለቲካ እስረኛ አለመፈታቱ እንደሚያሳስባቸውና ይህንንም ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ ማሰባቸውን አውስተዋል።

የክልል ፓርቲዎች በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእራት ግብዣ ላይ አለመጋበዛቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ አምዶም ሆኖም ግን ጥያቄዎቻቸውን በመድረክ በኩል ባላቸው ውክልና እንደሚያነሱ አብራርተዋል።

የመድረክና የአረና የስራ አስፈፃሚ አባል መምህር ጎይቶም ፀጋይ በበኩላቸው በዛሬው የእራት ግብዣ ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረው እርሳቸውን ጨምሮ አምስት የመድረክ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብዣ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

ሆኖም የውይይቱን መልክና ይዘት በዝርዝር እንደማያውቁ ተናግረዋል።

"እንደ አጀንዳ ይዘነው የምንገባው የተለየ ጉዳይ የለም።...በእራት ብቻ እንዲሸኙን ግን አንፈልግም..." ሲሉም አክለው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሠረት ውይይት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ እንዲከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል።