የአውሮፓ ህብረት ለሞያሌ ተፈናቃዮች እርዳታ እንደለገሰ አስታወቀ

የሞያሌ ተፈናቃዮች Image copyright BRIAN ONGORO

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ ከሞያሌ ቀያቸውን ለቅቀው በኬንያ ግዛት ለተጠለሉ ኢትዮጵያዊያን የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ መጠኑ አንድ መቶ ሺ ዩሮ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገ፣ ድጋፉም የኬንያ የቀይ መስቀል ማህበር ለተፈናቃዮቹ የመሰረታዊ ጤና ግልጋሎት እና የነፍስ አድን ቁሶችን ለማዳረስ ለሚያደርገው ጥረት እንደሚውል በአውሮፓ ህብረት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና የሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ ፒተር በርገስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአሁኑ ድጋፍ በስፍራው ያለውን ፍላጎት 'በከፊል ይሸፍናል፤' በሚል የተሰጠ እንደሆነ ያስገነዘቡት ሃላፊው፣ "ከዛሬ ጀምሮ በሞያሌ ተገኝቶ ሁኔታውን የሚያጠና ቡድን ይኖረናል። የቡድኑ አባላት የሚደርሱበትን መሰረት አድርገን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መመደብ ይኖርብን እንደሆነ እንመለከታለን፤'' ብለዋል።

ሰብአዊ ድጋፉ በሦስት ማዕከሎች የተጠለሉ አስር ሺህ ሰዎችን በቀጥታ እንደሚጠቅምም ህብረቱ አክሏል።

ከአንድ ወር በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት ከአስር በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ለነፍሳቸው የሰጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሸሻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱ የተፈፀመው በስህተት መሆኑን በማስረዳት፣ የሸሹ ነዋሪዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ጥሪ ቢያቀርብም "አሁንም ለህይወታችን እንሰጋለን" የሚሉ ነዋሪዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ቀናትን በመግፋት ላይ ናቸው።

በመጠለያ ማዕከላቱ ተጨማሪ ድጋፍ አሁንም እንደሚያስፈልግ የረድኤት ድርጅቶች እየተናገሩ ነው።

በኬንያ የወርልድ ቪዥን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዳንካን ኦዳዎ፣ "እኒህ በመጠለያዎቹ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚመግባቸው የለም፤ ውሃ ያስፈልጋቸዋል፤ የህክምና ትኩረትም ይሻሉ፤ ህፃናት፣ ሴቶች እና እናቶች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፤ አሁንም የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት አለ፣'' ብለዋል።

ዳንካን አክለውም ተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ መጠለያዎች በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ስለሚፈርሱ ጥገኝነት መጠየቅ የሚፈልጉ ወደ ስደተኛ ጣቢያዎች የሚያስገባቸውን ሂደት እንዲጀምሩ፣ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ካሉም ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ በአካባቢው ባለስልጣናት እንደተነገራቸው መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች