ቶተንሃም ከሲቲ...ሌላ ፈተና ለማንቸስተር ሲቲ?

ሲቲ ከቶትንሃም Image copyright BBC Sport

የማንቸስተር ሲቲ ሳምንት ወደ ዌምብሌይ ተጉዞ በሚያደርገው ጉዞ ድል ቀንቶት ያምር ይሆን? ወይስ ሌላ ሽንፈት ይገጥመው ይሆን? የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ማርክ ላውረንሰን ለዚህና ሌሎችም የፕሪሚዬር ሊጉ ጨዋታዎች የሚሆን ግምት አዘጋጅቷል።

ቅዳሜ

ሳውዝሃምፕተን ከቼልሲ

Image copyright BBC Sport

ባለሰፈው ሳምንት ከዌስት ሃም ጋር የነበረውን ፍልሚያ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ቼልሲ ነጥብ መጣሉ ቁንጮ ላይ ካሉት አራቱ ቡደኖች ተርታ እንዳራቀው እሙን ነው። እኔ በዚህ ዓመት ቼልሲ ከቁንጮ አራት በታች ሆኖ ያጠናቅቃል ብዬ ነው የማስበው።

ለሳውዝሃምፕተንም ነገሮች ቀላል አይደሉም፤ እንደውም የባሱ እንጂ። በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን የተሸነፉት ቅዱሳኑ በዚህ ጨዋታ ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ ከወራጅ ቀጣና የመውጣት ተስፋቸው የመነመነ ነው የሚሆነው።

ግምት፡ 1 - 1

በርንሊ ከሌይስተር

Image copyright BBC Sport

በርንሊ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በድል ማጠናቀቅ ችሏል። ይህንን ጨዋታ መርታት ከቻለ ደግሞ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተደላድሎ መቀመጥ ይችላል። ኧረ እንዲያውም በአውሮፓ ሊግ ሊሳተፍ የሚችልበትን እድል ሊያገኝ ይችላል።

ምንም እንኳ ሌይስተርም መጥፎ የሚባል የውድድር ዘመን ቢያሳልፍም ባለፈው ሳምንት በገዛ ሜዳው በኒውካስትል መረታቱ አስደንቆኛል።

ግምት፡ 2 - 1

ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን

Image copyright BBC Sport

ክሪስታል ፓላስ ይህን ጨዋታ ይረታል ብዬ እወራረዳለሁ። ብራይተን ባለፈው ሳምንትም ከሃደርስፊልድ ጋር በነበራቸው ፍልሚያ ነጥብ ጥለዋል።

ፓላሶች ደግሞ የፕሪሚዬር ሊግ ሕይወታቸውን ለማራዘም ትግል ላይ ናቸው። ለደጋፊዎቻቸው አስደሳች ከሰዓት ይሆናል ባይም ነኝ።

ግምት፡ 2 - 1

ሃደርስፊል ከዋትፎርድ

Image copyright BBC Sport

ዋትፎርድ አሁንም በአደጋ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ። ካለፉት አራት ጨዋታዎቻቸው አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።

ሃደርስፊልድም ቢሆን ደካማ እንቅስቃሴ ነው እያሳዩን ያሉት። ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ከሃደርስ ይልቅ ለዋትፎርድ ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ።

ግምት፡ 1 - 1

ስዋንሲ ከኤቨርተን

Image copyright BBC Sport

ባለፈው ሳምንት ከታሪካዊ ተቀናቃኛቸው ሊቨርፑል ጋር የገጠሙት ኤቨርተኖች የሚያበሳጭ አቋም ነበር ያሳዩት። ጨዋታውን ማሸነፍ እንደነበረባቸው ይሰማኛል። በዚህ ጨዋታም ከአቻ የዘለለ ነጥብ ያመጣሉ ብዬ አላስብም።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የረቱት ስዋንሲዎችም ከወራጅ ቀጣናው ለመሸሽ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።

ግምት፡ 1 - 1

ሊቨርፑል ከበርንመዝ

Image copyright BBC Sport

አሁን ሊቨርፑል ያሉበት አቋም እጅግ ግሩም ነው። ሲቲን ከቻምፒዮንስ ሊጉ ማሽቀንጠር ችለዋል። ምንም እንኳ እኔ ዕድል የታከለበት ነው ብልም።

በርንመዞች ምን ያህል በመልሶ ማጥቃት ኃይለኛ ቢሆኑ ሊቨርፑል ሜዳ ላይ ይሳካላቸዋል ብዬ አላምንም።

ግምት፡ 2 - 0

ቶተንሃም ከሲቲ

Image copyright BBC Sport

ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሲቲ ቶተንሃምን 4 - 1 መረምረሙ አይዘነጋም። ነገር ግን አሁን ሁኔታዎች ተቀይረዋል።

እኔ አስከፊ የሚባል ሳምንት ያሳለፉት ሲቲዎች ከዚህ ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ያገኛሉ ባይ ነኝ። በዚህ ጨዋታም ዋንጫውን ማንሳታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ አይመስለኝም። ጊዜ ይፍጅ እንጂ ዋንጫውን ማንሳታቸው እንደሁ አይቀሬ ነው።

ግምት፡ 1 - 1

እሁድ

ኒውካስትል ከአርሴናል

Image copyright BBC Sport

አርሴናሎች በሁሉም ውድድሮች ያከናወኗቸውን ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል። ግን ይህ የአርሴናል ባህርይ ነው፤ የውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ በርትተው ይታያሉ።

ኒውካስትልም ቢሆን አሁን ላይ ያላቸው አቋም እጅግ መልካም የሚባል ነው። የአርሴናል ቅድሚያ ትኩረት የአውሮፓ ሊግ መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም።

ግምት፡ 1 - 1

ዩናይትድ ከዌስትብሮም

Image copyright BBC Sport

ይህን ጨዋታ ዩናይትድ እንደሚያሸንፈው ምንም ጥርጥር የለኝም። ባይሆን ባለፈው ከሲቲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ከእረፍት በፊት ወይስ በኋላ ያለውን ቡድን ነው የምናየው የሚለው ነው የኔ ጥያቄ።

ነገሮች ለዌስትብሮም እየከበዱ መምጣታቸው ግን በግልፅ እየታየ ነው።

ግምት፡ 3 - 0

ሰኞ

ዌስት ሃም ከስቶክ

Image copyright BBC Sport

በአሁኑ ሰዓት ዕድል ከዌስት ሃም የወገነች ትመስላለች። ከባለሜዳው ቼልሲ ጋር በስታንፎርድ ብሪጅ አቻ መለያየታቸው ደግሞ የበለጠ እንዲነሳሱ ያደርጋቸዋል ባይ ነኝ።

መዶሻዎቹ ይህን ጨዋታ የሚረቱ ከሆነ ከስጋት ነፃ የሚሆኑትን ያክል ለስቶክ አስጊ ነው።

ግምት፡ 2 - 1

ተያያዥ ርዕሶች