የሲሊከን ቫሊ ልጆች ትልቁን ኢትዮጵያዊ የመረጃ ቋት የመፍጠር ህልምን ሰንቀዋል

ሰዎች የሰዋሰውን የፌስቡክ ገጽ የሚያመላክት ካርቶን ይዘው ለሰዋሰው ማስተዋወቂያ ዝግጅት አሜሪካ ባለችው በሲያትል ከተማ Image copyright SEWASEW
አጭር የምስል መግለጫ አሜሪካ ባለችው ሲያትል ከተማ የሰዋሰው ማስተዋወቂያ ዝግጅት

ዓለም የመረጃ ሱናሚ አጥለቅልቋታል። በአገር ቋንቋ የተደራጁ መረጃዎች ግን የሚያመረቁ አይደሉም፤ በይዘትም በጥራትም።

ይህንን ክፍተት እንሞላለን ያሉ አምስት ኢትዯጵያዊያን ወጣቶች ከሲሊከን ቫሊ ብቅ ብለዋል።

"የዶሮ ወጥ እንዴት ይሠራል?" ከሚል የማዕድቤት ጥያቄ እስከ አቡነ ጴጥሮስ ግለ ታሪክ፤ "ክራቫት እንዴት ይታሠራል?" ከሚል የማጌጥ ጥያቄ እስከ ዮዲት ጉዲት ሕይወትና የፖለቲካ እርምጃዎቿ ሁሉም ነገር በአገሬው ቋንቋ በመልክ በመልክ እያደራጁ እንደሆነም ያወሳሉ።

ሰዋሰው (ኢትዯጵያዊው ዊኪፒዲያ)?

እየፈጠርን ያለውን «ማናኛውንም አፍሪካዊ ነክ መረጃ የሚገኝበትን ቋት ነው፣'' ይላል እሸቱ አበበ ።

እሸቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማሰተርስ ዲግሪ ያለው ሲሆን የ15 ዓመት የሥራ ልምድን አካብቷል። ከአምስቱ የሰዋሰው መሥራቾች መካከል ''የሥራ ድርሻዬን ከሃገር ቤት ሆኜ እወጣለሁ'' የሚለው እሸቱ የሥራ አጋሮቹ በአሜሪካን አገር ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው እንደሚሠሩም ይናገራል።

ባሕር ማዶ የሚገኙት የተቀሩት አራቱ የሰዋሰው መሥራቾች በሲሊከን ቫሊ ውስጥ ስመ ጥር የሆኑ እንደ ኢንቴል፣ ጉግል፣ ኤችፒ፣ ኦራክልና ማይክሮሶፍት ያሉ ድረጅቶች ውስጥ የሥራ ልምድን ያካበቱ ናቸው።

ሲሊከን ቫሊ በቴክኖሎጂ ከፍተኛ እድገቶችንና ለውጦችን ወደ ቀሪው ዓለም የምታመነጭ በመሆኗ ይበልጥ ትታወቃለች።

''ዊኪፒድያ የዓለምን በሙሉ ዕውቀት መዝግቤ እይዛለሁ ብሎ የተነሳ ነው'' የሚለው እሸቱ ሆኖም ግን እውነታው ከዚህ እንደሚለው ያስረዳል።

''ለምሳሌ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፉ ጽሑፎች በአፍሪካ ቋንቋና ስለ አፍሪካ በአጠቃላይ ከተጻፉት ጽሑፎች ጋር ሲነፃፀር በሁለት እጥፍ ይበልጣል። ''ይህ የሚያሳየው ስለ አንዲት ሃገር ያለው የተመዘገበ መረጃ ስለ አንድ አህጉር ካለው መረጃ በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ነው።" ሲል ንጽጽሩን ያብራራል።

እሸቱ የአፍሪካን ያልተመጣጠነ ውክልና አጽእኖት ሰጥቶ ሲያብራራም "አፍሪካ ገና 'ዲጂታይዝ' አልተደረገችም'' ሲል ሐሳቡን ያሳርጋል።

እነ እሸቱ ታዲያ አዲስ የፈጠሩት "ሰዋሰው" ይህን ክፍተት ያጠባል ብለው ያምናሉ።

Image copyright SEWASEW
አጭር የምስል መግለጫ (ከግራ ወደ ቀኝ) ብርሃኔ ተገኘ፣ እሸቱ አበበ፣ ርብቃ ደመቀ፣ መሠረት እሸቴ እና ተስፋዬ ሙለታ

የሰዋሰው እድልና ፈተና

የአምስቱ የሰዋሰው መሥራቾች ትውውቅ ከድኅረ ምረቃ የጀመረ ቢሆንም ቀጥለው ግን ኢትዮ-ቴሌኮም በአንድ ላይ መሥራታቸው ይበልጥ አቀራርቧቸዋል።

''ሰዋሰውን ድረ-ገጽ ለማድረግ ምንም አልተቸገርንም'' የሚለው እሸቱ ''ምክንያቱም ሁላችንም የቴክኒክ ሰዎች ነንና እንዴት እንደሚሠራ እናውቅ ነበር'' ይላል።

የኋላ ኋላ ግን እንቅፋቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው አልቀረም።

''ሰዋሰው ገንዘብ ማመንጨት ባለመጀመሩ ያሰብነውን ያህል መሄድ አልቻልንም'' ነበር ይላል እሸቱ። ከዚያም በላይ ''ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ፤ በተደጋጋሚ በይነ-መረብ ስለሚዘጋ ባሰብነው መጠን ሰዎች ዘንድ በመድረስ ረገድ ችግር ፈጥሮብናል።''

የሰዋሰው መሥራቾች በአሁኑ ሰዓት በአገልግሎት ላይ ያሉ የበይነመረብ መረጃ ቋቶች የአፍሪካን ቋንቋዎች መሠረት ያልተረዱ በመሆናቸውና የቴከኖሎጂ ቋንቋ ለመማር በሚያመች መሣሪያ ባለማቅረባቸው ተደራሽነታቸው ተገድቧል ባይ ናቸው።

"ከዕለት ተዕለት የመረጃ ፍጆታችን አንስቶ እስከ ትላልቅ አገራዊ ታሪኮቻችን ድረስ ወግና ሥርአት ባለው መልኩ በበይነመረብ ተመዝግበው አለመኖር፣ካሉም ደግሞ በቀላሉ ተደራሽ አለመሆን ትልቁ የታዘብነው ችግር ነው" ይላሉ መሥራቾቹ በዩቲዩብ ላይ ባስተላለፉት የትውውቅ ቪዲዮ።

ይህን ችግር መፍታት ደገሞ አሁን ላለውና ለሚመጣው ትውልድ ትልቅ አበርክቶት ነው ብለው ያስባሉ።

ለመሆኑ እጅግ መጠኑ የበዛ፥ ሆኖም ግን ጥራቱን የጠበቀ መረጃን በአምስት ሰዎች አቅም ማደራጀት ይቻላል? እንዴትስ በሁሉም የሞያ ዘርፍ የሚገኝን መረጃ ወደ በይነ መረብ ቋት ማስገባትና መተንተን ይታሰባል?

እሸቱ አበበ ለዚህ መፍትሄ አዘጋጅተናል ይላል።

ድረ ገፁ ላይ "ቻሌንጅ" የሚል ቁልፍ ተፈጥሯል። ይህም ደርዝ ባለው መልኩ ያልተደራጁ መረጃዎች ለሞያው የሚቀርቡና ዕውቀቱ አላቸው የሚባሉ ሰዎች ራሳቸው የሚያደራጅበት ዘዴ ነው።

እንዲያም ሆኖ የመረጃ መፋለስ አልፎ አልፎ መፈጠሩ ስለማይቀር የተዛቡ መረጃዎች ሲታዩ ተጠቃሚዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያስችል ቁልፍም መዘጋጀቱን ወጣት መሠረት እሸቴ ይገልፃል።

"የመጣነው ሀብታም ባህል፥ ብዙ ቋንቋና ቀደምት ታሪክ ካለው ማኅበረሰብ ነው። ያለመታደል ሆኖ ይህን የምንጋራበት ዘመነኛ መንገድ የለንም። የሰዋሰው ሕልም ይህን መድረክ መፍጠር ነው።"

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ዓለም የመረጃ ሱናሚ አጥለቅልቋታል። በአገር ቋንቋ የተደራጁ መረጃዎች ግን የሚያመረቁ አይደሉም፤ በይዘትም በጥራትም።

ተያያዥ ርዕሶች