የጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ ስብጥር

የኢትዮጵያ ፓርላማ Image copyright Getty Images

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቧቸው የካቢኔ አባላት እጩዎች በሙሉ ድምጽ ጽድቆላቸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አስር አዳዲስ ሚንስትሮችን ወደፊት ያመጡ ሲሆን ስድስት ሚንስትሮችን ደግሞ ከነበሩበት ሥፍራ ወደሌላ ሚንስትር መስሪያ ቤት እንዲዘዋወሩ አድረገዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጧቸው ሹመቶች የፆታ እና የሃይማኖት ተዋጽዖን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው የሚሉ ተንታኞች እንዳሉ ሆኖ፤ የፆታ ተዋጽዖ ሚዛናዊ አይደለም እንዲሁም ለካቢኔ ሹመት ሃይማኖት እና ፆታ መስፈርት መሆን የለበትም የሚሉም አሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ለምክር ቤቱ የካቢኔው ሹመት ከዘገየበት ምክንያት አንዱ ''የሴቶችን ተሳትፎ በሁሉም የአመራር እርከን ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ነው'' ብለዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ አሁንም በእርሳቸው ካቢኔ ውስጥ የፆታ ተዋጽዖ እና ለሴቶች የተሰጠው የስልጣን እርከን የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ የሚሞግቱ አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዷ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ናቸው።

ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግሥት ቃል አቀባይና የሥርዓተ-ፆታ የመብት ተሟጋች ናቸው።

ወ/ሮ ሰሎሜ ''እውነት ለመናገር የተሻለ ነገር ጠብቄ ነበር ባለመሆኑም በጣም አዝኛለሁ። ላለፉት 27 ዓመታት በሙሉ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ጥያቄ ሲነሳ የሚሰጥ ተመሳሳይ መልስ አለ፤ ይህም 'ብቁ የሆኑ ሴቶችን ማግኘት አልቻልንም ነው።' ዛሬም ላለፉት 27 ዓመታት ሲሰጥ የነበረውን መልስ ነው የሰማሁት። በሃገሩ ሴት የለም ነው የሚሉት?'' ሲሉ ይጠይቃሉ።

ሌላው ወ/ሮ ሰሎሜ ለሹመቶቹ ግልጽ መለኪያ መኖር እንዳለበት ይከራከራሉ። ''ወንዶቹ የተሾሙት ምን መለኪያ ተቀምጦላቸው ነው? ሴቶቹ ወንዶቹ በተለኩበት መለኪያ አንሰው ነው ወይ?'' ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ለሴቶች የሚሰጠው የስልጣን ቦታ የተለመድ እንደሆነ ወ/ሮ ሰሎሜ ይናገራሉ። ''የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚንስትር የሚለውን ቦታ ወንዶቹም ስለማይፈልጉት እኛ ላይ መውደቁ አይቀርም። ባህል እና ቱሪዝም ሚንስቴርም ቢሆን ለአገር ያለውን ፋይዳ ብረዳም ከሌሎች ሚንስትር መስሪያ ቤቶች ጋር ሲነጻጸር ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ተቋም አይደለም። የተሻለ ብዬ የተመለከትኩት የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትርን ሹመትን ነው'' ይላሉ።

ከፆታ ተዋጽዖ ባሻገር በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ የእስልምና እምነት ተከታዮች መብዛታቸው የሙስሊሙን ህብረተሰው ውክልና ያጎለዋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ከሚል ናቸው።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ''በኢትዮጵያ የሚገኙ ሙስሊሞች መባላችን ቀርቶ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እየተባልን ባለንበት በዚህ ሰዓት፤ የአገራችን ሰላም እና እድገት ሙስሊሙም ክርስቲያኑም በጋራ ቆሞ እንደሚያጸናው ገዢው ፓርቲ ተረድቶት ይህን እርምጃ እንደወሰደ ነው የሚገባኝ'' ይላሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ''ወደፊትም የሚመጣውም ይሁን አሁን ያለው ሥርዓት ሙስሊሙን ካላማከለ የትም አይደርስም'' ባይ ናቸው።

በተቃራኒው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልሳን እና ቋንቋዎች ጥናት መምህር የሆኑት ዶ/ር ኢድሪስ ሞሃመድ በበኩላቸው ''ግለሰቦቹ የሚወክሉት ፓርቲያቸውን እንጂ ሃይማኖትን አይደለም።''

''በዚህ ቀመር መሄዱ ብዙም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። እኚህ ሰዎች የሚያገለግሉት ፓርቲ ወይም መንግሥት ከሃይማኖት ጋር የማይጎዳኝ ነው። የካቢኔ አባላቱ ሃገር ሊያገለግሉ እንጂ ሰዎቹ እዚያ ተቀመጡት የሃይማኖት ሥራ ለመስራት አይደለም'' በማለት ይከራከራሉ።

በዚህ የካቢኔ ሹመት ውስጥ ሙስሊም ባይካተት ኖሮ ተገለናል የሚል ቅሬታ መምጣቱ አይቀሬ ነው። እኔም እያልኩ ያለሁት የሃይማኖት፣ የብሄር ወይም የፆታ ተዋጽዖ አይመጣጠን አይደለም። ግን እንደ ልዩ ክስተት ተደርጎ መታየት የለበትም በማለት ዶ/ር ኢድሪስ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።

በካቢኔ ሹመቶች ላይ ብሄር፣ ፆታ እና ሃይማኖት ላይ ትኩረት ማድረግ አቁመን ብቃት ላይ የተመሰረት ሹመት ብቻ መካሄድ አለበት የሚሉት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጸሑፍ እና ግጭት አፈታት መምህር የሆኑት አቶ ገብረኢየሱስ ተክሉ ናቸው።

አቶ ገብረኢየሱስ ''በሚንስትርነት ቦታዎች ላይ መስፈርት መሆን ያለበት ችሎታ ብቻ ነው። ፆታን ወይም ሃይማኖትን ከግምት ውስጥ አስገብተን ሹመት ሰጥተን ስራውን ማለማመድ የለብንም'' በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

አቶ ገብረኢየሱስ ''በሚንስትር ቦታዎች የሚመደቡ ሰዎች በችሎታቸው ብቻ እንጂ በብሄራቸው፣ በፆታቸው ወይም በሃይማኖታቸው መመደብ የለባቸውም'' በማለት ይከራከራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ