በአሜሪካ እርቃኑን የሆነ ተኳሽ አራት ሰዎችን በጥይት ገደለ

ጥቃቱ የተፈፀመበት ምግብ ቤት Image copyright Getty Images

በአሜሪካዋ ግዛት ቴኒሲ ወደሚገኝ አንድ ምግብ ቤት እርቃኑ ገብቶ ተኩስ የከፈተ ግለሰብ አራት ሰዎችን በጥይት ገድሏል።

ተኳሹ ምግብ ቤቱ ውስጥ ሊነጋጋ ሲል ዘው ብሎ በመግባት ተኩስ እንደከፈተም ታውቋል።

ፖሊስ የተኳሹን ማንነት የ29 ዓመቱ ትራቪስ ሬይንኪንግ እንደሆነ ያሳወቀ ሲሆን ፍለጋ ላይ መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

ይሄው ግለሰብ ባለፈው ዓመትም ዋይት ሀውስ አካባቢ የተከለከለ ቦታ በመግባት ለእስር ተዳርጎ እንደነበርም የናሽቪል የፖሊስ ቃል አቀባይ ዶን አሮን ገልፀዋል።

በምግብ ቤቱ ሲስተናገድ የነበረው ጄምስ ሻው ከተኳሹ መሳሪያውን በመንጠቅ የብዙዎችን ህይወት ያዳነ ሲሆን "እኔ ጀግና ለመሆን አይደለም ይህንን ያደረግኩት" እንዳለ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

እሁድ በነበረውም ጋዜጣዊ መግለጫ ጄምስ ሻው የመሳሪያ ተኩስና የመስታወት መሰበር እንደሰማ እንዲሁም ሰዎችም ራሳቸውን ለማዳን ከአካባቢው ሲሮጡ እንደነበር ገልጿል።

በወቅቱም በምግብ ቤቱ መፀዳጃ ቤት አካባቢ ተደብቆ የነበረ ሲሆን ተኳሹም በበበሩ በኩል ተኩሶ እጁን አቁስሎታል።

"በዚያን ወቅት ነበር የወሰንኩት፤ በሩን መቆለፍ እንደማይቻል ስለገባኝ ከገደለኝም በቀላሉ አይሆንም አልኩ" ብሏል።

ጥቃት ፈፃሚው ተኩሱን ሲያቆም ሻው በበሩ እንደመታውና መሳሪያውን ነጥቆ እንደወረወረው ተናግሯል።

ተኳሹም እግሬ አውጭኝ ብሎ እንደሸሸ ታውቋል።

Image copyright Reuters

የምግብ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዋልዝ ኤህመር፤ ሻውን ስለፈፀመው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው ከጋዜጣዊ መግለጫም በኋላ አቅፈው አድናቆታቸውን ገልፀውለታል።

"በህይወት ውስጥ ብዙ ጀግኖችን ለመተዋወቅ ከባድ ነው፤ አንተ የኔ ጀግና ነህ" ብለውታል።

ሻው እጁ ላይ ያለውን ቁስል ለመታከም ሆስፒታል በገባበት ወቅትም አንዲት ሴት ልጅ ህይወቷን እንዳተረፈላት በመግለፅ ምስጋናዋን አቅርባለታለች።

ፒክ አፕ መኪና ይዞ ቦታው ላይ የደረሰው ተኳሽ ሁለት ሰዎችን ከምግብ ቤቱ ውጭ አግኝቶ የተኮሰባቸው ሲሆን ወደ ውስጥም ገብቶ ተኩሱን እንደቀጠለ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ የሞቱ ሲሆን አራተኛው ሆስፒታል ገብቷል።

ፖሊስ ተኳሹ የገደለበት መሳሪያ በአሜሪካ ውስጥ በጅምላ የሚገድሉ ሰዎች የሚተኩሱት ኤአር15 የሚባለው መሳሪያ እንደሆነ አሳውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች