ደቡብ አፍሪካዊያን ሴቶች የኑክሌር ስምምነትን በማስቆማቸው ተሸለሙ

ሊዝ ማክዳይድ እና ማኮማ ላካላካላ Image copyright GERALD PETERSEN/ GOLDMAN ENVIRONMENTAL PRIZE
አጭር የምስል መግለጫ ሊዝ ማክዳይድ እና ማኮማ ላካላካላ

ሁለት የደቡብ አፍሪካ ሴቶች በሚስጥር ሲደረግ የነበረን የባለ ብዙ ቢሊየን ዶላር የኑክሌር ስምምነትን ተቃውመው ባደረጉት ጥረት ለስኬት በመብቃታቸው ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጥን ከፍተኛ ሽልማት አሸነፉ።

ማኮማ ላካላካላ እና ሊዝ ማክዳይድ ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ ጋር በመሆን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የነበራትን ዕቅድ በመቃወም ለአምስት ዓመታት የዘለቀ የፍርድ ቤት ሙግት አድርገዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባለ 76 ቢሊዮን ዶላር የግንባታ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

በተጨማሪም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ከስምንት ዓመታት በፊት በዚሁ የኑክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ በጋራ ስምምነት ፈርመው ነበር።

ሁለቱ ሴቶች እንዳሉት ስምምነቱ የተደረሰው ተገቢው ውይይት በፓርላማ ውስጥ ሳይደርግ ነው በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተገቢ መሆኑን ተቀብሎ ዕቅዱ ሕገ-ወጥና ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ነው በሚል ውሳኔ ሰጥቷል።

የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታን በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች ትችት የቀረበ ሲሆን የወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ንህላህላ ኔኔ ዕቅዱ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ተቃውመውት ነበር።

ተቃዋሚዎች ግንባታው ለጃኮብ ዙማ በቀጥታ ጥቅም ያስገኛል ብለው ይተቻሉ። በዚህ ዕቅድ ምክንያትም ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱን አላፀድቅም በማለታቸው በዙማ ከስልጣናቸው ተነስተው ቆይተዋል።

ባለፈው ዓመት የተላለፈው ተጠቃሽ የፍርድ ቤት ውሳኔ የትኛውም አይነት የኑክሌር ኃይል ግንባታ ዕቅድ በመጀመሪያ በፓርላማው ተቀባይነት ማግኘት ሲኖርበት ሕዝብም ሊያውቀው ይገባል ተብሏል።

ጉዳዩን ፍርድ ቤት በማድረስ ስኬታማ የሆኑት እንስቶች ማኮማ ላካላካላ እና ሊዝ ማክዳይድ በፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ሁለት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖችን ይወክላሉ።

"ሁለታችንም ማንኛውንም ኢፍትሃዊነት ለመታገል በፅናት ቆመናል። በትግል ያገኘናቸውን መብቶች ማስጠበቅ እንፈልጋልን" ስትል ማኮማ ላካላካላ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የተፈጥሮ አካባቢን ለመጠበቅ የሚደረጉ ሕብረተሰብ ተኮር ጥረቶችንና ስኬቶችን እውቅና የሚሰጠው ጉልድማን የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት "የአካባቢ ጥበቃ ጀግኖች" በሚል በየዓመቱ ሽልማት ያበረክታል።

ማኮማ ላካላካላ እና ሊዝ ማክዳይድም ለአካባቢ ጥበቃ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ይህንን ሽልማት አግኝተዋል።

በዚህ ዓመት ከሁለቱ ደቡብ አፍሪካዊያን እንስቶች በተጨማሪ ከኮሎምቢያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከቬትናምና ከአሜሪካ ግለሰቦች ሽልማቱን አግኝተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች