የቀይ ባሕር ሰላዮች፡ ሞሳድ ቤተ-እስራኤላዊያንን ለመታደግ የፈጠረው ሐሳዊ ሪዞርት

ሐሳዊ ሪዞርት

ከአርባ ዓመታት በፊት በወቅቱ የእራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለሞሳድ በሰጡት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ቤተ እስራኤላዊያንን በድብቅ በሱዳን በኩል ወደ እስራኤል ተወስደዋል።

ለዚህም የእስራኤል የስለላ ተቋም አባላት እንደ ሽፋን አሮስ በምትባለው የሱዳኗ የባሕር ዳርቻ ሐሰተኛ ቅንጡ መዝናኛ ሆቴልን ለዚህ ተልዕኮ ተጠቅመው ነበር።

የቢቢሲው ጋዜጠኛ ራፊ በርግም ይህንን አስደናቂ የስለላ ተልዕኮን ታሪክ የሚያወሳ "ሬድ ሲ ስፓይስ" የተባለ መጽሐፍ ጽፏል።

ይህንን ተልዕኮ በተወሰነ ደረጃ የሚያሳይ ታሪክ ከዚህ ቀደም ቢቢሲ አቅርቦ ነበር፤ እነሆ . . .

በደርግ መውደቂያ ዋዜማ እስራኤል ስላካሄደችው «ዘመቻ ሰለሞን» ብዙ ሰው ያወጋል። 14 ሺህ ቤተ-እስራኤላዊያንን ከታደገው ከዚህ ምስጢራዊ ዘመቻ አስር ዓመት በፊት በሱዳን ስለሆነው ነገር የሚያውቅ ግን እምብዛም ነው።

አሮስ ይባላል። ሱዳን በረሀ ላይ በቀይ ባህር ዳርቻ ተንጣሎ የሚገኝ መንሸራሸሪያ፤ ቅምጥል ሪዞርት፤ የማይጠገብ።

ይህ ሥፍራ እስራኤል ሠራሽ ሐሳዊ መንሸራሸሪያ ነበር ቢባል ብዙ ሰው ለማመን የሚቸገረውም ለዚሁ ነው።

ስለዚህ ሪዞርት መልካምነት የሚያትቱ ሺህ በራሪ ወረቀቶች በጉዞ ወኪሎች በኩል ተበትነዋል። መዝናኛው በጄኔቫ በከፈተው ወኪል ቢሮው በኩል ለበርካታ «ቱሪስቶች» ትኬት ሽጧል። በመሆኑም አሮስን ማንም የሰላዮች ቤት አድርጎ ሊገምተው አይቻለውም ነበር።

"ሱዳን ውስጥ በጊዜው ከነበሩት መዝናኛዎች ጋር ሳወዳድረው፣ እኛ እንሰጥ የነበረው አገልግሎት ከሂልተን ሆቴል ቢበልጥ እንጂ አያንስም፤ እጅግ የሚያምር ቦታ ነበር፤ የሆነ «ከአረቢያን ናይትስ» ተረቶች ውስጥ አንዱን ነበር የሚመስለው። በውበቱ አፈዝ አደንግዝ ነገር ነበር» ይላል እስራኤላዊው የሞሳድ ባልደረባ ጋድ ሺምሮን ስለ አሮስ ሪዞርት ትዝታውን ሲያወጋ።

የሱዳን ቱሪስት ኮርፖሬሽን ራሱ የሚኩራሩበት ቦታ ነበር። ሥፍራውን እያከራየ ረብጣ ሪያል ሲያፍስ ነበር። ራሳቸውን አውሮፓዊ ባለሐብቶች ብለው ላስመዘገቡ የጎብኚ ቡድን አባላት ቦታውን እያከራየ፣ እያስጎበኘ ኖሯል። ስለነገሩ አንደም ሳያውቅ።

ጨረቃና ከዋክብት ወከክ ብለው የሚታዩበት፣ ሕልም እንጂ እውን የማይመስል የነበረው ይህ ሪዞርት፤ ጎብኚዎች ከዓመት በፊት ትኬት ቆርጠው ለጉዞ ተንሰፍስፈው የሚጠብቁት ነበር።

Image copyright GAD SHIMRON

ይህ ብዙ የተባለለት የበረሀ ገነት ለካንስ ሞሳድ የፈጠረው ሐሳዊ መዝናኛ እንጂ ሌላ አልነበረም።

ለምን ዓላማ ማለት ተገቢ ጥያቄ ይመስላል።

መልሱ "ኢትዮጵያዊ ቤተ-እስራኤላዊያንን ለመታደግ" የሚል ነው።

ከ1980ዎቹ አንስቶ ለአራት ዓመታት የሥራ ላይ የነበረው ይህ ሪዞርት ሞሳድ አምጦ የወለደው ኅቡዕ የሰላዮች መናኸሪያ እንደነበር የታወቀው እጅግ ዘግይቶ ነው።

በሺ የሚቆጠሩ ከኢትዯጵያ የሾለኩ ቤተ እስራኤላዊያንን በጥንቃቄ ወደ እስራኤል ምድር ለመጓጓዝ ነበር ይህ ሁሉ የሆነው። ምክንያቱም ሱዳን በዚያን ወቅት ለእስራኤል በጄ የምትል አገር አልነበረችም፤ እንዲያውም ከአረብ ጠላቶቿ አንዷ ነበረች። ይህ ኀቡእ ዘመቻ ታውቆ ቢሆን የብዙ ሺህ ቤተ-እስራኤላዊያን ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችል ነበር።

«ጥብቅ የአገር ምስጢር ነበር። ቤተሰቦቼ እንኳ ስለነገሩ የሚያውቁት ነገር አልነበረም» ይላል ጋድ ሺምሮን፣ የቀድሞ የሞሳድ ባልደረባ።

ኦሪትን የሚከተሉትን ቤተ-እስረኤላዊያን ሃይማኖታቸውንም ሆነ ማንነታቸውን ለማንም እንዳይገልጡ፣ ማንነታቸው ከታወቀ ግን በሱዳን የጸጥታ ኃይሎች አደጋ እንደሚጋረጥባቸው ይነገራቸው የነበረው መቀመጫውን በአሮስ መዝናኛ ባደረገው በዚህ ኅቡዕ የሞሳድ ቡድን በኩል ነበር።

Image copyright AAEJ ARCHIVES ONLINE

ቤተ-እስራኤላዊያን በተመለከተ መላ ምቱ ብዙ ነው።

ከአስሩ የጠፉ የእስራኤል ነገዶች ዝርያቸው የሚመዘዝ እንደሆነ ይነገራል። ሌሎች ሰነዶች ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት 950 ዓመተ ዓለም አካባቢ የንግሥት ሳባና የንጉሥ ሰለሞንን ልጅ አጅበው ወደ ኢትዮጵያ ምድር የመጡ እስራኤሎች የልጅ ልጅ ልጆች እንደሆኑ ይገምታሉ። ሌሎች ደግሞ ትልቁ የአይሁድ ቤተ አምልኮ በ586 ዓመተ-ዓለም ሲፈርስ ወደ ሐበሻ ምድር የተሰደዱ እንደሆኑ ይገምታሉ።

ሞሳዶች አሮስ መዝናኛን ገንብቶ ለመክፈት 12 ወራትን ወስዶባቸዋል።

ከአገሬው 15 የሚሆኑ የቤት ሠራተኞችን፣ ሾፌሮችን፣ የወጥ ቤት ሠራተኞችን ቀጥረዋል። አንዳቸውም ግን የሆቴሉን ኅቡዕ ተግባር አያውቁም ነበር። አለቆቻቸው የሞሳድ ሰዎች እንጂ የወጥ ቤት ሰዎች እንዳልሆኑ ያወቁት ከብዙ ዘመን በኋላ ነበር።

ምድር ቤት የሚገኘው እቃ ቤት ግን ማንም ዘው ብሎ ገብቶ አያውቅም፣ እዚያ ከድስቶች ጋር የርቀት መነጋገሪያ ስልኮች ነበሩ። ከቴላቪቭ የሚያገናኙ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ