የቢንላደን የቀድሞ ጠባቂ በጀርመን

Sami A - file photo Image copyright Funke Foto Services

በአንድ ወቅት የኦሳማ ቢን ላደን ጠባቂ የነበረው የቱኒዝያ ዜግነት ያለው ሰው ከአውሮፓውያኑ 1997 ጀምሮ በጀርመን መጠለያ ጣቢያዎች መኖሪያውን እንዳደረገ ተገለፀ።

የጀርመኑ የቀኝ አክራሪ አማራጭ ፓርቲ፤ ሳሚ ኤ ስለሚባል ሰው ማንነት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎም የሰውየው ምስል በክልሉ መንግሥት ይፋ ሆኗል።

የጀርመን መገናኛ-ብዙሃን የሰውየውን ሙሉ ስም የግል መረጃውን ለመጠበቅ ሲባል እንዳልዘገቡ ተገልጿል።

የጂሃድ አራማጆች ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ብሎ የካደ ሲሆን፤ የጀርመን መንግሥትም ግለሰቡን ወደ ቱኒዝያ ለመመለስ ይዞት የነበረውን እቅድ እንግልትና ስቃይ ይደርስበታል በሚል ስጋት እንደሰረዘው አስታውቋል።

ቢንላደን አልቃይዳ ተብሎ የሚጠራውን የጂሃድ አራማጅ ቡድንን ይመራ የነበረ ሰው ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2001ም አሜሪካ ምድር ላይ ለደረሰው የሽብር ጥቃት ተጠያቂ ነው ተብሎ ነበር።

በ2011 ደግሞ በአሜሪካ ልዩ ኃይል ፓኪስታን ውስጥ ታድኖ ተገድሏል።

አሜሪካ ላይ በተፈፀመው የመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ተሳታፊ ከነበሩት አጥፍቶ ጠፊ ፓይለቶች መካከል ሦስቱ በሰሜናዊ ጀርመን በምትገኘው ሀምቡርግ የአልቃይዳ ህዋስ አባል ነበሩ።

በአውሮፓውያኑ 2005 የጀርመን ፀረ-ሽብር ፍርድ ላይ አንድ ምስክር በሰጠው ቃል ይህ ሳሚ ኤ የተባለው ሰው በአውሮፓዊያኑ 2000 በአፍጋኒስታን ውስጥ የቢንላደን ጠባቂ ሆኖ እንደሰራ መስክሯል።

ምንም እንኳን በጊዜው ሰውየው ቢክድም የወቅቱ ዳኛ የነበሩት ዱሴልዶርፍ ምስክሩን አምነውታል።

በአውሮፓውያኑ 2006ም ሳሚ ኤ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ምርመራ ተደርጎበት የነበረ ሲሆን ክስ ግን አልተመሰረተበትም።

ሳሚ ኤ ከጀርመናዊ ሚስቱና ከአራት ልጆቹ ጋር በምዕራባዊ ጀርመን በምትገኘው ቦቹም በምትባል ከተማ ነዋሪ ነው።

ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ የተለያዩ ቴክኖሎጂ ስልጠናዎችንም ወስዷል። የጥገኝነት ጥያቄውን ባለስልጣናቱ ለደህንነት ጠንቅ ነው በሚል አልተቀበሉትም።

በየቀኑም ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ሪፖርት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ተጠርጣሪ የሆኑ የጂሃድ አራማጆች በሰሜን አፍሪካ ባሉ ሀገራት ስቃይ እንደሚደርስባቸው የጀርመን መንግሥት መረጃ ያሳያል።

በዚህም ምክንያት ቱኒዝያም ሆነ ጎረቤት አረብ ሀገራት ስደተኞችን ለመመለስ ደህንነታቸው የተጠበቁ አገሮች አይደሉም ተብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች