"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7?

ፍቅር እስከ መቃብር በአይፎን

ቴክኖሎጂ ትንፋሽ አሳጣን። በመረጃ ወጀብ ተናጥን፤ ተናወጥን።

ማን ይሆን በዚህ ዘመን ከቀልቡ የሆነ? ማን ይሆን ረዥም ልቦለድ ለመጨረስ አደብ የገዛ? ከብጥስጣሽ የበይነ-መረብ የመረጃ ሱናሚ ራሱን ያዳነ!?

የዳሰስናቸው፣ የዳበስናቸው፥ የገለጥናቸው፣ አንብበን ሼልፍ ላይ የደረደርናቸው መጻሕፍት ዘመን ሊሽራቸው ነው። በፖስታና በሕዝብ ስልክ ላይ የደረሰው መገፋት ሊደርስባቸው ነው። ለዝመናና ለዘመን የሚሰው ባለተራዎች ለመሆን እየተንደረደሩ ነው።

ከትናንት በስቲያ የነርሱ ቀን ነበር። የዓለም የመጻሕፍት ቀን! እኛ ዛሬ ብናስባቸው እምብዛም አልዘገየንም።

"ሽፋናቸውን ካልዳሰስኩ፣ ጠረናቸው ካላወደኝ፣ ያነበብኩም አይመስለኝ" ዓለማየሁ ገላጋይ

እርግጥ ነው መጻሕፍት ከናካቴው ደብዛቸው አይጠፋ ይሆናል። ሆኖም ብዙ ዘመን አብረውን እንደማይዘልቁ ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው። ለምሳሌ ገና ከአሁኑ ከተፈጥሯዊው መዳፋችን እየተንሸራተቱ በቅንጡ ስልኮቻችን በኩል ራሳቸውን በቴክኖሎጂያዊ "መንፈስ" መግለጥ ጀምረዋል። ካላመናችሁ ብሩክን ጠይቁት።

ወጣት ብሩክ ኃይሉ ላለፉት አምስት ወራት መጻሕፍትን ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚዶል "ሎሚ" የሚባል መተግበሪያ (App) ከወዳጆቹ ጋር አበጅቶ፣ የበይነመረብ መጻሕፍት መደብር ከፍቶ፣ በድረ-ገጽ መጽሐፍ እየቸረቸረ ይገኛል።

ሎሚ የተሰኘው ይህ የስልክ መተግበሪያ እስካለፈው ሳምንት ብቻ 16ሺ ሰዎች በእጅ ስልኮቻቸው ጭነውታል።

ለመሆኑ ደራሲዎቻችን ይሄን "ጉድ" ሰምተዋል? ከሰሙስ ምን አሉ?

የዓለም መጻሕፍት ቀንን አስታከን የተለያዩ ትውልድን የሚወክሉ ደራሲዎች ሃሳብ ጠይቀናል፡፡

የቀንዲል ቤተ ተውኔት መሥራችና እስከ ቅርብ ጊዜም የኢትዯጵያ ደራሲያን ማኅበር ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ጋሽ አያልነህ ሙላት ድንገት በአንድ ጊዜ ወደ በይነ-መረብ መገስገሳችንን እምብዛምም የወደዱት አይመስልም።

"ይሄ መጻሕፍትን ኦንላይን የመሸጡ ጉዳይ እኛ ደራሲያን ማኅበርም መጥተው ጠይቀውናል። እና ብዙዎቻችን ከቴክኖሎጂው ጋር ግንኙነት የለንም። ግራ ተጋብተን ምንድነው ጥቅሙ? ጉዳቱስ? ደራሲውስ ምን ይጠቅማል? እያልንናቸው ነው…" ሲሉ ብዥታ መኖሩን ካተቱ በኋላ ስጋታቸውን ያስከትላሉ።

"...ገና በንባብ ዳዴ የምትል አገር ናት። በዚህ ወቅት እንደዚህ ዓይነት የኦንላይን ሽያጭ ሲጀመር ይሄ ዳዴ የሚለው የንባብ ባሕል የሚቆረቁዝ ይመስለኛል።" ይላሉ።

ግን እኮ ጋሽ አያልነህ…!ሰው በምንም ያንብብ፥ እንዴትም ያንብብ፣ ዞሮ ዞሮ ዋናው ማንበቡ አይደለም ሊገደን የሚገባው? ስንል ጠየቅናቸው፥

"የቴክኖሎጂ ጠላቶች ሆነን አይደለም እኮ" ብለው ጀመሩ አቶ አያልነህ፤ "...በቴክኖሎጂ የተነሳ ንባብ ጋ እየተፋታ ያለ፣ በፌስቡክ የተወሰኑ ነገሮችን እየወሰደ አነበብኩ ብሎ የሚል ወጣት፣ እንደገና መጽሐፍቱን በዚህ በኩል ይሰራጭ ማለት የንባብ ባሕሉን አይገድለውም ወይ? የሚል ስጋት ነው ያለኝ።"

"መጽሐፍ በኢንተርኔት አንብቤ አላውቅም" ደራሲ አስፋው ዳምጤ

እረ ለመሆኑ! ከምኑም ከምኑም በፊት፥ በኪንድል ወይም በስልካችሁ ወይም በኮምፒውተሮቻችሁ መጽሐፍ አንብባችሁ ታውቃላችሁ ወይ? አንድ አንዶቹን ብለንም ነበር፤ የ"ጉንጉኑ" ጋሽ ኃይለመለኮት የተወሰነ ሞካክረዋል። ደራሲ አስፋው ዳምጤ ግን የሉበትም።

ከጥንት ከጠዋቱ የኩራዝ አሳታሚ ጀምሮ የነበሩት ጋሽ አስፋው ዳምጤ ለዚህ ኤሌክትሮኒክስ ለሚባለው የመጽሐፍ ግብይት ፍጹም ባዕድ ናቸው። ዘመናቸውን ሙሉ ከንባብ ያልተለዩት ጋሽ አስፋው በሕይወታቸው አንድም ቀን ይህን የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍ የሚባልን ነገር አለመጠቀማቸው እምብዛምም ላይገርም ይችላል።

"የተሟሉ ሆነው የሚቀርቡ አይመስለኝም" ይላሉ፥ የኦንላይን መጻሕፍትን የማያነቡበትን ምክንያት ሲያስረዱ። ይህንኑ የጋሽ አስፋውን ስሜት ብዙዎቹ ይጋሯቸዋል።

ደራሲ ዓለማየሁ በሎሚ የበይነ-መረብ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ በምናባዊ ሼልፍ ላይ ተደርድሮ የሚሸጥ አንድ መጽሐፍ ቢኖረውም ይሄ የኦንላይን ነገር አይሆንለትም። ምቾትም የሚሰጠው ነገር አልሆነም።

"በሶፍት ኮፒ አንብቤ የጨረስኳቸው መጻሕፍት አሉ። ኦሪጅናል ቅጂያቸውን ሳገኝ ግን በድጋሚ አነባቸዋለሁ። ለምን ካልከኝ ያነበብኳቸው ስለማይመስለኝ" ይላል ዓለማየሁ።

በዚያ ላይ "ከነፍስህም ጋር ያለ ቅርርብ አለ። መጽሐፍህ ስንት ውጣ ውረድ አልፎ፥ ታትሞ ለመጀመርያ ጊዜ እጅህ ሲገባ ያለውን ስሜት አስበው። ያን ሁሉ ታጣለህ!" ይልና ሐሳቡን ያጠናክራል።

"ለምን እንደሆን አላውቅም ሶፍትኮፒ ሳነብ ነባሩን እርካታዬን አይሰጠኝም።" የሚሉት አቶ ኃይለመለኮት በበኩላቸው ንጽጽሩን ከዚህም በላይም ያሰፉታል፤ "በካሴት ሙዚቃ መስማትና ሙሉ ባንድ ሲጫወት በአካል ተገኝቶ መታደም አንድ ነው?"

የሎሚ የስልክ መተግበሪያ ላይ ድርሰቶቻቸውን እየሸጡ ከሚገኙ ወጣት ደራሲዎች መሐል የሸገር ሬዲዮው የወግ ጽሑፎች ተራኪ ግሩም ተበጀ ይገኝበታል።

ግሩም ባሕላዊው የኅትመት አሠራር የሚታክት ሂደትን ማለፍ ይጠይቃል ይላል። ደርዝ ያላቸው አሳታሚዎች ገና እንዳልተወለዱ ካብራራ በኋላ የሎሚ መተግበሪያ ወደ ገበያው መምጣት ጊዜውን የጠበቀ እንደሆነ ይናገራል።

ግሩም እውነት አለው። በተለምዷዊው አሠራር አንድ መጽሐፍ ተጽፎ አንባቢ እጅ እስኪገባ በአማካይ መንፈቅ ይወስድበታል፡፡ በነ ሎሚ የቀን አቆጣጠር ግን ጠዋት የተጻፈ መጽሐፍ ከሰዓት አንባቢ እጅ ሊደርስ ይችላል፡፡ አላጋነንኩም፡፡ የመተግበሪያውን ፈጣሪ ወጣት ብሩክ ይህንኑ አረጋግጦልኛል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7?''

ጋሽ አስፋው ዳምጤ እና ወጣት ብሩክ ኃይሉ

ይሄ ነገር በትውልዶች መካከል ያለ ልዩነት ይመስላል።

ጋሽ አስፋው ዳምጤ አንድም የኦንላይን መጽሐፍ አንብበው እንደማየውቁ እንደተናገሩት ሁሉ የሎሚ የበይነ መረብ መጽሐፍ መደብሩ መሥራች ወጣት ብሩክ ኃይሉ፥ ነፍስና ሥጋ ያለው፣ ደንበኛውንና መደበኛውን መጽሐፍ ከዳሰስ ረዥም ጊዜ ሆኖታል።

ለመጨረሻ ጊዜ መቼ የሚዳሰስ መፃሕፍ እንዳነበበ ሲጠየቅ፤ አጠር ያለ ሳቅ ከሳቀ በኋላ "እኔ እንደነገርኩህ ሚሊኒያ ለሚባለው ለአዲሱ ትውልድ እቀርባለሁ፤ በእኛ ጊዜ ደግሞ ስናድግ ከመጽሐፍ የበለጠ ዲጂታል ከሆኑ ነገሮች ጋር ያለን ቁርኝት ስለሚበልጥ፣ ታላላቆቼ ለሚዳሰሱ መጻሕፍት ትዝታ ሊኖራቸው ይችላል። እኔ ግን የለኝም፤ ሁሉንም ነገር ስልኬ ላይ ማግኘት እመርጣለሁ..." ሲል ይናገራል።

"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7 የምናነብበት ዘመን እየቀረበ ይመስላል።

ተያያዥ ርዕሶች