የቱርክ መንግሥት በመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ጋዜጠኞችን ለእስር ዳረገ

የጋዜጠኞቹን እስር የተቃወሙ ሰዎች ፎቷቸውን ይዘው Image copyright AFP

የቱርክ ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ናቸው ያላቸውን 13 ጋዜጠኞችን ለእስር ዳርጓል። ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቁጣን ቀስቅሷል።

ጋዜጠኞቹ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት በማቅረብ የሚታወቀው ተቃዋሚው 'ቹምሁሪየት' ተብሎ የሚታወቀው ጋዜጣ ሰራተኞች ናቸው።

ችሎት ፊት ከቀረቡት ጋዜጠኞች መካከል ሦስቱ ነፃ ሲወጡ፤ ሌሎቹ ደግሞ ጉዳያቸው በይግባኝ እንደተንጠለጠለ ነው።

ጋዜጠኞቹ ለእስር የተዳረጉት ከሁለት ዓመት በፊት ከሸፈ የተባለው መፈንቅለ-መንግሥትን ተከትሎ ነው።

የቱርክ ባለስልጣናት ጋዜጠኞቹን በአሸባሪነት የሚወነጅሏቸውን የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲና ለከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርጋቸውን የሀይማኖት መሪውን ፌቱላህ ጉለንን የመሳሰሉትን በመደገፍ ነው።

በግዞት አሜሪካ የሚገኙት ጉለንንም አሜሪካ ለቱርክ አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታውቃለች።

የመፈንቅለ-መንግሥቱን ሙከራ ተከትሎ ሃምሳ ሺህ ግለሰቦች ዘብጥያ የወረዱ ሲሆን ከ150 ሺህ በላይ ግለሰቦች ደግሞ ከሥራ ተባረዋል። ከእነዚህም ውስጥ ጋዜጠኞች፣ ፖሊሶች፣ የሠራዊት አባላትና መምህራን ይገኙበታል።

ረቡዕ እለት ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ካላቸው 13 ጋዜጠኞች መካከል በሀገሪቱ ስመ-ጥር የሆኑት አዘጋጅ ሙራት ሳቡንቹ፣ የካርቱን ባለሙያው ሙሳ ካርት እንዲሁም አምደኛው ካድሪ ጉርሴል ይገኙበታል።

የጋዜጣው ኃላፊ አኪን አታላይ ከአምስት መቶ ቀናት የእስር ጊዜ በኋላ ሰባት ዓመት የእስር ፍርድ ተፈርዶበታል።

በአውሮፓውያኑ 1924 የተመሰረተው ይህ ጋዜጣ መንግሥት በማያፈናፍነው የሚዲያ ከባቢ ለነፃነት የቆመ ጋዜጣ ሲሆን የቱርኩ ፕሬዚዳንትን ሪሴፕ ታይፕ ኤርዶጋንን በመገዳደደርም ይታወቃል።

ረቡዕ ከችሎቱ በፊት ጋዜጣው በፊት ገፁ ይዞት በወጣው ርዕሰ-አንቀፅ "ይህ ጭካኔ ይብቃ" የሚል ሲሆን፤ ከውሳኔው በኋላ በድረ-ገፁ ላይ "በታሪክ ፊት ታፍራላችሁ" የሚል ፅሁፍ ይዞ ወጥቷል።

የቱርክ ፕሬዚዳንት የፕሬስ ነፃነትን በመገደብ ብዙ ጊዜ ይተቻሉ።

በባለፈው ወርም ከፌቱላህ ጉለን ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል 25 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል።

ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ቡድኖችም የቱርክ መንግሥትን መገናኛ ብዙሃንን በማፈን ይከሳሉ።

ሲፒጄ ተብሎ የሚታወቀው ለጋዜጠኞች ጥበቃ የቆመ ድርጅትም ጉዳዩን አውግዞ ጋዜጠኞቹ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።