በሩዋንዳ የጅምላ መቃብር ተገኘ

Image of skulls in Rwanda Image copyright AFP

በአውሮፓውያኑ 1994 ከተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ የሚታመን የጅምላ መቃብር በሩዋንዳ ተገኝቷል።

የመቃብሩ ስፍራ ከመዲናዋ ኪጋሊ ወጣ ብላ በምትገኝ ጋሳቦ ግዛት የተገኘ ሲሆን 200 የሚሆኑ አስከሬኖች ተገኝተዋል።

በጭፍጨፋው ሦስት ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች ጠፍተው የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ሰዎች በዚህ የጅምላ መቃብር ስፍራ ሊገኙ ይችላሉ የሚል አመኔታ አላቸው።

በመቶ ቀናት ውስጥ 800 ሺህ የሚሆኑ የቱትሲ ጎሳ አባላትና ለዘብተኛ ሁቱዎች በሁቱ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል።

ይህ የጅምላ መቃብርም የተገኘው የግድያውን ጅማሮ ማስታወሻ ከተደረገ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው።

አንዲት ሴት ብዙ አስከሬኖች ቦታው ላይ ተጥሎ ተገኝቷል ማለቷን ተከትሎ ነው በጎ ፈቃደኞች የፍለጋ ሥራውን የጀመሩት ተብሏል።

አስከሬኖቹ በተሰሩ ቤቶች ስር በመቀበራቸው ምክንያት አጽሞቹን ለማውጣት ብዙ ቤቶች ፈርሰዋል።

"እስካሁን አራት የጅምላ መቃብሮችን አግኝተናል ፍለጋውም ይቀጥላል" በማለትም በዘር ማጥፋት ለተጎዱ የእርዳታ ድርጅት የሚለግሰው ኢቡካ የተሰኘው ኃላፊ ቲዎጅን ካባጋምቢሬ ለሩዋንዳው ጋዜጣ ኒውስ ደይ ተናግረዋል።

የዘር ጭፍጨፋውን ያደረሱት አካላት የፍርድ ጊዜያቸውን አጠናቀው ከእስር ተለቀዋል።

የጅምላ መቃብሩን የሚያውቁ ሰዎች እስካሁን ድረስ ጉዳዩን ከመግለፅ ለምን ታቀቡ የሚል ጥያቄ በሀገሪቱ ሚዲያ ላይ እንደተፈጠረ የቢቢሲ አፍሪካ የፀጥታ ጉዳዮች ዘጋቢው ቶሚ ኦላዲፖ ገልጿል።

ካባጋምቢሬ በበኩላቸው አምስተኛ የጅምላ መቃብር ፍለጋ ላይ መሆናቸውን አሳውቀው፤ በዘር ጭፍጨፋ ጥፋተኛ የሆኑ ግለሰቦችም "የምንወዳችውን ግለሰቦች የተቀበሩበት ቦታ ለማሳየት ቸላ ብለዋል" ብለዋል።

የዘር ማጥፋቱ ተጠቂ የሆኑ ቤተሰቦችም ይህንን አካባቢ የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ለማግኘት ሲያስሱ እንደነበር ተገልጿል።

"ወላጆቼ ተገድለው ከእነዚህ የጅምላ መቃብሮች መካከል አንዱ ውስጥ እንዳሉ መረጃ ደርሶኛል። እዚህ የመጣሁትም ለብሰው የነበረውን ቁርጥራጭ ልብስ መለየት ብችል በማለት ተስፋ አድርጌ ነው" በማለት ከጭፍጨፋው የተረፈች ኢዛቤል ኡዊማና ለኒውስ ደይ ተናግራለች።

"ማግኘቴን እርግጠኛ ከሆንኩ በትክክለኛ መንገድ ልቀብራቸው እፈልጋለሁ" ብላለች።

በአካባቢው የቢቢሲው ፕሩደንት ሴንጊዩምቫ በበኩሉ በሃገሪቱ ውስጥ ብዙ ያልተገኙ የመቃብር ሥፍራዎች እንዳሉ ገልጿል።

የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1994 ሲሆን ይህም የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ሀብያሪማና እንዲሁም የብሩንዲው አቻቸው ሲፕሪየን ንታርያምራ አውሮፕላናቸው ተተኩሶበት ከወደቀ በኋላ ነው።

ፕሬዚዳንቶቹም ከአውሮፕላን አደጋው አልተረፉም።

የሁቱ አክራሪ ቡድኖችም የጭፍጨፋ ዘመቻቸውን ከመጀመራቸው በፊት የቱትሲ ታጣቂ ቡድን የሆነውን የሩዋንዳ አርበኞች ግንባርን ለዚህ አደጋ ተጠያቂ አድርገዋል።

ተያያዥ ርዕሶች