መሻሻል ያላሳየው የኢትዮጵያ ፕሬስና የጋዜጠኞች ይዞታ

የጋዜጣ አንባቢዎች Image copyright Getty Images

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድን ይፋ ያደረገው የዚህ ዓመት የዓለም የጋዜጠኞችና ሃሳብን የመግለፅ ይዞታ ዘገባ ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት እርከን ከ180 የዓለም ሃገራት 150ኛ ላይ ሲያስቀምጣት፤ ኤርትራ ደግሞ ሰሜን ኮሪያን ቀድማ 179ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አመለከተ።

ዘገባው እንዳመለከተው ኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም 30 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ሃገር ጥለው እንዲሰደዱ ካስገደደው ስድስት ጋዜጦችን የመዝጋት የመንግሥት እርምጃ በኋላ በሃገሪቱ የፕሬስ ይዞታ ላይ ተጠቃሽ የሆነ መሻሻል አለመታየቱን ተቅሷል።

በተቃራኒው በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መንግሥት ተቺ የሆኑ ጋዜጠኞችን ለማሰርና ሕዝቡም የተወሰኑ የመገኛኛ ብዙሃን ስርጭቶችን እንዳይከታተል ለመከልከል ያስችለዋል ሲል ዘገባው ስጋቱን አስቀምጧል።

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘው ይህ ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው ዘገባው ላይ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ እንዲሰደዱ በማድረግና በማወከብ ከሚነሱ ሃገራት መከከል ትጠቀሳለች።

የድርጅቱ የአፍሪቃ ክንፍ ተጠሪ የሆኑት አርኖውድ ፍሮጀር ይህን ዘገባ ይፋ ሲያደርጉ ክትትል ያደረጉበት ጊዜ ከባለፈው ዓመት ጥር እስከአሁኑ ዓመት ጥር ወር ድረስ የተመለከቷውን ጉዳዮች እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አሁን ድረስ እንደ አውሮፓዊያኑ 2009 የወጣው የፀረ-ሽብር ሕግ ጋዜጠኞችን ያለፍርድ ለረጅም ጊዜ ለማሰር ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ሃገሪቱ በድጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በመሆኗ ጋዜጠኞች ያለእስርና እንግልት ሥራቸውን እንዳይሰሩ መሰናክል ነው" ሲሉ የጋዜጠኞችን ስጋት ተናግረዋል።

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ያወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ያለውን የጋዜጠኞች ሁኔታ ይገልፀዋል የሚለው በቅርቡ ከዓመታት እስር በኋላ የተፈታው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እየታተሙ ያሉት ጋዜጦች ቁጥር ጥቂት መሆኑን የሚጠቅሰው ውብሸት "ይህ ደግሞ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የሚያሳፍር ሁኔታ ነው። በተጨማሪም ምንም መሻሻል እንደሌለ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ የወጣው ሪፖርት በትክክል ይህንን የሚያንፀባርቅ ነው።"

ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ መንግሥት ያሉትን ሁኔታዎች ለማሻሻል በርካታ ዓመታት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የቆዩ ጋዜጠኞችን ከእስር እንዲወጡ አድርጓል። ይህ ደግሞ ለለውጥ በር ከፋች እርምጃ እንደሆነ የሚያምኑ በርካታ ሰዎች አሉ።

ውብሸትም ከእስር የመፍታቱ እርምጃ መልካም ጅምር እንደሆነ ቢያምንም ይህ ብቻ በቂ አይደለም ይላል። "አሁንም ፕሬሱ አደጋ ውስጥ ነው። ሃገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆኗ ጋዜጠኞች ያለፍርሃት ነፃ ሆነው እየሰሩ አይደለም። እነዚህ ሁኔታዎች በቀጣይ የማይሻሻሉ ከሆነ ደግሞ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ይቀጥላል" በማለት ስጋቱን ይገልፃል።

ሌላው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳናም ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታቱ የፕሬስ ነፃነት መሻሻል መገለጫ ነው ብሎ አያምንም። "መታየት ያለበት እስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች መፈታት ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ጉዳይ አሽቆልቁሎ የደረሰበት የሞት አፋፍ ላይ መሆኑ ነው" ይላል።

እርሱም ታስሮ እንደነበር የሚናገረው ኤሊያስ መጀመሪያም መታሰር የሌለባቸው ጋዜጠኞች ስለተፈቱ ብቻ በጋዜጠኞች ሥራ ላይ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምን ይናገራል።

"በጥቅሉ ሲታይ እስረኞችን መፍታት አንድ ነገር ነው።" የሚለው ኤልያስ "ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር የጋዜጠኝነት ሙያ አሁን ያለበት ደረጃ ነው። የተፈቱት ጋዜጠኞች ከመታሰራቸው በፊት ከነበረበት ደረጃ ወርዷል። የተፈቱት ጋዜጠኞች ይሰሩባቸው የነበሩት ጋዜጦች በሙሉ ጠፍተዋል" ሲል የፕሬሱ ምህዳር በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን አመልክቷል።

ነገር ግን ሁሉም የሚስማሙት በመንግሥት በኩል የተጀመሩት የለውጥ እርምጃዎች ተጠናክረው መገናኛ ብዙሃኑና ጋዜጠኞች ሳይፈሩና ሳይዋከቡ እንዲሰሩ የሚያስችሉ ህጋዊና ሌሎች ማዕቀፎች የሚመቻቹ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ተቋማት ከዓመት ዓመት በፕሬስ ይዞታ ከታችኛው ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሃገራት ተርታ ውስጥ ለመውጣት ያስችላታል ይላሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ