ለሽያጭ የሚያዘጋጅ 'የህፃናት ፋብሪካ' በናይጄሪያ

"የህፃናት ፋብሪካ" Image copyright AFP

አንድ መቶ ስድሳ ሁለት ልጆች "የህፃናት ፋብሪካ" ተብለው በሚጠሩ ወላጆቻቸውን ያጡ የህፃናት ማቆያዎች ውስጥ መገኘታቸውን የናይጄሪያ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

እነዚህ የህፃናት ፋብሪካ ተብለው የሚታወቁት ስፍራዎች ትክክለኛ ተግባር ምን እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።

ይህ ስያሜ አንዳንድ ጊዜ የተጣሉ ወይም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት የሚቆዩባቸው ቦታዎች ከመሆናቸው ባሻገር ህፃናቱ ለትርፍ የሚሸጡባቸው እንደሆነም ይነገራል።

ነገር ግን ቀደም ብሎ አጋጥሞ በነበረ ክስተት "የህፃናት ፋብሪካ" የሚለው ስያሜ ነፍሰ-ጡር ሴቶች እስኪወልዱ ድረስ የሚቆዩበትና ከወለዱ በኋላም ልጆቻቸው የሚሸጡበት ቦታ ነው።

ትናንት 162 የሚደርሱት ሕፃናት ከተገኙ በኋላ የሌጎስ ግዛት ወጣቶችና ማህበራዊ ልማት ሃላፊ የሆኑት አግቡላ ዳቢሪ ሲናገሩ "የህፃናቱን ደህንነት ለማረጋገጥ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት የሚቆዩባቸውን ሦስት ማዕከላትን መዝጋት አለብን። ከእነዚህ መካከልም አንዱ የህፃናት ፋብሪካ የሚባል ሲሆን ሁለቱ ያለተመዘገቡ ሕገ-ወጦች ናቸው" ብለዋል።

ሃላፊው ጨምረውም በእነዚህ የህፃናት ፋብሪካዎች ውስጥ የተገኙት ልጆች መንግሥት እውቅና በሰጣቸው ማቆያዎች ውስጥ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።