ካንዬ ትራምፕን በትዊተር በመደገፉ ዘለፋን እያስተናገደ ነው

Donald Trump and Kanye West at Trump Tower in New York City in December 2016. Image copyright Getty Images

አሜሪካዊውው ታዋቂ የሂፕ ሆፕ አቀንቃኝ ካንዬ ዌስት በቅርቡ በትዊተር ገፁ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ መስጠቱን ተከትሎ ብዙዎች ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ነው።

የ40 ዓመት እድሜ ያለው ካንዬ ትራምፕን በሚደግፉ በተከታታይ በትዊተር ካሰፈራቸው ፅሁፎቹ መካከል "አሜሪካን እንደገና ታላቅ ማድረግ" የሚለውን የፕሬዚዳንቱን መፈክርና በትራምፕ የተፈረመበት ቀይ ኮፍያም አጥልቆ ታይቷል።

"ከትራምፕ ጋር መስማማት ማንም አይጠበቅበትም ነገር ግን፤ የህዝቡ ግፊት ግን ትራምፕን ሊያስጠላኝ አይችልም" በማለት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

ትራምፕ በአፀፋ ምላሻቸው በትዊተር ላይ "ካንዬ አመሰግናለሁ! አሪፍ ነው" ብለዋል።

ካንዬ በተለያዩ ድረ-ገፆች ዘለፋን ማስተናገዱን ተከትሎም ባለቤቱ ኪም ካርዳሽያን ዌስት በበኩሏ ደግፋው ተከራክራለች።

"ባለቤቴን ጥላሸት ለመቀባት ለምትጣጣሩ የሚዲያ አካላት በሙሉ ካንዬ ቀውሷል እንዲሁም በትዊተር ገፁ ያሰፈረው ይረብሻል የሚለው አስተያየታችሁ አስፈሪ ነው። ሀሳቡን በነፃነት ስለገለፀና ራሱን ስለሆነ የአዕምሮ ጤንነት መጓደል ነው ብላችሁ ለመፈረጅ ወይ ፍጥነታችሁ! ትክክል አይደለም" ብላለች።

ካንዬና ትራምፕ የተዋወቁት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ሲሆን ባለፈው ረቡዕም ከትራምፕ ጋር "የድራጎንን ኃይል እንደሚጋሩ" እንዲሁም ትራምፕ "ወንድሙ እንደሆኑ" በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

ካንዬ ቺካጎ ያደጉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፉት ስምንት ዓመት ስልጣን ላይ ቢቆዩም "ችካጎ ምንም አልተቀየረችም" በሚል ተችቷቸዋል።

አስተያየቱም የትዊተር ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎችን ያበሳጨ ሲሆን አንድ የትዊተር ተጠቃሚም የዘፋኙን "ዘ ላይፍ ኦፍ ፓውሎ" የሚለውን ዘፈኑን በመጥቀስ "የዱሮው ካንዬ ናፈቀኝ" ብላለች።

ኪም ካርዳሽያን ትችቶቹን በማጣጣል" ካንዬ በመንጋዎች የሚንሸራሸር ሀሳብ አይደግፍም ለዚህም ነው የምወደው እንዲሁም የማከብረው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደሱ አይነት ተመሳሳይ አስተያየት የሚሰጡ እንደሱ አይፈረጁም እንዲያውም ይመሰገናሉ። ካንዬ ከጊዜው የቀደመ ነው" ብላለች።

ከእሷም በተጨማሪ ቻንስ ተብሎ የሚታወቀው ራፐርም በትዊተር ላይ ባሰፈረው ምላሽ የአዕምሮም ሆነ አካላዊ ጤንነቱን ለሚጠራጠሩት "በደህና ሁኔታ ላይ ነው ያለው" በማለት የድጋፍ ምላሽ ሰጥቷል።

ካንዬም በበኩሉ ከባለቤቱ ምክር በመስማት የሚስማማው ከራሱ ጋር ብቻ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል።