የሆንግ ኮንግን የዘር መድልዎ የሚፋለሙ አፍሪካዊያን እግር ኳስ ተጫዋቾች

አፍሪካዊ ተጫዋቾች Image copyright All Black FC

የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ከየትኛውም ሀገር ወደ ቻይና ካቀኑ ስደተኞች ጋር እግር ኳስ ሲጫወቱ መመልከት እንግዳ ነገር ነው።

ኳስ አብሮ አለመጫወት ብቻ ሳይሆን፣ የዕለት-ተለት እንቅስቃሴያቸውንም ከስደተኞች ራቅ ብለው ማከናወን እንደሚመርጡ ሆንግ ኮንግ ዩኒዝን የተሰኘ የተራድኦ ድርጅት የሰራው ጥናት ያመለክታል።

ከሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ሲሶው፣ ከሌላ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር መቀላቀል አይሹም። በህዝብ ማመላለሻዎች እንኳ አብረው መቀመጥ ጉርብትናም አይፈልጉም።

ልጆቻቸው ከስደተኞች ልጆች ጋር በአንድ ክፍል መማራቸውንም አይፈልጉም።

ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ ይህንን እውነታ ይለውጥ ይሆን? ስደተኞች የሚደርስባቸውን የዘር መድልዎ የመቅረፍ ኃይልስ ይኖረዋል? በሚል መነሻ አንድ የእግር ኳስ ቡድን የተቋቋመው እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ነበር።

''ኦል ብላክ'' የተሰኘው ቡድን አባላት በሙሉ ጥቁሮች ናቸው። አባላቱ በሆን ኮንግ ስለ አፍሪካውያን ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማቃናት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ኳስ ተጫዋቾቹ ከሌሎች ዜጎች ጋር በመቀላቀል የመገለልን ግርግዳ ለማፍረስም እየሞከሩ ነው።

የቡድኑ መስራች መዳርድ ፕሪቫት ኮያ፣ በሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ሳለ ኳስ ተጫዋች ነበር። ቡድኑን ሲመሰርት ኳስ የሚጫወቱት አፍሪካውያን ስደተኞች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን የተለያየ አገር ጥገኝነት ጠያቂዎችና ቻይናውያንም ቡድኑን እየተቀላቀሉ ነው።

"እግር ኳስ ሁላችንንም ያስተሳስረናል። ሀሳብ መለዋወጥ እንዲሁም እርስ በእርስ መደጋገፍ እንችላለን።" ይላል።

ከቡድኑ በሆን ኮንግ መስራት ለማይፈቀድላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች ግዜ ማሳለፍያ መሆኑም ሌላው ጠቀሜታው ነው።

ሆን ኮንግ ውስጥ መስራት ከማይፈቀድላቸው አንዱ የቡድኑ አምበል ዳሪየስ ከቶጎ ከተሰደደ አምስት አመታት ተቆጥረዋል። ሆን ኮንግ ውስጥ መስራት ባይችልም ኳስ መጫወት ለህይወቱ ትርጉም እንደሚሰጠው ይናገራል።

"ለአንድ ወጣት አምስት ዓመታት ያለ ሥራ ማሳለፍ ቀስ በቀስ የመሞት ያህል ነው። ህይወቴ ወዴት እያመራ ነው? የሚል ጥያቄም ያስነሳል። ያለ ምንም ስልጠናና ሥራ ልምድ ማን ይቀጥረኛል?" ሲል ይጠይቃል። ለጥያቄው መልስ የሰጠውና የተስፋ ጭላንጭል ያሳየው የእግር ኳስ ቡድኑን መቀላቀሉ መሆኑንም ያስረዳል።

Image copyright All Black FC
አጭር የምስል መግለጫ የቡድኑ አምበል ዳሪየስ (መሃል ላይ) እና የቡድኑ መስራች ሜዳራ (በቀኝ) ከሌላ ቡድን ተጫዋቾች ጋር ተቀምጠው

"እኔን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር ተቀላቅያለሁ። ሰዎች በችሎታችን ያከብሩናል። እኛም ለምናምንበት ነገር በጋራ እንታገላለን።" ይላል።

ከቡድኑ አባላት የላቀ ችሎታ ያላቸው፣ ኳስ ተጫዋችነታቸውን የመኖርያ ፍቃድ ማመልከቻ ለማስገባትም ይጠቀሙበታል።

"ሰዎች ፎቶ ያነሱናል"

መዳርድ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ቢያበረታታም ቡድኑን ለመቀላቀል የሚያመነቱ አሉ።

ጥቁሮች የሚደርስባቸው መገለል ከዚህም በላይ መሆኑን ለቢቢሲ የሚገልፀው ደግሞ የ26 አመቱ ጋምቢያዊ ሰለሞን ኒያሲ ነው።

ባጠገባቸው ሲያልፍ አፍንጫቸውን የሚይዙ ፎቶ አብረውት ለመነሳት የሚጠይቁትም ገጥመውታል።

ቻይናውያን ከበውት ፎቶ ለማንሳት ሲጠይቁት እንደሚያሳፍረውም ይናገራል።

የሰለሞንን ሀሳብ በመጠኑ የምትጋራው ቻይናዊት የሴት ጓደኛው ልዊዝ ቻን ናት። የ 20 ዓመቷ ልዊዝ ከሰለሞን ጋር ያላትን ግንኙነት ቤተሰቦቿ ቢደግፉትም፣ አሉታዊ አስተያየት የሚሰነዝሩባትም አሉ።

ልዊዝ አፍሪካውያን ወንዶች ብልህና ንቁ እንደሆኑ ታምናለች። በተቃራኒው "የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ስለ ሌላው ማህበረሰብ እውቀት ያንሳቸዋል። አፍሪካውያንን ጥላሸት የሚቀቡ ፅሁፎች ሲልኩልኝ ያሳፍረኛል። " ትላለች።

ዳሪየስ እንደሚለው፣ አፍሪካውያን ላይ ያነጣጠረው የተሳሳተ አመለካከት የእግር ኳስ አጨዋወታቸውንም አስተችቷል። አንዳንድ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ''አፍሪካውያን ኳስ ሲጫወቱ በኃይል ተሞልተው ነው'' የሚል አመለካከት አላቸው።

ዳሪየስ ግን እንደ ቡድን አምበልነቱ ተጫዋቾቹ በተገቢው መንገድ እንዲጫወቱ ያበረታታል።

"የቆዳ ቀለም አይታየኝም"

በሌላ በኩል የጥቁሮች የእግር ኳስ ቡድንን መቀላቀልን እንደ እንግዳ ነገር የማያው የ 34 ዓመቱ ዶንግ ዚ፣ ክለቡን የተቀላቀለው በ 2017 ነበር።

ቡድኑን የተቀላቀለ ሰሞን ከተጫዋቾቹ ጋር ለመግባባት ግዜ እንደወሰደበት ያስታውሳል። ለዚህም ምክንያት ሆኗል የሚለው የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ለአመታት ጥቁሮችን ማግለላቸው ነው።

ከብዙ ጥረት በኋላ የቡድኑን አባላት ጓደኞቹ ከማድረግም አልፎ አብሯቸው ረዘም ያለ ግዜ ማሳለፍ መጀመሩን ይናገራል።

"ለኔ የቆዳ ቀለም አይታየኝም። ሁሉም ምርጥ ኳስ ተጫዋቾች ናቸው።" ሲል ያስረዳል።

Image copyright Biu Chun Rangers

በቅርቡ ለቡድኑ ተሰልፎ የተጫወተው የኮሌጅ እግር ኳስ ተጫዋቹ ኬቨን ፉንግ በበኩሉ፣ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ብርቱ በመሆናቸው የሆን ኮንግ ተወላጆችን ያነሳሳሉ ብሎ ያምናል።

ቢሆንም አብዛኞቹ የሆን ኮንግ ነዋሪዎች በተለያዩ ስራዎች ተጠምደው ኳስ መጫወት ስለሚዘነጉ፣ ጨዋታው በሁለቱ ህዝቦች መሀከል ህብረት ስለመፍጠሩ ይጠራጠራል።

"የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችም ያን ያህል ታዋቂ ስላልሆኑ በኳስ አማካይነት የዘር መድልዎን መቅረፍ ይከብዳል።" ይላል።

ይህን ሃሳብ የ "ኦል ብላክ" አባላትም ይጋራሉ። ዘላቂ ለውጥ ለማምጣትም ከእግር ኳስ ውጪ በተለያዩ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ይሳተፋሉ። አረጋውያንን በመጎብኘት ከህብረተሰቡ ለመቀራረብ የሚያደርጉት ጥረት ይጠቀሳል።

"በእንቅስቃሴያችን አሁን ላንጠቀም እንችላለን። ሆኖም በቀጣዩ ትውልድ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የተሻለ ሁኔታ ይጠብቃቸው ይሆናል።" ሲል ተስፋውን ይገልፃል።

ተያያዥ ርዕሶች