ኤኤንሲ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ውሳኔ 'ዘረኛ' ነው አለ

ካስተር Image copyright Getty Images

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ስፖርት የበላይ አካል የሆነው ፌዴሬሽን (አይኤኤኤፍ) አዲስ ያወጣው ደንብ በደቡብ አፍሪካዊቷ የ800 ሜትር ርቀት የኦሊምፒክ አሸናፊ ካስተር ሴሜኒያ ላይ የተሰነዘረ "ግልፅ ዘረኝነት" ነው ሲል የደቡብ አፍሪካው ገዢ ፓርቲ ኤኤንሲ አወገዘ።

"ይህ አዲስ ደንብ ከሌሎች መካከል ባለፉት ዓመታት ተገቢ ባልሆነ ጫና ስር የቆየችውን ካስተር ሴሜኒያን ኢላማ ያደረገ ነው" ሲል ኤኤንሲ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል።

አዲሱ ደንብ በመጪው ህዳር ወር ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተነግሯል። በዚህም ከፍተኛ ተፈጥሯዊ የቴስቴስትሮን መጠን ያላቸው ሴቶች ከወንዶች ጋር እንዲወዳደሩ ወይም መድሃኒት የማይወስዱ ከሆነ የሚወዳደሩበትን የስፖርት አይነት እንዲቀይሩ ያዛል።

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንደሚያምነው የተወሰደው እርምጃ ከፍተኛ የቴስቴስትሮን መጠን ያላቸው ሴቶች በውድድሮች ላይ የሚይዙትን የበላይነት ለማስቀረት እንደሆነ ገልጿል።

ይህንን ተከትሎም ኤኤንሲ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ፌዴሬሽኑ ያወጣውን አዲስ ሕግ ተቃውሞ ጣልቃ እንዲገባም ተማፅኗል።

"ይህ አዲስ ደንብ በአብዛኛው በምሥራቅ አውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ አህጉሮች የሚገኙትን አትሌቶች ሰብአዊ መብት የሚፃረር ነው" ሲል ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሶ "በውሳኔው የሚንፀባረቀው ዘረኝነት ግን ሊደበቅ አይችልም" ብሏል።

ሴሜኒያ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2009 በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ካሸነፈች በኋላ ፆታዋንና አትሌትክስን በተመለከተ በዓለም ዙሪያ የክርክር ርዕስ ሆናለች።

ሴሜኒያ ቀደም ሲል በአትሌቲክስ ስፖርት ባለስልጣናት የፆታ ምርመራ እንድታደርግ ተጠይቃ የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን እስካሁን ለሕዝብ አልተገለፀም።