ያልተነገረላቸው ትዝታዎችን ከዛኙ -"ቪንቴጅ አዲስ''

የአዲስ አበባ ትዝታ Image copyright vintageaddisababa/instagram

ከ1960ዎቹ መጨረሻ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ የነበረውን የኢትዮጵያን ገጽታ የሰነዱ መዝገቦች ጨለም ያሉ ትዕይንቶች ይበዛባቸዋል፡፡ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር፣ ጅምላ እስር፣ ጅምላ ርሸና እያለ የሚከታተል ትርክት፡፡

መዝጋቢዎች ትልቅ ቦታ በሰጧቸው በእኒህ የታሪክ ጋራዎች የተከለሉ ወርቃማ ቤተሰባዊ ትዝታዎች፣ የፍቅርና መስዋዕትነት ታሪኮች፣ የጓደኝነትና አብሮነት ሁነቶችም ግን ነበሩ፡፡

ለእኒህ ሁነቶች ማስረጃ የሚሆኑ ፎቶዎች በብዙ ኢትዮጵያን እልፍኞች ውስጥ አሉ፡፡ ፎቶዎቹ ወደ አደባባይ እንዲወጡ እና ብዙሃን እንዲነጋገሩባቸው ለማድረግ "ቪንቴጅ አዲስ" - የአዲስ አበባ ትዝታ ድረ-ገጽ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

የአዲስ አበባ ትዝታ -ጽንሰት

"ቪንቴጅ - አዲስ" -የአዲስ አበባ ትዝታ ፡- ዕድሜቸው 30 እና ከዚያ በላይ ያስቆጠሩ፣ በአብዛኛው በጥቁርና ነጭ ቀለም የተነሱ፣ ትናንትን ነጋሪ ፎቶዎች የተከዘኑበት ድረ-ገጽ ነው፡፡

የድረ-ገጹ መስራቾች ናፍቆት ገበየሁ፣ ፊሊፕ ሹትዝ እና ወንጌል አበበ የሚሰኙ ዕድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ እኒህ ወጣቶች ያልኖሩበትን ዘመን የሚያሳዩ ምስሎችን ለመሰብሰብ የተነሳሱት ከጎረቤት ሀገር ተሞክሮ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት በእጃቸው የገባው የፎቶ መጽሃፍ የዐይን ገላጭነት ሚናን ተጫውቷል፡፡

Image copyright Facebook/Instagram
አጭር የምስል መግለጫ የአዲስ አበባ ትዝታ መሥራቾች ከቀኝ ወደግራ ናፍቆት ገበየሁ፣ ፊሊፕ ሹትዝ እና ወንጌል አበበ።

"መጀመሪያ ያየነው "ቪንቴጅ ዩጋንዳ" የሚባል መጽሃፍ ነው፤ በዚያ መጽሃፍ ላይ የቀደመውን ትውልድ የህይወት መልክ ለማሳየት በጥቁርና ነጭ የተነሱ ፎቶዎች ታትመዋል፡፡ እኛም ይሄንን ባየን ጊዜ 'ለምንድነው ይሄን የመሰለ ነገር አዲስ አበባ ላይ የማንሰራው?' ስንል ጠይቅን፣›› ስትል ጅማሮውን የምታስታውሰው ከመስራቾች አንዷ ናፍቆት ገበየሁ፣ 1960ዎቹና 70ዎቹ ከሚታወቁበት የውጥንቅጥ ትዝታ ወዲያ ያሉ መልካም ትዝታዎችን መዘከር ዋነኛ ግባቸው እንደነበረ ታወሳለች፣ ‹‹ያ ችግር በነበረበት ዘመንም ቢሆን ሰዎች ይጋቡ ነበር፣ ይማሩ ነበር፣ ሀገር ይጎበኙ ነበር፣ ጥሩና የደስታ ጊዜ ነበራቸው፤›› ስትል ታክላለች፡፡

ሌላኛው የድረ-ገጹ መስራች ስዊዘርላንዳዊው የንድፍ እና የፎቶ ጥበብ ባለሙያው ፊሊፕ ሹትዝ የናፍቆትን ሀሳብ በሚደግፍ መልኩ ፎቶዎቹ ለሱም ሆነ ለጎብኝዎች ያለፈውን ዘመን ሌላ ገጽታ ለማሳየት ያላቸውን ሃይል ሲገልጽ ‹‹በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የተነሱ ፎቶዎች አሉን፡፡ ሙሽሮችና ሚዜዎቻቸውን፣ ሰዎች ወደ ፎቶ ቤቶች ሄደው የተነሷቸው ዓይነት የሚያሳዩ ዓይነት ፎቶዎች፡፡ሁላችንም በዚያ ወቅት ስለነበረው ቀይ ሽብር ክስተት እናውቃለን፡፡ ቀይሽብር ጫፍ በነካበት በዚያ ወቅትም ቢሆን ሰዎች እየተደሰቱና እየሳቁ የተነሷቸውን ፎቶዎችን ማየት ስለዘመኑ የነበረኝን ዕይታ እንድቀይር የሚያደርግ ነው፣›› ይላል፡፡

ፊሊፕ የተናገረውን የሚደግፈው ፎቶ የዐይናለም እና ገነት ሰርግ በሚል በአራት ክፍል የተተረከው የፍቅር ታሪክ ነው። ያኔ ወጣቶቹ ዐይናለም እና ገነት የተጋቡት ቀይ ሸብር በበረታበት በ1971 ዓ.ም. ነው። ከዚያ በፊት ከ1966-1971 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ገነት እስረኛ ነበረች። ፎቶዎቹ ሁለት የፍቅር ወፎች ያሳለፉትን ፈተና፣ በጭንቅ ዘመንም ቢሆን ያለሙትን ጋብቻ ለማስፈፀም ያሳዩት ቆራጥነት ማሳያ ዐይነት ናቸው።

ጥቁርና ነጭ መልካም ቀናት

‹የአዲስ አበባ ትዝታዎች› ድረ-ገጽ ከ1000 በላይ አዲስ አበቤዎች በአዘቦትና በልዩ ቀናት የተነሷቸው ፎቶዎች በአምድ በአምድ ተከፋፍለው ቀርበውበታል(ከ56 ቤተሰቦች የተገኙ ናቸው) ፡፡ከፎቶዎቹ የበረከቱቱ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የተነሱ ቢሆንም እስከ 1920ዎቹ የሚወርዱ እስከ 1980 መጀመሪያ የሚዘልቁም አሉ፡፡ ከፎቶዎቹ ጀርባ ያሉ ታሪኮችን ጎብኝዎች እንዲረዱ የግርጌ ማስታወሻዎች ተካትተዋል፡፡

የአንዳንዶቹ የግርጌ ማስታወሻ ፈገግታን የሚደቅን፣ መደመምን የሚያጭር ዓይነት ነው፤ ለአብነት እኒህን ይመልከቱ፡፡

ስለወንድምና የአባቱ ሽጉጥ

Image copyright vintageaddisababa/instagram

የዓይናለም እና ገነት ሰርግ

Image copyright vintageaddisababa/instagram

የበቀለች ኪሮሽ

Image copyright vintageaddisababa/instagram

ኢትዮጵያዊያን ጎብኝዎች ከፎቶዎቹ ጋር መንፈሳቸውን ለማዛመድ ቶሎ ይቀናቸዋል፡፡ ሆኖም ለሀገሪቱ እንግዳ ለህዝቡ ባዳ የሆነ ሰውም ቢሆን ፎቶዎቹን አይቶ ከመቼታቸው ጋር ከመቆራኘት የሚድን አይመስልም፡፡ ፊሊፕ ሹትዝ ይሄ የሆነው ከፎቶዎች ቀልብን የሚስብ ምስላዊ ይዘት፤ ትዝታ ቀስቃሽ ተፈጥሮ አንጻር እንደሆነ ይናገራል፡፡

የጥቁር እና ነጭ ፎቶች መናኸሪያ የሆነው የአዲስ አበባ ትዝታ ድረ-ገጽ ከዋናው ገጽ ጎብኝዎች በተጨማሪ ከ44ሺ በላይ የፌስቡክ ተከታዮች ከ2ሺ በላይ የኢንስታግራም ወዳጆች አሉት፡፡ አሰናጆቹ ከዚህ በላይ ጎብኝዎች እንደሚገኙ ተስፋ አላቸው፡፡

ሆኖም ገጹ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የታለፉ መሰናክሎችንም አይዘነጉም፡፡

"የፎቶ ያለህ!"- ደጅ ጥናት

ከአዲስ አበባ ትዝታዎች ገጽ ፊታውራሪዎች አንዷ የሆነችው ወንጌል አበበ፣ ፎቶ ግራፍ ታሪክን አትሞ ለማስቀመጥ ያለውን ሃይል ቀድማ እንደተረዳች ሚያሳብቁ ስራዎችን ከዚህ በፊት አቅርባለች፡፡ ከባልደረባዋ ናፍቆት ገበየሁ ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን መልክዐ ህይወት የሚሳይ የፎቶግራፍ ስብስብ ከዚህ በፊት አቅርበዋል፡፡

የቀደመ ልምድ ቢኖርም ቅሉ "ቪንቴጅ አዲስ አበባ"ን ለማዘጋጀት በሚጥሩበት ወቅት እልህ አስጨራሽ መሰናክሎችን ማለፍ ግድ ሆኖባቸዋል፤" አንዳንድ ሰዎች መጀመሪያ ላይ አያምኑንም፡፡ እነዚህን ፎቶዎች ወስዳችሁ ምን ልታደርጉ ነው? ሲሉ (በጥርጣሬ) ይጠይቃሉ፡፡ (አንዳንዶቹ) ዓላማችንና ዕቅዳችንን ስንነግራቸው በደስታ ሊረዱን ይስማማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፎቶ ሊሰጡን ከተስማሙ በኃላ ስለሚጠፉብን፣ እነሱን ማሳሳብ ግዴታ ይሆንብናል፡፡ በማሳሰብ እና መጨቅጨቅ መካከል ያለውን ስሜት ለማስታረቅ እየሞከርን ስራችንን ቀጥለናል፡፡ ከመሬት ተነስቶ ፎቶ ስጡኝ ብሎ መጠየቅ ከባድ ነው›› ትላለች ወንጌል፡፡

ሰዎችን ከማግባባት በተጨማሪ፣ የተገኙ ፎቶዎችን ወደ ዲጂታል ቀይሮ ለመሰነድ ያለው ሌላ ልፋትም እንደማይዘነጋ አሰናጆቹ ይናገራሉ፡፡

በዚህ ሂደት ያለፉ ፎቶዎች የሰዎች መነጋገሪያ እና መማሪያ ሲሆኑ ማየት የአሰናጆቹ እርካታ ምንጭ እንደሆነ ይታመናል፡፡ አንዳንዴ ራሳቸው 'የአዲስ አበባ ትዝታ' አዘጋጆችን የሚመስጡ፣ ዘመንን በማወዳዳር ጥያቄ እንዲጭሩ የሚያደርጓቸውን ፎቶዎች የሚያገኙባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡

ወንጌል አበበ፣ በደርግ ጊዜ ወደ ሆላንድ ሀገር ተሰደው የኢትዮጵያዊነት ዜግነታቸውን ሳይፈልጉ የቀየሩበትን አፍታ እያነሱ ዛሬም ድረስ በዐይናቸው ዕምባ ስለሚቋጥረው ጋሽ ስማቸው ስለሚባሉ የመርከብ ካፒቴን ስታስብ የተገለጸላትን እውነታ እንዲህ ትገልጸዋለች፣ "ዜግነቴን እንድቀይር ጊዜው አስገደደኝ እያሉ ዕምባ ሲተናነቃቸው ሳይ ገረመኝ፡፡ አሁን ያለው ጊዜ ተገላባጭ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ያለ ወጣት መሄድ ፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያዊነታችን ያለን ኩራት ቀንሷል፡፡ (ጋሽ ስማቸው) እምባ እየተናነቃቸው ይሄንን ሲናገሩ የተማርኩት ይሄንን ነው፡፡"

"የአዲስ አበባ ትዝታ" ራዕይ

በተመሰረተ በሁለት ዓመታት ውስጥ የበርካቶችን ቀልብ የሳበው ድረ-ገጽ መስራቾች፣ ተጨማሪ ወዳጆችን ለማፍራት ዕቅዶችን ሰንቀዋል፡፡ ናፍቆት ገበየሁ የሰበሰቧቸው ፎቶዎች የብዙሃንን ዐይን እንዲያገኙ መላ እየዘየዱ መሆኑን ስታጋራ ‹‹በቀጣይ ዓመት ኅዳር 100 ፎቶዎችን የያዘ መጽሃፍ ለማሳተም አቅደናል፡፡ መጽሃፉ የዚያን ዘመን ሁኔታዎች ሚገልጹ አንቀጾች አብሮ ይይዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት እየዞርን የልምድ ማካፈል ስራ እንሰራለን፣›› ትላለች፡፡

ፊሊፕ በበኩሉ አሁን ትኩረቱን በአዲስ አበባ ላይ ብቻ የሆነው ድረ-ገጽ የሌሎች ከተሞችን ትዝታዎች በሚካትት መልኩ ለማወቃር ስለታሰበ ውጥን አጫውቶን ሆኖም ስራው ጉልበትና ጊዜን የሚወስድ ከመሆኑ አንጻር የበጎ ፈቃደኞችን ትብብር እና የለጋሾችን ተሳትፎም እንደሚፈለግ አልሸሸገም፡፡

"ቪንቴጅ -አዲስ" የትዝታ ጥግ ብቻ አይደለም። ያልታየ ገፅን ገላጭ፣ ከጭንቅ ዘመን ጀርባ ያሉ ብሩህ አፍታዎችን የሚያሳይ ሶስተኛ ዓይንም ጭምር እንጂ። በሁላችንም ቤት ግድግዳ ላይ እነኝህ ብርሃናማ ትዝታዎችን የመዘገቡ ጥቁር እና ነጭ ፎቶዎች እንደሚኖሩ እሙን ነው። ታሪክ እንደ ፎቶዎቹ ሁሉ ጥቁር እና ነጭ ነው። የጠቆሩ ክስተቶችን እንደመመዝገቡ የፈኩ ግለሰባዊ ትዝታዎችንም አትሟል-የኃለኞቹ በተራቸው ለዓይን እንዲበቁ ግን "የቪንቴጅ አዲስ አበባ" ዓይነቶቹ የትዝታ ካዝናዎች በእጅጉ ሳያስፈልጉን አይቀርም።