የሳምንቱ ምርጥ አስራአንድ

የአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኦልድ ትራፎርድ በመጡበት ክሪስታል ፓላስ የአቻምና ባለዋንጫዎቹ ሌይስተሮችን 5 ለምንም በረመረመበት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እነማን በጋርዝ ክሩክስ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ መካተት ቻሉ?. . . አብረን እንመልከት።

ግብ ጠባቂ

ቤን ፎስተር (ዌስትብሮም)

Image copyright Reuters

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዌስትብሮም እያሳየ ያለው ድንቅ ብቃት አንዱ ምንጭ ቤን ፎስተር ወደ ቀደመ ብቃቱ ከመመለሱ ጋር ይያያዛል። የኒውካስሉ ድዋይት ጌይል የሰነዘራት ኳስ እንዴት አድርጎ እንደመከታትና ወደኋላ እንዳሽቀነጠራት እኔ አልገባኝም።

ምስጋና ለቤን ፎስትር ይሁንና ዌስትብሮም በ13 ጨዋታዎች ለሁለተኛ ጊዜ ጎል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ ሆኗል።

ተከላካይ መስመር

ዋርድ እና አንሆልት (ክሪስታል ፓላስ)፣ አዝፕሊክዌታ (ቼልሲ)፣ ዶውሰን (ዌስትብሮም)

Image copyright BBC Sport

ጆዌል ዋርድ ቡድኑ ክሪስታል ፓላስ ከሌይሰተር ጋር በነበረው ፍልሚያ ያሳየው ብቃት የሚገርም ነበር። የጄሚ ቫርዲን ኳስ ለማዳን ያላደረገው ነገር አልነበረም። ለዚህም ነው በሳምንቱ ምርጥ አስራአንድ ውስጥ እንዳካተው ግድ የሆነበኝ። በተመሳሳይም የቡድን አጋሩ ፓትሪክ ቫን አንሆልት ሌይስተሮች ወደ ጎል ክልሉ እንዳይጠጉ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ ሆኗል።

ሴዛር አዝፕሊክዌታ ቼልሲ ውስጥ ያለውን ሚና በማጉላት ድንቅ መሆኑን ማስመስከሩን አሁንም ቀጥሏል። የሚያስጥላቸው ኳሶች እጅግ የሚገርሙ ነበሩ። የወድድር ዓመቱ ለቼልሲ በጎ የሚባል ባይሆንም ቅሉ አዝፕሊክዌታ የነበረው አቋም ግን የማያወላውል ነበር።

የዌስትብሮሙ ክሬግ ዶውሰን በዚህ ሳምንት ምርጥ ተከላካዮች መደብ እንዲካተት የሚያደርገውን ብቃት ማሳየት የቻለበት ሳምንት ነበር።

አማካይ መስመር

ፈርናንዲንሆ (ሲቲ)፣ ኢድሪሳ ጋና (ኤቨርተን)፣ ሩበን ሎፍተስ ቺክ (ክሪስታል ፓላስ)

Image copyright BBC Sport

የማንችስተር ሲቲው ፈርናንዲንሆ የዩናይትዱ ፖል ፖግባ መሆን ያለበትን ሁሉ እየሆነ ያለ ተጫዋች ነው። ምንም እንኳ ባለፈው ጊዜ ፖግባ ሲቲዎችን ጉድ ቢሰራቸውም ዓመቱን ሙሉ ተመሳሳይ አቋም ቢያሳይ ኖሮ ነገሮች የተገላቢጦሽ በሆኑ ኖሮ።

የኤቨርተኑ ኢድሪሳ ጋና በሳምንቱ ምርጥ አስራአንድ ውስጥ መካተት የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጎል ከማስቆጠሩም በላይ ከተከላካይ መስመር በፍጥነት በመውጣት የሚያደርሳቸው ጉዳቶች በጣም የሚያምሩ ነበሩ።

ሩበን ሎፍተስ ቺክ ለክሪስታል ፓላስ እያሳየ ያለውን አቋም የሚዘልቅበት ከሆነ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወደ ሩስያ የዓለም ዋንጫ ሊሄድ እንደሚችል አስባለሁ።

አጥቂ ሥፍራ

ዱሳን ታዲች (ሳውዝሃምፕተን)፣ ስተርሊንግ (ሲቲ)፣ ዛሃ (ክሪስታል ፓላስ)

Image copyright BBC Sport

ከአንድ ዓመት በኋላ የመጀመሪያው የሆነችውን ጎል ያስቆጠረው የሳውዝሃምፕተኑ ዱሳን ታዲች ቅዳሜ እና አሁድ በተደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ከማንኛውም ተጫዋች በበለጠ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችሏል።

ምንም እንኳ የሲቲው ራሂም ስተርሊንግ በዚህ ዓመት 23 ጎሎችን ከመረብ ቢያገናኝም የተገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ቢችል አሁን ላይ 40 ያህል ጎል በስሙ በተመዘገበለት ነበር። ለጎል እንዲሆኑ አመቻችቶ ያቀበላቸው ሶስት ኳሶችም የልጁን ብቃት ደረጃ የሚናገሩ ናቸው።

ዊልፍሬድ ዛሃ ከሌይስተር ጋር በነበረው ጨዋታ አንዳች ኃይል ተላብሶ ነበር። ዛሃ ይህን አቋሙን ይዞ እንዲቀጥል መምከርም እፈልጋለሁ።