ጅቡቲ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ

ጅቡቲ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ Image copyright Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሀገር ውስጥ ጉብኝታቸው በተጨማሪ ወደ ጂቡቲ አምርተው ኢትዮጵያ በወደቡ ላይ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ ፓርላማ ፊት ቀርበውም ንግግር አድርገዋል፤ አልፎም በሁለት ቀናት ጉብኝታቸው ወቅት የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ውህደትን እውን ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

ኢትዯጵያ ለአስርታት በተጠቀመበች የጂቡቲ ወደብ በየዓመቱ 1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ እንደምታፈስ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሻምቦ ፊታሞ ይናገራሉ።

ይህም 70 በመቶ የጂቡቲ በጀት ያክል እንደሆነ ነው ጨምረው የሚያስረዱት። ኢትዮጵያስ ለወደብ ስምምነቱ በምላሹ ምን ይዛ ትቀርባለች? እንዲሁም የስምምነቱ ዝርዝር ምን ይሆን የሚሉት በበርካቶች ዘንድ የሚመላለሱ ጥያቄዎች ናቸው።

ሀገራቱ በጋራ የሚያስተዳድሩት ወደብ ለማልማት በሐሳብ ደረጃ መስማማታቸው መነገሩ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት አስፈላጊነት ከፍ እንደሚያደርገው እየተነገረ ይገኛል።

"የሁለቱ ሀገራት ስምምነትን ዝርዝር አፈፃፀም ለማየት በሁለቱ ሀገራት ሚኒስትሮች የሚመራ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የወደቡ ድርሻ ምን ያህል ይሆናል የሚለውን በቀጣይ የሚሰራ ነው" ይላሉ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ።

ኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት እየተጠቀመችበት ላለው የጂቡቲ ወደብ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ እንደምታፈስ አምባሳደሩ ይናገራሉ።

እንደ አምባሳደሩ አገላለፅ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በነባር ወደቦችም ይሁን ወደፊት በሚሰሩ ወደቦች ድርሻ እንዲኖራት የሚያደርግ ነው። ይህም ማለት ወደቦቹን በጋራ የማልማት ዕድል ኢትዮጵያ ታገኛለች።

አምባሳደሩ "ኢትዮጵያ ወደቦቹን በጋራ የማልማት እድል ስታገኝ የወደቡን አገልግሎት አሰጣጥ እና ለምጣኔ ሃብት እመርታ ቅልጥፍና ሊሰጥ የሚችል የወደብ አገልግሎት እንዲኖር አብራ የማስተካከል፤ ችግሮች ካሉም አብሮ የማረም ስራ መስራት ያስችላታል" ባይ ናቸው።

"ይህ የወደብ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚኖረውን የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያሳይ እና በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት የፖሊሲዎች የማጣጣም ስራም ይሰራል" ሲሉ ይገልፃሉ አምባሳደሩ።

ይህ የወደብ ስምምነት ለሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ውህደቱ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም ሃሳባቸውን ያስረግጣሉ።

"ጅቡቲም ሆነ ኢትዮጵያ የጋራ ኢኮኖሚ ውህደት ቀይሰው ብዙ ፕሮጀክቶችን ያካሄዱ ሃገራት ናቸው ኢትዮጵያ በኢትዮ ጅቡቲ ኮሪደር ላይ የ12 ቢሊየን ዶላር ወጪ በማውጣት ባቡርን ጨምሮ የተለያዩ የማስፋፊያ ግንባታዎች እና አዳዲስ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን አካሂዳለች።"

አሁንም ጅቡቲ በኢትዮጵያ እንደ ቴሌኮም ዘርፍ ያሉ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችላቸው የግብርና ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ ስምምነት ላይ መደረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ይህም የሆነው ኢትዮጵያ የፖሊሲ ለውጥ አድርጋ ለውጭ ባለሃብቶች የቴሌ ኮም ዘርፉን ከፍታ ሳይሆን አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና ትስስሩን ለመፍጠር ታልሞ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ለጅቡቲ መንግሥት የኤሌክትሪክ ሐይል፣ ለእርሻ የሚሆን ሰፊ ሄክታር መሬት፣ ለመጠጥ ውሃ የሚሆን የከርሰምድር ውሃ ያለበት ቦታ መስጠቷ ይታወሳል።