እንግሊዝ፦ 'ከኢራን ጎን ነኝ'

ቴሬዛ ሜይ Image copyright Christopher Furlong

እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን የአቶሚክ መሳሪያዎችን እያመረተች ነው ብለው ቢከሱም፤ እንግሊዝ ከኢራን ጋረ የተደረሰውን በጣም ወሳኙን የኒውክሌር ስምምነት ደግፋለች።

እስራኤል ኢራን የአቶሚክ መሳሪያዎችን በድብቅ እያመረተች እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ አለኝ ብትልም ኢራን ግን ጉዳዩን አልተቀበለችውም።

አሜሪካ በበኩሏ 'የእስራኤል የመረጃ ምንጭ ታማኝና ቀጥተኛ ነው' ስትል ደግፋታለች።

በ2015 ነበር ኢራን የኒውክሌር ማምረት ተግባሯን ለማቆምና ስድስት ሃገራት ደግሞ ተጥሎባት የነበረውን ማእቀብ ለማንሳት የተፈራረሙት።

የእንግሊዝ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑ ግለሰብ "በስምምነቱ መሠረት የተመደቡት መርማሪዎች ያለ ማንም ተጽዕኖ ኢራን ስምምነቱን እንዳላፈረሰች እና በጣም ወሳኝ የሆኑ ሌሎች መረጃዎችን እያቀረቡ እንደሆነ አስረድተውናል" ሲሉ ይናገራሉ።

ሰኞ ዕለት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን ሚስጥራዊ የኒውክሌር ማምረት ሂደት የሚያሳይ ያሉትን መረጃ ይፋ አድርገው ነበር።

"በእስራኤል የተገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ኢራን የኒውክሌር ማምረቻ የለኝም በማለት ዓለምን እንደሸወደች ነው" ሲሉ ያክላሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር።

ኢራን በበኩሏ፤ የእስራኤልን ውንጀላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግንቦት አጋማሽ ሃገራቸው በስምነቱ ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚለውን ውሳኔያቸውን ላይ ጫና ለማደረግ የተቀነባበረ የህጻን ጨዋታ ነው ስትል ኣጣጥላዋለች።

ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ስምምነቱን የፈረሙት የአውሮፓ ሃገራት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈቱት ካለሆነ ግን አሜሪካ ከኢራን ላይ ተነስቶ የነበረውን ማእቀብ ለማራዘም እንደምትቸገር ገልጸዋል።

ዋይት ሃውስ በለቀቀው መግለጫ እንዳለው ስለ ኢራን ኒውክሌር ማምረት በእስራኤል የቀረበው መረጃ አዲስ እና ኣሳማኝ ነው።

መግለጫው ሲያክልም ሰነዶቹ አሜሪካ ከሰነደችው መረጃ ጋር የሚመሳሰል እና ቀጥተኛ ሲሆን ኢራን ከዜጎቿ እና ከመላው ዓለም ልትደብቀው እየሞከረች ያለውን ሚስጥር ያጋለጠ ነው ብሏል።