"የክልሉን መንግሥት በእግዚአብሔር ስም ጠይቁልን..."

ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች

ወርሃ ጥቅምት ላይ ቤኒሻንጉል ከሚገኘው ካማሼ ዞን የነበሩ ዜጎች በሥፍራው በተነሳ ግጭት ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ዘግበን ነበር።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ እኒህ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በጊዜያዊነት የባህርዳር የምግብ ዋስትና ግቢ መጋዘን ውስጥ እንደተጠለሉ ባልደረባችን በሥፍራው ተገኝቶ መዘገቡም ይታወሳል።

አሁን ደግሞ በጊዜያዊነት ከተጠለሉበት መጋዘን መባረራቸውን ነው ቢቢሲ መረዳት የቻለው።

የተፈናቃዮቹ ተወካይ የሆኑት አቶ አበባው ጌትነት ከ150 ሰዎች በላይ መጠለያ አጥተው እየተንከራተቱ እንደሆነ ነግረውናል። ከዚህም በተጨማሪ ስምንት ሰዎች ለሰዓታት ያክል ለእሥር ከተዳረጉ በኋላ እንደተፉም ለቢቢሲ አሳውቀዋል።

"በመጀመሪየ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነበር የቆየነው፤ ከዚያ የአካባቢው ህብረተሰብ ተሰባስቦ ምሳ አበላን። በመቀጠልም ጉዟችንን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደረግን። ወደዛ የሄድንበት ዋነኛው አላማችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ዋና አስተዳዳሪ ጳጳስ ማግኘትና የክልሉን መንግስት በእግዚአብሄር ስም እንዲጠይቁልን ለማድረግ ነበር።"

"ጳጳሱም ሰላማዊ ሆነን እንድንንቀሳቀስ እና ምንም ዓይነት ወንጀል ውስጥ እስካልገባን ድረስ፤ የሚመለከተውን አካል በማነጋገር መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተውልናል" ሲሉ ተወካዩ ነግረውናል።

"እዛውም ቆይተን ምሳ እና እራታችንን በልተን፤ አዳራችንን በቤተክርስቲያኒቱ እንዲሆን ትእዛዝ ሰጥተው ሄዱ" በማለት አሁን ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ተፈናቃዮቹ ችግሮቻቸውን ይዘው ዘላቂ መፍትሄ ይበጅላቸው ዘንድ ለክልሉ አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፤ ከክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተቀምጠው መወያየታቸውንም ያስረዳሉ።

ነገር ግን ክልሉ ያቀረበላቸው ሁለት አማራጮች ፤ ወደተፈናቀሉበት ካማሼ ዞን መመለስ ወይንም ቀድሞ ትተዋቸው በሄዷቸው የትውልድ ቀየዎቻቸው ዳግመኛ መስፈር፤ ያስደሰቷቸው አይመስልም።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የአማራ ክልል ሕዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን እንዲሁም የክልሉን ባለሥልጣናት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ተያያዥ ርዕሶች