ወደ ድብቁ የዋትስአፕ መንደር ስንዘልቅ

ወደ ድብቁ የዋትስአፕ መንደር ስንዘልቅ Image copyright AFP

ጋዜጠኛ ጆሴፍ ዋሩንጉ ብዙ አባላት ያላቸው የዋትስአፕ ቡድኖች አስተዳዳሪዎች ትክክለኛ ማንነታቸው ምን እንደሚመስል ያስቃኘናል።

በቅርቡ ኬንያ ውስጥ በምትገኘው የትውልድ አካባቢዬ የልማት ሥራዎችን ለማስተባበር ተብሎ የተመሠረተ የዋትስአፕ ቡድን አስተዳዳሪ እንድሆን ተመረጥኩ ይላል ጆሴፍ።

ወዲያው አባላትን ከቡደኑ ማስወጣትና ማስገባት ቀላል ሥራ ሆነልኝ የሚለው ጆሴፍ፤ የቡድኑን እንቅስቃሴ በመከታተልና በመቆጣጠር ብቻ ብዙ እንቅልፍ አልባ ምሽቶችን ማሳለፍ ጀመረ።

"ስልጣን እንደዚህ እንደሚጣፍጥ አላውቅም ነበር፤ የመረጃ ሚኒስትር መሆን እንደዚህ ነው ማለት ነው?'' ይላል ጆሴፍ።

ዋትስአፕ ተግባቦታችንን እና ማህበራዊ ግንኙነታችንን በአስገራሚ ሁኔታ ቀይሮታል። ጥሩ የዜና ምንጭ ነው። የመጥፎውም፣ የጥሩውም እንዲሁም የውሸቱ። የብዙ ሰዎችን ግንኙነትም አበላሽቷል።

እኔ አባል በሆንኩበት አንድ የጋዜጠኞች የዋትስአፕ ቡድን ውስጥ የማንኛውንም ኬንያዊ ስልክ ማግኘት ሰከንዶችን ብቻ ነው የሚፈጀው።

የተለያዩ የንግድ ፈጠራ ሃሳቦችን ከሚያንሸራሽሩት እስከ ፖለቲካ፤ ቀልድ እና ኃይማኖት የማይፈቀድባቸው ቡድኖች በናይሮቢ የሚስተዋሉ የዋትስአፕ እቅስቃሴዎች ናቸው።

'ዋትስአፕ ሕይወትን ለማዳን'

በቅርቡ አንድ ኬንያዊ ጓደኛዬ ለአስቸኳይ ሕክምና ወደ ሕንድ ለመጓዝ በቂ ገንዘብ ስላልነበረው፤ በዋትስአፕ በተደረገለት ዘመቻ፤ በሁለት ቀን ውስጥ ብቻ 20ሺህ ዶላር ማሰባሰብ ችሎ ነበር።

አንድ በጋና የሚገኝ ጓደኛዬ እንደነገረኝ ከሆነ፤ እሱ አባል የሆነበት ብዙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚገኙበት የዋትስአፕ ቡድን ውስጥ አንዱ አባል እራሱን ሊያጠፋ እንደሆነ የሚገልጽ ረዥም መልዕክት ጽፎ ነበር።

የቡድኑ አባላትም በፍጥነት በመሰባሰብ የእርዳታ እጃቸውን ለዚህ ወጣት ለመዘርጋት ይጣደፋሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ እርዳታው ሳይደርስለት በፊት እራሱን አጠፋ።

ይህ ቡድንም ለሞተው አባል ማስታወሻ እንዲሆን የቡድኑን ተልዕኮ ወደ ግንዘቤ ማስጨበጥ ለውጠው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

ከእራሴ እና ከሌሎች ልምድ በመነሳት ስድስት ዓይነት የተለያዩ የዋትስአፕ ቡድን አስተዳዳሪዎችን መለየት ችያለሁ ይላል ጆሴፍ።

1: አምባገነኖቹ

እነዚህ ስልጣን የተጠሙ ናቸው። ማንም አልመረጣቸውም ግን ሁሉም አባል ይፈራቸዋል።

ቡድኑን እንደራሳቸው የግል ንብረት ነው የሚቆጣጠሩት። ከእነሱ ፍላጎት ጋር የማይስማማ ማንኛውም ዓይነት ሃሳብ ከፍተኛ ትችትና ውግዘት ይደርስበታል።

ማንም ሰው ቡድኑን እንዳይለቅ ያደርጋሉ። በእራሱ ቢለቅ እንኳን መልሰው ያስገቡታል። የቁም እስር እንደማለት ነው።

2: አስተጋቢዎቹ

እነዚህ ደግሞ የእራሳቸውን ድምፅ ማስተጋባት የሚወዱት አስተዳዳሪዎች ናቸው። እንደዚህ ዓይነት አስተዳዳሪዎች ያለባቸው ቡደኖች ብዙ አባላት የሏቸውም።

ሌላኛው እኔ አባል የሆንኩበት የዋትስአፕ ቡድን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ነው። ብዙዎቹ አባላትም ቡድኑን ለቀው ወጥተዋል።

ግን ሁሌም ቢሆን የቡድኑ አስተዳዳሪ እንደምን አደራቸችሁ አባላት እያለ መልዕክት ያስቀምጣል። ማንም አባል ግን መልስ አይሰጥም።

3: የማፍያ መሪዎች

እነዚህን እንኳን እንደ አስተዳዳሪ ለመውሰድ ይከብዳል። ግን ከመሥራቾቹ በስተጀርባ ሆነው ብዙ ነገር ይቆጣጠራሉ።

በቡድኑ ውስጥ ግንኙነቶች ምን መምሰል እንዳለባቸው ሕግ እና ደንብ ያወጣሉ። ማን አባል መሆን አለበት ማንስ መሆን የለበትም የሚለውን ውሳኔ ይሰጣሉ።

የእነርሱ ፍላጎት ሲነካ ሁሌም ቢሆን ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ።

Image copyright AFP

4: የአማፂያን መሪዎች

እነዚህ መሪዎች አስተዳዳሪ መሆናቸውን የረሱ ዓይነት ናቸው። ሁሌም አስደንጋጭ እና አነጋገሪ ምስሎችን ለቡድኑ ለማጋራት የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

ብዙም ተሳትፎ የማያደርጉ አባላት ላይ ሁሌም አመፅ የሚያስነሱ እንዲሁም የቡድኑ ዋልታ እና ማገር መሆን የሚፈልጉ ናቸው።

5: ሁሉንም አስደሳቾች

የአምባገነኖቹ ተቃራኒ ናቸው። ሁሉንም ያበረታታሉ።

በቡድኑ አስተዳዳሪነት ኃላፊነታቸው ውስጥ ነገሮችን ችላ በማለት ማሳለፍ ይመርጣሉ።

ስለዚህ ብዙ ጊዜ ቡድኑ የተረባበሸ እና ሕጎች የማይከበሩበት እንዲሁም ማንም ሕጎቹን ለማስከብር የማይንቀሳቀስበት ነው።

6: ሥነ-ጽሑፍ አስተማሪዎቹ

እነዚህ ደግሞ ያለቦታቸው የተቀመጡ አስተማሪዎች ናቸው። ማንኛውንም የሥነ- ጽሑፍ ስህተት መለየት እና መሳለቅ ይወዳሉ።

እንደዚህ ዓይነት የሥነ-ጽሑፍ ስህተት የሚሠሩ የቡድኑ አባላትን እንደ አዲስ ሊያስተምሯቸው ይሞክራሉ።

ለቡድኑ አይመጥኑም ተብለው የሚታሰቡ ሃሳቦችም በእነዚህ አስተዳዳሪዎች ተሽቀንጥረው ይጣላሉ።