ኮዴይን፦ ገዳዩ 'ሽሮፕ'

ኮዴይን፦ ገዳዩ 'ሽሮፕ'

በሰሜን ናይጄሪያ በምትገኘው ካኖ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ በቡድን ቡድን የሆኑ ወጣቶች፤ ቡናማ የመድሃኒት ብልቃጥ ጨብጠው ወፍራም ጣፋጭ ፈሳሽ እየተጎነጩ ነው።

ወጣቶቹ የሚጠጡት ለሳል ተብሎ የሚሰጠውን በተለምዶ 'ሽሮፕ' ተብሎ የሚጠራውን (የsyrup እና codeine ንጥረ ነገሮች ቅይጥ ) ፈሳሽ ነው።

ጣፋጩን የእንጆሪ ጣዕም ያለውን መድሃኒት የሚጠጡ ወጣቶች ይሰክሩና እንዲናውዛሉ።

ይሄ ትዕይንት በአስጨናቂ ሁኔታ በመላዋ ናይጄሪያ የተንሰራፋ ነው። የዚህ ኃይለኛ መድሃኒት ሱሰኞች ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ እጅጉን ከፍ ብሏል።

እንደ ናይጄሪያ መንግሥት ቆጠራ በሰሜን ናይጄሪያ ሁለት ክልሎች ብቻ 3 ሚሊዮን ብልቃጥ ሽሮፕ በየቀኑ ይጠጣል። ውጤቱም እጅግ አሳዛኝ ነው።

በመንግሥት በሚተዳደረው የሱስ የማገገሚያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሶሰኞች ሌላ ሰው ያጠቃሉ በሚል ፍርሃት ከመሬት ጋር በሰንሰለት ተጠፍረዋል ይታያሉ።

"ይሄ ጉዳይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሁሉንም ሰው እየለከፈ ነው" የሚለው ሳኒ ችግሩ ከአንደኛው ቤት ወደ አንደኛው እየተዛመተ መሆኑን ይናገራል። የኮዲን ሽሮፕን ከሚገባው መጠን በላይ መውሰድ አንጎል ላይ ጫና ይፈጥራል ወደ እብደትም ይወስዳል።

በማገገሚያ ማዕከሉ ካሉት ታካሚዎች መካከል የ16 ዓመቷ ወጣት ለዕድሜ አቻዎቿ ስለ ችግሩ ግልፅ መልዕክት አላት።"እውነት ለመናገር እስከአሁን አልሄዱ እንደሁ ወደ ሱሰኝነቱ እንዳይሄዱ እመክራቸዋለሁ። ህይወታቸውን ያበላሸዋልና" ትላለች።

በየሳምንቱ ህገ-ወጥ የኮዴን ሽሮፕ ቅይጥን ለመያዝ እንደሚሰማራው በካኖ የሚገኘው ብሄራዊ የመድሃኒት ህግ አስፈፃሚ አጄንሲ ዕምነት ከሆነ፤ በጎዳናዎቹ ላይ ከተንሰራፋው ቅይጥ ለመያዝ የቻሉት አንድ አስረኛውን ብቻ ነው።

"እነዚህ መድሃኒቶች ከጨረቃ የመጡ አይደሉም። ከባህርም የወጡ አይደሉም። የሆነ ቦታ ተመርተው፣ ከአንድ ስፍራ ወደ አንድ ስፍራ የሚጓጓዙ ናቸው። ለማወቅ አንፈልግም እያልን ነው" በማላት የናይጄሪያ መንግሥት አስፈላጊውን ቁጥጥር እንዳላደረገ የሚናገሩት ደግም የህክምና ባለሙያዋ ዶክተር ማይሮ ማንዳራ ናቸው።

የቢቢሲ የአፍሪቃ ዐይን ልዩ የ5 ወራት ህቡዕ ምርመራ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሯል። የምርመራ ጋዜጠኞቹ እራሳቸውን የሳል ሽሮፑን ካለ ህጋዊ የማዘዣ ወረቀት እንደሚገዛ የንግድ ሰው በማቅረብ፤ ህገ-ወጡን የሽሮፕ ቅይጥ የሽያጭ ስምምነትን ምስል ለመቅረፅ ችለዋል።

ለአብነትም በኢሎሪን ናይጀሪያ ዋነኛ የሳል ሽሮፕ አምራች ከሆኑት መካካል አንዱ የሆነው የባዮራጅ ፋብሪካ ይጠቀሳል። የሽያጭ ተወካይ የሆኑት አልመንሰሩ እንዲሁም የመጋዘን አስተዳዳሪው ባባ አይቢጄ ለህቡዕ የምርመራ ቡድኑ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የኮዴን ምርትንና ሌላ ውህድን ለመሸጥ ፈቅደዋል።

ባባ ኢቢጂ እንደሚለው ህፃናት ሱስ የሚሆነውን የኦፒዮድ ቅይጥን አንዴ ከቀመሱ ተጨማሪ ለማግኘት ተመልሰው ይመጣሉ። ባዮራጅ ፋብሪካ ባዮሊን የተባለውን ፈሳሽ ከኮዴን ጋር እንደማይሸጥ አል መንሱሩም ከሁለት ዓመት ነፊት ፋብሪካው እንደለቀቁ ተናግረዋል።

ባባ ኢቢጂም ሆነ አልመንሱሩ ጥፋት መፈፀማቸውን ክደዋል። እኒህ ግለሰቦች መሰል ንግድ ለመስራት ነፃ ቢሆኑም በዚህ ውጥንቅጥ በእጅጉ የተጎዱት የናይጄሪያ ወጣቶች ናቸው።

ቢቢሲ ይህን መርማሪ ዘገባ ከሰራ በኋላ የናይጄሪያ መንግሥት ይህ ገዳይ እና ሱስ አስያዥ መድሃኒት በሃገሪቱ እንዳይሸጥ ማዘዙ ተሰምቷል።