ስዕልን በኮምፒውተር

ከብሩሽና ሸራ ወደ ኮምፒውተር ስክሪን Image copyright Dagim Worku

ወይንሸት ጎሹ የአራተኛ ዓመት የኪነ-ህንፃ ተማሪ ናት። "ኦርዲነሪ ቢውቲ" የተሰኘው የዲጂታል ሥነ-ጥበብ ሥራዋ በየዕለቱ የሚታዩ ነገር ግን ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸው መስተጋብሮችን እንደሚያንፀባርቅ ትናገራለች።

ወይንሸት ሥራዎቿን ፌስቡክና ቴሌግራምን በመሰሉ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ትለጠፋለች። እንደሷው የዲጂታል ሥነ-ጥበብ ሙያተኞችና ጓደኞቿ የሥራዎቿ ተመልካቾች ናቸው።

በኮምፒውተር ሶፍትዌሮች በመታገዘ የሥነ-ጥበብ ሥራዎችን መፍጠር (ዲጂታል አርት)፣ በተቀረው ዓለም ታዋቂ ቢሆንም እንደ ወይንሸት ያሉ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ገና እውቅና አላገኙም።

ወይንሸት፤ "ኦርዲነሪ ቢውቲ" የተሰኘውን ሥራዋን ከማህበራዊ ድረ-ገፅ ባሻገር በሥነ-ጥበብ ዐውደ ርዕይ ለመጀመርያ ግዜ የማሳየት እድል ያገኘችው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ዲጂታል ሥነ-ጥበብ ብዙም አለመታወቁና እንደ ሥነ-ጥበብ ዘርፍ አለመወሰዱ፤ የዲጂታል ሥነ-ጥበብ ዐውደ ርዕይ እንዳይዘጋጅ ምክንያት ነበር።

ይህንን እውነታ ለመቀየር ዳግም ወርቁ፣ ነስረዲን መሀመድና ወንዱ ጉዲሳ "የሃ" የተሰኘ የዲጂታል ሥነ-ጥበብ ዐውደ ርዕይ ማሰናዳተቸውን ይናገራሉ።

በአውደ ርዕዩ ሥራቸውን የሚያሳዩ ወጣቶች ለማግኘትም ማህበራዊ ድረ-ገፆችን ማሰስ ነበረባቸው። በኢንስታግራም ወይም በፌስቡክ ሥራዎቻቸውን ለተመልካች ከሚያደርሱ ወጣቶች መካከል ስድስቱን መረጡ።

Image copyright Dagim Worku

ወይንሸት ከአርቲስቶቹ አንዷ ስትሆን፣ ቤተልሔም ሞላ፣ ኤርምያስ አሰፋ፣ ፋኑኤል ልዑል፣ ኦማር ያሲን፣ ተካ ሀይሌና ዮሐንስ ባልቻም ተካተዋል።

በቦስተን ደይ ስፓ የተከፈተው ዐውደ ርዕይ፤ ዲጂታል ሥነ-ጥበበኞችና ማህበረሰቡን ለማቀራረብ ታስቦ መዘጋጀቱን የሲቪል ኢንጅነሪንግ ምሩቁ ዳግም ይናገራል።

"በኮምፒውተር በመታገዝ የሚሰራው ዲጂታል ሥነ-ጥበብ ለኢትዮጵያ አዲስ ነው። ወጣቶች በየቤታቸው ሰርተው በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ያቀርባሉ" ይላል።

ወጣቶቹ አዶቤ ፎቶሾፕና ኢሉስትሬተር የተሰኙ መተግበሪያዎችን ተጠቅመው ስዕሎች ይሰራሉ። ሆኖም ከማህበራዊ ድረ-ገፅ የዘለለ መድረክ እንደሌላቸው ነስረዲን ያስረዳል።

ዲጂታል ሥነ-ጥበበኛው ነስረዲን "በፌስቡክ ጠንካራ የዲጂታል ሥነ-ጥበብ ባህል ቢኖርም፣ አደባባይ አልወጣምና ዐውደ ርዕዩን በየጊዜው ደጋግሞ ማዘጋጀት ያስፈልጋል" ይላል።

ያሰባሰቧቸው አርቲስቶች የኪነ-ህንፃ፣ የኢንዱስትሪያል ዲዛይንና ሥነ-ጥበብ መነሻ ያላቸው ናቸው።

"በብዙሀኑ ዘንድ እንደ ሥነ-ጥበብ ተቀባይነት ያለው በእርሳስና ወረቀት ወይም በብሩሽና ሸራ የተሰራ ስዕል ነወ። ይህን የማህበረሰቡን ምልከታ መለወጥ እንፈልጋለን" ሲል ነስረዲን ይናገራል።

Image copyright Dagim Worku

በአውደ ርዕዩ ከቀረቡ ሥራዎቹ መሀከል በቀለም ማከል (ከለራይዚንግ) የተዘጋጁት ይጠቀሳሉ። በንጉሡ ዘመን የተነሱ ጥቁርና ነጭ ፎቶዎችን በኮምፒውተር ቀለም ጨምሮ የማቅረብ ጥበብ ነው። የሦስት አውታር (ስሪዲ) ሥራዎችም ተካተዋል።

"ዲጂታል ሥነ-ጥበብ ቦታ እንዲሰጠውና እንደ ጥበብ እንዲቆጠር እንፈልጋለን" በማለት ነስረዲን ይጠይቃል።

ወይንሸት እንደምትለው ጥበብ በኮምፒውተር ሲታገዘ የፈጠራና ጥበባዊ ዋጋው የሚወርድ የሚመስላቸው አሉ።

"አብዛኛው ሰው ሥራውን ኮምፒውተር የሚሰራው ይመስለዋል። ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ ሙሉ ሥራው የአርቲስቱ ድርሻ ስለሆነ እንደሌላው ጥበብ ነው" ትላለች።

ዐውደ ርዕዩ ግንዛቤ ፈጥሮ የጥበቡን ተዳራሽነት እንደሚያሰፋውም ተስፋ ታደርጋለች።