የህንድ ፍርድ ቤት መንግሥት ለታጅ መሃል ጥበቃ እንዲያደርግ አዘዘ

ታጅ መሃል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ታጅ መሃል

የህንዱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአሳሳቢ ሁኔታ ቀለሙን እየቀየረ የመጣውን የታጅ ማሃል ቤተ-መንግሥት ለመታደግ መንግሥት የውጪ ሃገራትን እርዳታ እንዲጠይቅ አዘዘ።

"ይህን ችግር ለመፍታት ብቃቱ ቢኖራችሁም በአግባቡ እየተጠቀማችሁት አይደለም። ወይም ግድ አይሰጣችሁም'' ብለዋል የፍርድ ቤቱ ዳኞች።

እንደ ፍርድ ቤቱ ከሆነ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ከነጭ ኖራ እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች የተሰራው ታዋቂው ቅርስ ቀለሙ ወደ ቢጫ የተለወጠ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ አረንጓዴ እየተቀየረ ነው።

የአየር ብክለት፣ የተለያዩ ግንባታዎች እንዲሁም ነፍሳት ለቤተ-መንግሥቱ ቀለም መቀየር እንደ ዋነኛ ምክንያት ተቀምጠዋል።

ማዳን ሎኩር እና ዲፓክ ጉፕታ የተባሉ የፍርድ ቤቱ ዳኞች፤ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ያቀረቡላቸውን ችግሩን የሚያሳዩ ምስሎች ከተመለከቱ በኋላ የህንድ መንግሥት ከሃገር ቤትም ሆነ ከውጪ ሃገራት እርዳታ እንዲጠይቅ አዘዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህንድ መንግሥት በታጅ ማሃል ቤት-መንግሥት አካባቢ የሚገኙ ፋብሪካዎችን እየዘጋ ያለ ቢሆንም የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ግን አሁንም የኖራው ግንብ ውበቱን እያጣ ነው ብለዋል።

በቤተ-መንግሥቱ አካባቢ ከሚገኘው ያሙና ወንዝ የሚወጣው ፍሳሽ እንዲሁም የተለያዩ ነፍሳት አይነ ምድር በከፍተኛ ሁኔታ የታጅ ማሃል ቤተ-መንግሥት ግድግዳዎችን እያበላሹት ይገኛሉ።

በሙጋሉ ንጉሥ ሻህ ጃሃን በአግራ ከተማ የተገነባው ይህ ቤተ-መንግሥት በቀን እስከ 70 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን፤ በዓለማችን ብዙ ጎብኚዎችን ከሚስቡ አስደናቂ ቦታዎች አንዱ ነው።

ቤተ-መንግሥቱን በኖራ ማደስ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን፤ በቅርቡ መስከረም ወር ላይም ይህ ሥራ ተከናውኗል።

ባለሙያዎቹ ኖራውን በግድግዳው ላይ በመለጠፍ ቆሻሻውን ይዞ እንዲነሳ ያድርጋሉ። ይህ ዘዴም ከፍሳሽ ጋር አብረው የሚመጡትን ቆሻሻዎች እና የነፍሳቱን አይነ ምድር ከግድግዳው ላይ ለማጽዳት ይጠቅማል።

ይህ ሥራ እስከ ያዝነው ዓመት መጨረሻ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት ለግንቦት ወር ቀጠሮ ይዟል።