ሰሜን ኮሪያ ውስጥ የታሰሩት ሶስቱ አሜሪካውያን

ደቡብ ኮርያ ወደ ፒዮንግያንግ ሆቴል ያዘዋወረቻቸው አሜርካውያን እስረኞች እነማን ናቸው? Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ከታሳሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ኪም የአስር ዓመት እስር ሲፈርደበት እንባውን መቆጣጠር አልቻለም ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶንልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ-ኡን ይገናኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት፣ ሰሜን ኮሪያ ለአሜርካ መለሳለሷን የሚጠቁም ተግባር ፈፅማለች።

በሰሜን ኮሪያ ከአምና አንስቶ የታሰሩ ሶስት አሜርካውያን ፒዮንግያንግ ወደሚገኝ ሆቴል ተዘዋውረው፣ በአግባቡ እየተመገቡ እንዲሁም የህክምና ክትትልም እያገኙ መሆኑ ተዘግቧል።

ፕሬዘዳንት ትራምፕ አዘውትረው መረጃ በሚያሰራጩበት የትዊተር ገፃቸው፣ እስረኞቹን ለማስፈታት ጥንቃቄ የተሞላው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፣ "ቀጥሎ የሚከሰተውን ተጠባበቁ" ሲሉ ለተከታዮቻቸው ተስፋ ሰጥተዋል።

ከሶስቱ አሜሪካውያኑ ሁለቱ የታሰሩት ትራምፕ ስልጣን በተቆናጠጡበት ዓመት ነበር።

ሆኖም ፕሬዘዳንቱ እስረኞቹ እስከ አሁን አለመፈታታቸውን በቀደመው የኦባማ አመራር አላከዋል። "እንደሚታወቀው ባለፈው አስተዳደር ታጋቾቹን ለማስፈታት ጥረት ቢደረግም ፍሬያማ አልሆነም" በማለት።

እስረኞቹ ወደ ሆቴል የመዛወራቸው ዜና ምንጭ ሰሜን ኮሪያዊው የመብት ተሟጋች ቾይ ሱንግ ርዮንግ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ክፍል ዝውውሩ እውን መሆኑን ማረጋገጥ እንደማይችል አሳውቋል።

ቢሆንም ቃል አቀባዩ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ የታገቱ ዜጎቿን ለማስመለስ እየሞከረች መሆኑን መጠቆማቸው አይዘነጋም።

ለመሆኑ እስረኞች እነማን ናቸው?

የእርሻ መምህሩ ኪም

ኪም ሀክ-ሶንግ በፒዮንግያንግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርስቲ (ፒዩኤስቲ) ሰራተኛ የነበረ ሲሆን፣ እ.አ.አ ግንቦት 6፣ 2017 በቁጥጥር ስር የዋለው "አደገኛ እንቅስቃሴ አድርጓል" ተብሎ ነበር።

በርካታ የውጪ ሀገር ዜጎች በተቋሙ ያስተምራሉ። በሮይተርስ ዘገባ መሰረት፣ አሜሪካዊው እስረኛ ኪም፣ የምርምር እርሻ በተቋሙ ለመመስረት ያለመ የክርስትያን በጎ አድራጊ መሆኑን ግልፆ ነበር።

በደቡብ ኮሪያና በቻይና ድንበር የተወለደው ኪም፣ ከዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ ቢያቀናም በትውልድ ኮሪያዊ ነው። ወደ ፒዮንግያንግ ከማምራቱ አስቀድሞም በቻይናዋ ያንቢያን ግዛት እርሻ ተምሯል።

በጎ አድራጊው ኪም

ሌላኛው ኪም ሳንግ-ደክ ወይም ቶኒ ኪም የታሰረው በስለላ ተጠርጥሮ ነበር።

የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙሀን እንደሚሉት፣ የ55 ዓመቱ ኪም ለዓመታት በበጎ አድራጎት ስራ ይሳተፍ ነበር። በፒዩኤስቲ ለአንድ ወር ሰርቶ፣ ሰሜን ኮሪያን ሊለቅ ሲል ነበር ለእስር የተዳረገው።

የዩኒቨርስቲው ቻንስለር ቻን-ሞ ፓርክ ለሮይተርስ እንዳስረዱት፣ ኪም የታሰረው በዩንቨርስቲ ስራው አይደለም። ከዩኒቨርስቲው ውጪ በወላጅ አልባ ህፃናት ድርጅቶች ይሰራ እንደነበርም ገልፀዋል።

ፓስተሩ ኪም

በስልሳዎቹ ገደማ የሚገኘው ኪም ዶንግ-ቹል በትውልድ ሰሜን ኮሪያዊ አሜሪካዊ ፓስተር ነው። በስለላ ተጠርጠሮ እ.አ.አ በ2015 ከተያዘ በኋላ በ2016 የአስር ዓመት እስር ተበይኖበታል።

ከብይኑ በፊት፣ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝቶ፣ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በመመሳጠር ከሰሜን ኮርያ ወታደራዊ መረጃ መመዝበሩን አምኖ ነበር። ሆኖም የደቡብ ኮሪያዋ መዲና ሴኡል ውንጀላውን ውድቅ አድርጋዋለች።

እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 2016፣ ሲኤንኤን ለኪም ቃለ መጠየቅ ሲያደርግለት በቨርጂንያ እንደሚኖር ተናግሮ ነበር።

በደቡብ ኮሪያው ልዩ የኢኮኖሚ ክልል ራሰን፣ የንግድና ሆቴል አግልግሎት ሰጪ ተቋም የነበረው ሲሆን፣ ከታሰረ ጀምሮ ቻይና የሚኖሩትን ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን አለማግኘቱንም አክሏል።