በናይጄሪያ 51 ሰዎች በሽፍቶች ተገደሉ

ከከብቶች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ግጭቶች ያጋጥማሉ Image copyright STEFAN HEUNIS
አጭር የምስል መግለጫ ከከብቶች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ግጭቶች ያጋጥማሉ

በሰሜን ናይጄሪያ የቀንድ ከብቶችን በመዝረፍ የሚታወቁ ሽፍቶች 51 ዜጎችን ማረዳቸው ታወቀ። ከሟቹቹ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ይገኙበታል። ሽፍቶቹ ነዋሪዎቹን ከመቅላታቸው ባሻገር በርካታ ቤቶቸንም አቃጥለዋል።

በካዱና ግዛት ቢርኒን ግዋሪ በተባለ ቀበሌ በደረሰው በዚህ ጥቃት ተጥለው ከተገኙ ትኩስ አስከሬኖች ውስጥ የአንዳንዶቹ ነዋሪዎች የመራቢያ አካል ተሰልቦ ነበር ተብሏል።

ከሞት የተረፉ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ሽፍቶቹ አካባቢውን የከበቡት ቅዳሜ ከሰዓት ላይ ነበር።

ነዋሪዎቹ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ቡሃሪ የጸጥታ ኃይል በአፋጣኝ እንዲልኩና ከዛምፋራ ግዛት ጋር የሚያዋስነውን ድንበር እንዲያስጠብቁ ተማጽነዋል።

ባለፈው ወር በዚሁ ቢርኒን ግዋሪ ቀበሌ 14 የማዕድን ቆፈሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መገደላቸው ይታወሳል።

ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ጥቃት አድራሾቹ ቀደም ሲል ከብቶችን በመዝረፍ የሚታወቁ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን የለየላቸው ሽፍቶች ሆነዋል ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች