ለየት ያሉ ተቃውሞዎች በዓለም ዙሪያ

ሌይማህ ገቦዊ Image copyright VITAL VOICES
አጭር የምስል መግለጫ ሌይማህ ገቦዊ

ዓለማችን ለየት ያሉ ተቃውሞዎችን አስተናግዳለች። ከዚህ በታች አንድ ሦስቱን እንመለከታለን።

በጃፓን ኦካያማ በምትባል ከተማ ሰሞኑን የአውቶቡስ ሾፌሮች የሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው። እውነት ለመናገር ሥራ አላቆሙም። አውቶቡሶቹን እየሾፈሩ ነው። ተሳፋሪዎቹንም እየጫኑ ነው። ነገር ግን አንድ ነገር እያደረጉ አይደለም። ተሳፋሪዎቹን ለጉዟቸው አያስከፍሏቸውም። ነዋሪውን እንደጉድ በነጻ እያሳፈሩ ወደፈለገበት ያንሸራሽሩታል።

ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ያሉት በጨዋ ደንብ ነውም ተብሎላቸዋል።

"የአንሶላ አንጋፈፍም" አድማ

በላይቤሪያ በ2003 የተካሄደው የሚስቶች አድማ የሚዘነጋ አይደለም።

በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት የተማረሩ ሚስቶች መላ ዘየዱ። ከባሎቻቸው ጋር አንሶላ ለመጋፈፈ አለመፍቀድ። ይህ ተቃውሞ የተመራው ሌይማህ ገቦዊ በተባለች ሴት ነበር። ይህቺ ወይዘሮ የመታችው መላና የዘየደችው ዘዴ እጅግ ውጤታማ ሆኖ የእርስ በርስ ጦርነቱን ማስቆም ብቻ ሳይሆን የኖቤል የሰላም ተሸላሚ አድርጓታል።

አጭር የምስል መግለጫ አለቃቸው ወደ ሥራው እንዲመለስ የጠየቁት ሰራተኞች

የምንወደው አለቃ ይመለስ

በማሳቹሴት ደግሞ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ። ጥያቄያቸው ደመወዝ ይጨመርልን አይደለም። እጅግ የምንወደው አለቃችን ወደ ሥራው ይመለስ የሚል ነበር።

ማርኬት ባስኬት ግሮሰሪ የሚሠሩት እነዚህ ሠራተኞች አለቃቸው አርቶር ዲሞላስ ካልተመለሰ ወይ ፍንክች ብለው ነበር አድማ የመቱት። ይህ የሆነው በ2004 ነበር።

ኩባንያው በአቋሙ በመጽናቱ በቀን እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር መክሰር ጀመረ። ሠራተኞቹም የሚወዱት አለቃ ወደ ሥራው እስካልተመለሰ ድረስ አንመጣም አሉ። ወደ አደባባይም ለተቃውሞ ወጡ።

ክረምቱ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ። በመጨረሻ የግሮሰሪው ባለ አክሲዮኖች አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ለዚህ ተወደጅ አለቃ የአክሲዮን ድርሻ መስጠትና መገላገል። ይህን በማድረጋቸው ሠራተኞች ተደሰቱ። አመጹም አበቃ።