"ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አጭር ቀሚስ አትልበሱ!" የዛምቢያ ዩኒቨርስቲ

Dikina Muzeya Image copyright Dikina Muzeya

ከደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ዛምቢያ ጉምቱ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የሆነው የትምህርት ተቋም የቤተ መጻሕፍት ሴት ተጠቃሚዎችን "እባካችሁ ተገላልጣችሁ አትምጡ፣ ወንዶች ሐሳባቸውን ሰብስበው ማጥናት አልቻሉምና" ይላል።

ሉሳካ የሚገኘው ይህ የዛምቢያ ዩኒቨርስቲ ይህንን መመሪያ ያስተላለፈው ከሰሞኑ ነው።

"የደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ዩኒቨርስቲዎች በወግ አጥባቂነታቸው ይታወቃሉ። ሆኖም ሴት ተማሪዎቻቸው በአመዛኙ በዘመነኛ አለባበሶች ማጌጥን ይመርጣሉ" ይላል የቢቢሲው ዘጋቢ ኬኔዲ ጎንደዌ ።

ለወንድ ተማሪዎች አብዝቶ የተጨነቀው ይህ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን በግቢው ውስጥ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት "እባካችሁ ሴት ተማሪዎች ወጉን የጠበቀ አለባበስ ልበሱ። ወንድ ተማሪዎቻችንን ከጥናታቸው እያናጠባችኋቸው ነው።" ሲል ተማጽኗል።

"እግር እግር ምን ያሳያችኋል፤ ይልቅ መጻሕፍቱን ተመልከቱ" ሴት ተማሪዎች

አጫጭር ቀሚስን የሚያወግዘው ዩኒቨርስቲ ይህን አወዛጋቢ ማሳሰቢያ ካስነገረ ወዲህ በርከት ያሉ ተቃውሞዎች ቀርበውበታል። በተለይም ሴት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ብዙዎቹ መመሪያው አልተዋጠላቸውም።

"ቤተመጻሕፍት የምትመጡት መጻሕፍትን እንጂ የሴት እግር ለማጥናት አይደለም" ያሉም አልጠፉም።

"መጀመርያውኑ ለምንድነው እግር እግራችንን የሚመለከቱት" ትላለች የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነቸው ዲኪና ሙዘያ ለቢቢሲ "አርፋችሁ ተደፍታችሁ መጽሐፋችሁን አታነቡም?"

ሆኖም ቢቢሲ ያናገራቸው ወንድ ተማሪዎች አዲሱ መመሪያ ተስማምቶናል ብለዋል።

ኪሊየን ፊሪ የተባለ የዩኒቨርስቲው ተማሪ እንዲህ ይላል።

"እንደምታውቀው የሴቶች ገላ አማላይ ነው። እንዴት ነው የተገለጠ ገላ እያየን ጥናታችን ላይ ትኩረት የምናደርገው። አስበው እስቲ አንዲት ልጅ አጭር ቀሚስ ወይም ጥብቅ ያለ ሱሪ (ታይት) አድርጋ በአጠገብህ ስታልፍ። ሐሳብህ ሁሉ ወደ ሌላ ነገር ነው የሚሄደው።"

ተያያዥ ርዕሶች