"ዳንስ እንደተወዛዋዡ ነው" ምንተስኖት ጌታቸው

ምንተስኖት ጌታቸው ትርኢት እያቀረበ Image copyright MAURACE GUNNING

የምንተስኖት የትውልድ ከተማ አዳማ ናት። በአዳማ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ወደ አዲስ አበባ የመጣው በዊንጌት የቴክንክና ሙያ ትምህርት ቤት ለመማር ነው። ከዚያ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ ዳንስ ህይወት መግባቱን ይናገራል።

ዳንስ የልጅነት ህልሙ አልነበረም። ''መሆን የምፈልገው አባቴ አትሌት ስለነበር የማርሻል አርት ባለሙያ ነበር'' ይላል። በፊልም ላይ የሚያያቸውን የቻይና ማርሻል ጥበቦች እካንበታለሁ ብሎ ያስብ ነበር።

''ቤተሰቦቼ እንደማንኛውም ልጅ ሕክምና አልያም ምህንድስና ባጠና ደስ ይላቸው ነበር'' የሚለው ምንተስኖት ''እኔ ግን ዳንስን መረጥኩና ልቤንም ቀልቤንም ሳበው'' ይላል።

ቤተሰቦቹም በዚህ ሙያ ራስህን የምትችልና በአግባቡ የምትኖር ከሆነ በማለት እንደፈቀዱለት ያስታውሳል።

ምንተስኖት ውዝዋዜን የጀመረው በአዳማ ሰርከስ ውስጥ ነው። በቡድኑ ውስጥ የጅምናስቲክ ስፖርትና የተለያዩ ጥበቦች የነበሩ ቢሆንም በተጨማሪም የባህላዊ ውዝዋዜዎች ይሰሩ ነበር።

ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም ይህንን የውዝዋዜ ተሰጥኦውንና ትንሽ ልምዱን ይዞ ወደ መኩሪያ የቲያትር ስቱዲዮ አመራ።

የተውኔት ባለሙያው አቶ አባተ መኩሪያ በቲያትር ስቱዲዮ ውስጥ መኩሪያ የዳንስ ቡድን ነበረው ይላል ምንተስኖት። በዚያ ውስጥ በመታቀፍ የዳንስ ትርኢቶችን ያቀርብ እንደነበር ያስታውሳል።

Image copyright Meaza Worku

በተለይ የአቶ አባተ መኩሪያ ልጅ ውቢት ይህንን ኃላፊነት ወስዳ ታሰለጥናቸው እንደነበር የሚያስታውሰው ምንተስኖት አሁን ላለበት የዘመናዊ ዳንስ ስልት መነሻ እንደሆነው ይናገራል።

ኮንተፐረሪ ዳንስ

አዲስ አበባ ለዚህ የውዝዋዜ ስልት አፍቃሪዎች የበለጠ የተመቸች ነች የሚለው ምንተስኖት፤ ምክንያቱም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸውን በከተማዋ ማድረጋቸው ነው። የእነዚህ ተቋማት በአዲስ አበባ መኖር ለእርሱ የተለያዩ ትርኢቶችን ለማዘጋጀትና ለማቅረብ እድሉን እንዳሰፋለት ያስታውሳል።

ምንተስኖት ከጀርመን ባህል ማዕከል ጎተ ኢንስቲቲዩት፣ ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ፣ ከኖርዌይ፣ ደቡብ አፍሪካ ኢምባሲዎች ጋር በመሆን ዝግጅቶች አቅርቧል።

ሌላው በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የዳንስ ቡድኖች ጋር በመሆን ትርኢቶችን ማቅረቡንም ይናገራል። ከአዱኛ የዳንስ ቡድን ሌላ ከዴስትኖ፣ ከሀሁ፣ ከጃቤዛ፣ ከወንዳታ የዳንስ ቡድኖች ጋር የተለያዩ ስራዎች መስራቱን ያስታውሳል።

በአዲስ አበባ የዳንስ ጥበብ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ መሰራት እንዳለበት ይናገራል።

Image copyright Meaza Worku

ከሰላምታ ጋር

ምንተስኖት የመአዛ ወርቁ ድርሰት የሆነው 'ከሰላምታ ጋር' በተሰኘው ተውኔት ላይ በዳንስ ተሳትፏል። ዳንሱንም ያቀናበረውም እርሱ ነበር።

ከተውኔቱ ደራሲ መዓዛ ጋር መኩሪያ ስቱዲዮ እያለ እንደሚተዋወቁ የሚናገረው ምንተስኖት ተውኔቱን ይዛ ስትመጣ ሃሳቡን እንደወደደው ይናገራል። ተውኔቱ ላይ በየትዕይንቱ በዳንስ እንዲገለፅ የምትፈልገውን ሃሳብን ፅፋ መምጣቷን የሚያስታውሰው ምንተስኖት "በተውኔቱ ላይ ሁለት ተወዛዋዦች እንዲኖሩ ትፈልግ ስለነበር እኔ ሃሳቧን ወስጄ ቅንብሩን ሰራሁት" ይላል።

መአዛ በተውኔቱ ላይ እንዲቀርብ ያደረገችው ዳንስ በሌሎች ቲያትር ቤቶች ከሚቀርቡ ሙዚቃዊ ተውኔት የተለየ መሆኑን የሚናገረው ምንተስኖት በተውኔቱ ላይ የኮንተምፐረሪ ዳንስ በአብስትራክት መልኩ እንደቀረበበት ይናገራል።

በተውኔቱ ላይ ስመጥር የሆኑት ኤልሳቤጥ መላኩ እና አለማየሁ ታደሰ በሚተውኑበት መድረክ ውስጥ ተቀናጅቶ መስራት የበለጠ ደስታውን ከፍ አድርጎለት እንደነበር የሚገልፀው ምንተስኖት "እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ብዙ ልምድ ያላቸው ምሳሌ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ከእነርሱ ጋር አንድ መድረክ ላይ መሳተፌ ለእኔ ትልቅ መነሳሳት፣ ትልቅ ድጋፍና ጥንካሬ ነበር የሆነኝ። ወደዚህ ዘርፍ ገብቼ እንድማርም ምክንያት የሆነኝም አንዱ ይህ ነው" ይላል።

ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር ስትሰራ ራስህን ወደተሻለ ቦታ ማድረስ እንዳለብህ ትረዳለህ የሚለው ምንተስኖት የዳንስ ትምህርቱን በአውሮፓ ውስጥ በአየርላንድ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሊምሬ ተከታትሏል።

ዳንስን በዲግሪ

Image copyright TANIN TORABI

ዳንስን በተሰጥኦ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ማሳደግ እንደሚቻል ካሳዩት ሰዎች መካከል መአዛ ወርቁ እና ውቢት መኩሪያ መሆናቸውን በቀዳሚነት ይጠቅሳል። ያኔ ነው ዳንስን ዩኒቨርስቲ ገብቼ ለመማር የነሸጠኝ ይላል። ከዚያ በኋላ አይኑን ወደ ተለየዩ ተቋማት አማተረ፤ ተሳክቶለትም በአየርላንድ የሚገኘው እድል ሰጠው።በተቋሙ ደብተር ይዞ ክፍል ውስጥ ከመማር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራዊ ስልጠናዎችን አግኝቷል። ትምህርቱ በተለያየ ዘርፍ ብቁ ሆኜ እንድወጣ ያለመ ነበር የሚለው ምንተስኖት፤ ከትምህርቱ ባሻገር ከዳንስ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ጋር በመገናኘት የዳንስ ትርኢቶችን ያቀርብም ነበር። ይህ ደግሞ ሀገሩንም ሆነ ባህሉንም ለማስተዋወቅ ረድቶታል።

በመቀጠል ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል የተለያዩ ነገሮችን እየሞከረ እንደሆነ ይገልፃል።

ዳንስና ለምአቀፍ ጉዞ

አባተ ሙኩሪያ እያለ በአብዛኛው ከአፍሪካ ከሚመጡ ባለሙያዎች ጋር ሥራውን አቅርቦ ያውቃል። ከአሜሪካ፣ ኖርዌይና ስዊዲን ባለሙያዎች ጋር አንድ መድረክ ተጋርቷል። እነዚህ ባለሙያዎች ስመጥር ከመሆናቸው በተጨማሪ ትላልቅ መድረኮች ላይም አብሯቸው የመሳተፍ እድል ነበረው።

ከተሳተፈባቸው ትላልቅ መድረኮች መካከል አንደኛው ቻይና ሆንግ ኮንግ የተካሄደ ፌስቲቫል ሲሆን "በሴኔጋልና ታንዛኒያ የተካሄዱት ፌስቲቫሎች ራሴንም ሥራዬንም ለማስተዋወቅ መሰረት የሆነኝ ናቸው" ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች