ማንበብና መጻፍ ሳይችል 17 ዓመት ያስተማረው መምህር

ጆን ኮርኮራን Image copyright Alamy

'ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገሩ' የሚለውን ብሂል የሚያጠይቅ ታሪክ ነው።

ትምህርት ለማስተላለፍ ከሚያስፈልጉ ክህሎቶች መካከል ማንበብ እና መጻፍ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ታድያ ሁለቱን መሰረታዊ የእውቀት ማሸጋገሪያዎች ሳይችሉ ለ17 ዓመታት ማስተማር ይቻላልን?

ጆን ኮርኮራን "ማንበብና መፃፍ ሳልችል ለዓመታት አስተምሬያለሁ" ይላል።

እንዴት? ለሚለው ጥያቄም ምላሽ አለው።

ጆን የመምህርነት ሙያን የተቀላቀለው እንደ አውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ ነበር። ልጅነቱን በአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ አሳልፎ፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከተመረቀ በኋላ ለ17 ዓመታት አስተምሯል።

ያደገው በምድር ላይ ማንኛውንም ነገር የመከወን ችሎታ እንዳለው በቤተሰቦቹ እየተነገረው ነበር። እሱም 'የሚሳነኝ አንዳችም የለም' በሚል ልበ ሙሉነት አደገ። ምኞቱ እንደ ታላላቅ እህቶቹ የተጨበጨበለት አንባቢ መሆን ነበር።

ትምህርት ቤት በገባባቸው የመጀመሪያ ዓመታት የንባብ ችሎታን የሚያዳብሩ እንቅስቃሴዎች እምብዛም አልነበሩም። መምህራን እሱና የእድሜ እኩዮቹ ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ያሳስቧቸዋል። ሰልፍ ላይ 'ከንዳ አውርድ' ከማለት ባለፈ የሚጠበቅባቸውም አልነበረም።

ንባብ ለመቻል ፈጣሪን መማፀን

ጆን ሁለተኛ ክፍል ሲደርስ ትምህርት ጠነከረ። ተማሪዎች ንባብ ይለማመዱ ጀመር። ለእሱ ግን ንባብ ፈፅሞ ግራ አጋቢ ነበር። "መጻሕፍት ስከፍት የማየው ነገር አይገባኝም።" ሲል ያስታውሳል።

በልጅ አእምሮው መፍትሔ ሆኖ የታየው ፈጣሪን መማፀን ነበር። ዘወትር ከመተኛቱ በፊት ከእንቅልፉ ሲነቃ በንባብ ተክኖ ይነሳ ዘንድ ፈጣሪ እንዲያግዘው ይለማመናል። ከፀሎቱ በኋላ መጻሕፍት ቢያገላብጥም የጠበቀው ተአምር አልተከሰተም።

እጣ ፈንታው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ማለትም 'የሰነፎች ጎራ'ን መቀላቀል ነበር። ምድቡን መቀላቀሉ ሰነፍ ተማሪ ስለመሆኑ 'ምስክር' የሆነ ቢመስለውም፣ መምህራኑ ግን ተስፋ አልቆረጡም።

'የኋላ ኋላ ንባብ ይገለጥለታል' ብለው ስላመኑ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው እንዲሸጋገር ወሰኑ። አራተኛ፣ አምስተኛ . . . ክፍል መጨመሩን ቀጠለ። የንባብ ነገር ግን አልሆንልህ አለው "ለእኔ ትምህርት ቤት መሔድ የጦርነት አውድማ እንደመሔድ ነበር" ይላል።

ተስፋ መቁረጥ የወለደው አመጸኛነት

አምስተኛ ክፍል ሲደርስ ንባብ ባለመቻሉ ተስፋ ቆረጠና ትምህርት ቤቱን መጥላት ጀመረ። ሰባተኛ ክፍል ላይ ብስጭቱን ከተማሪዎች ጋር በመጋጨት ይገልፅ ጀመር። ባህሪው ከትምህርት ቤት ለመባረርም አበቃው።

"መሆን የማልፈልገውን አይነት አመጸኛ ሰው ሆኜ ብገኝም፤ ምኞቴ ጎበዝ ተማሪ መሆን ነበር። ያሰብኩት ሊሳካልኝ አልቻለም እንጂ" ሲል ወቅቱን ይገልፃል።

ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ መምህራን የሚያዙትን ባጠቃላይ በመፈፀም ራሱን ለመቀየር ሞከረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን የመወጣት ተስፋውም አንሰራራ። ሆኖም ንባብና ጆን መሀከል ያለው ጉድጓድ ሊጠብ አልቻለም። በተቃራኒው በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጎበዝ ስለነበር ሯጭ መሆን ይመኝ ነበር።

በተማሪዎች ዘንድ ከመወደዱ የተነሳ የቤት ሥራውን የሚሰሩለት ጓደኞቹ ነበሩ። በፈተና ወቅት፣ የክፍል ጓደኞቹ መልስ በመስጠት እንዲያልፍ ይረዱታል። ጆን ግን ስሙን ከመጻፍ ያለፈ ችሎታ አልነበረውም። "የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ብሆንም የንባብ ችሎታዬ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እንኳን አይሆንም ነበር" ይላል።

"ከኮራጅነት ወደ ወንጀለኛነት ተሸጋገርኩ"

ጆን በሩጫ ዘርፍ ነፃ የትምህርት እድል አግኝቶ ዩኒቨርስቲ ገባ። ኩረጃንም ቀጠለበት። ቀደም ያሉ ዓመታት ፈተናዎችን መልስ በመሸምደድ መፈተንን ዋነኛ አማራጩ አደረግ።

የመምህራንን ቢሮ ሰብሮ በመግባት የጥያቄ ወረቀት መስረቅ ሌላው መንገድ ነበር። የአንድ መምህርን የፈተና ጥያቄ ለመስረቅ ጓደኞቹን ጭምር ማሰማራቱን ሲያስታውስ "ከኮራጅነት ወደ ወንጀለኛነት ተሸጋገርኩ" በማለት ነው።

ከፈተናዎቹ አንዱን የሰረቀው ቁልፍ ሰሪ ቀጥሮ የመምህሩን ቢሮ በተመሳሳይ ቁልፍ በማስከፈት ነበር። ፈተናውን ለማለፍ ብቸኛ አማራጩ እንደሆነ ቢያምንም ስርቆት ህሊናውን ይቆጠቁጠው ጀመር። "ፈተናውን ከሰረቅኩ በኋላ አለቀስኩ" ቢልም፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም መመረቅ የተሻለ ህይወት ለመምራት ቁልፍ እንደሆነ በማመን ዲግሪ ለማግኘት ኩረጃን ገፋበት።

እንደምንም ብሎ ከተመረቀ በኋላ የመምህራን እጥረት ያለበት አካባቢ የማስተማር እድል አገኘ። ማንበብ ሳይችል መምህር የመሆኑን ተቃርኖ "ማንም ሰው አንድ መምህር ማንበብ አይችልም ብሎ አያስብም" ሲል ይናገራል።

ማንበብ ሳይችሉ ማስተማር

አስተማሪ ሳለ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የማህበረሰብ ሳይንስ ማስተማር ይጠበቅበት ነበር። አንድም ቀን ጥቁር ሰሌዳ ላይ ፅፎ አያውቅም። በእሱ ክፍለ ግዜ የፅሁፍ የትምህርት መርጃዎች ጥቅም ላይ አይውሉም። በምትኩ ለተማሪዎቹ ብዙ ቪድዮ እያሳየ እንዲወያዩ ያደርጋል።

ማንበብ አለመቻሉን ከተማሪዎቹ መደበቅ ነበረበትና ከተማሪዎቹ መሀከል ጎበዝ ተማሪዎችን መርጦ እንዲያነቡለት ያዛል። ተማሪዎቹ በላቀ ችሎታቸው እንደተመረጡ ከመገመት በዘለለ መምህራቸው ማንበብ እንደማይችል አልተጠራጠሩም።

ለተማሪዎቹ የሚቆረቆርና እውቀት እንዲያገኙ የሚፈልግ መምህር በመሆኑ በራሱ ቢኮራም፤ በማስመሰል በመኖሩ ጥፋተኝነት ይሰማዋል። "ማስተማር አይገባኝም ነበር። ዘወትር የጥፋተኛነት ስሜት ያንገበግኝ ነበር። ቢሆንም ሚስጥሬን ለማንም ለመናገር አልደፈርኩም" ሲል ይናገራል።

"ካቲ ማንበብ አልችልም"

ጆን ባለቤቱ ካቲን የተዋወቃት መምህር ሳለ ነበር። 'ባልና ሚስት መሀል ሚስጥር የለም' ብሎ አንድ ምሽት ባለቤቱን "ካቲ፤ ማንበብ አልችልም" አላት። 'ብዙ አላነብም' እንጂ 'ፈፅሞ ማንበብ አልችልም' ማለቱን አልተገነዘበችም።

ከዓመታት በኋላ ለሦስት ዓመት ልጁ መጸሐፍ 'እያነበበ' እንደሆነ ሲያስመስል ባለቤቱ ሚስጥሩን ደረሰችበት። ለልጁ መጸሐፉን ሲተርክ የሚደመጠው ታሪክና የመጸሐፉ ይዘት እንደሚለያይ ባለቤቱ ደረሰችበት። ማንበብ እንደማይችል ስታውቅ ንባብ በሚሻባቸው ቦታዎች መርዳቷን ከመቀጠል ባለፈ ቅሬታ አላሰማችም ነበር።

ሚስጥሩን የምታውቅ ብቸኛ ሰው ባለቤቱ ሆናም ዓመታት አለፉ።

እድሜው ወደ አርባዎቹ ሲጠጋ ማስተማር አቆመ። ካቆመ ከአምስት ዓመት በኋላ ህይወቱን የሚለውጥ አጋጣሚ ተፈጠረ። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የጆርጅ ቡሽ ባለቤት ባርባራ ቡሽ፤ ማንበብ ስለማይችሉ ጎልማሶች በቴሌቪዠን ሲናገሩ የሰማበትን ቅፅበት አይዘነጋውም።

በ47 ዓመቱ ማንበብና መጻፍ የማይችል ብቸኛ ሰው እንደሆነ ያስብ ነበር። ከባርባራ ንግግር ግን ብዙዎች ማንበብ ሳይችሉ እድሜያቸው እንደሚገፋ ተገነዘበ።

የንባብን ሀሁ በ47 ዓመት

በአንድ የመገበያያ ማዕከል ውስጥ ማንበብና መጻፍ ስለማይችል ጎልማሳ ወንድማቸው የሚያወሩ እህትማማቾች አገኘ። ወንድማቸው በአቅራብያው በሚገኝ ቤተ-መጻሕፍት የንባብ ትምህርት እየወሰደ ነበር። ጆን ይህንን አስደሳች ዜና ከሰማ በኋላ ግዜ ሳያጠፋ ወደ ቤተ-መጻሕፍቱ አመራ።

በቤተ መጻሕፍቱ የምትሰራ የ65 ዓመት በጎ ፍቃደኛ ንባብ ልታስተምረው ወደደች። "መምህሬ ማንበብ ስለምትወድ ሁሉም ሰው ንባብ እንዲችል ትፈልጋለች። ንባብን ከስር ከመሰረቱ ታስተምረኝም ጀመር" ይላል።

ወረቀት ላይ አረፍተ ነገር መመስረት ባይችልም በርካታ ሊጽፋቸው የሚፈልጋቸው ሀሳቦች ነበሩት። መምህርቱ ስሜቱን በግጥም እንዲገልፅ በማድረግ ትምህርቱን ገፋችበት።

"ማንበብ ለመማር ሰባት ዓመት ወሰደብኝ። በስተመጨረሻ ማንበብ ስችል ገነት የገባሁ ያህል ነው የተሰማኝ። ከደስታ ብዛት አልቅሻለሁ። ሙሉ ሰው እንደሆንኩ ተሰማኝ" ሲል ይናገራል።

የንባብ መምህርቱ የህይወት ታሪኩን በአደባባይ እንዲናገር ያበረታታችው ታሪኩ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሰዎች እንደሚያነሳሳ በማመን ነበር።

ታሪኩን ለህዝብ ለማካፈል ጥቂት ቢያቅማማም ሰዎች በታሪኩ እንደሚማሩ ተስፋ አድርጎ ለመናገር ወሰነ። ተሞክሮውን በመገናኛ ብዙሀን ካካፈለ በኋላ በአሜሪካ ታዋቂ በሆኑ የቴሌቭዥን መርሀ ግብሮች ተጋበዘ። በሌሪ ኪንግ፣ በኦፕራ ዊንፍሬይና ሌሎችም መሰናዶዎች አሜርካውያን ታሪኩን ሰሙ።

ጆን "ለመማር መቼም አይረፍድም" ሲል መልዕክቱን አስተላልፎ፤ "ለ 48 ዓመታት እስረኛ ነበርኩ። በስተመጨረሻ ግን ነፃ ወጣሁ" ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች