"በተፈጥሮዬ ሰዎች ይስቁብኝ ነበር"

ሮይ ማክጋየር Image copyright RORY MCGUIRE

ሮይ ማክጋየር በልጅነቱ ብዙ ተሰድቧል። የእድሜ እኩዮቹ ቀልወደውበታል። አንጓጠውታል። ይህ ሁሉ የደረሰበት የፊት ቅርፁ ከሌሎች ልጆች የተለየ በመሆኑ ነበር።

የፊቱን ቅርፅ ለማስተካከል በተደጋጋሚ ቀዶ ህክምና ቢደረግለትም የጎላ ለውጥ አልታየም። ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ በሰቀቀን የኖረው ሮይ፤ በ24 ዓመቱ ነገሮችን ለመለወጥ ቆርጦ ተነሳ።

እንደእሱው በፊት ቅርፃቸው ሳብያ መሳለቂያ የሆኑ ሰዎችን ለመደገፍም እንቅስቃሴ ጀመረ።

ልጅ ሳለ ህይወቱ መቼም እንደማይለወጥ ስለሚያስብ አብዛኛውን ግዜ በትካዜ ያሳልፍ ነበር። "እድሜ ልኬን እየተሳቀብኝ እንዲሁም ሰዎች እየተዘባበቱብኝ የምኖር ይመስለኝ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ስኮትላንድ ተናግሯል።

ከቤተሰቦቹ ውጪ ስቃዩን የተረዳለት አልነበረም። በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉና ማህበረሰቡ ያገለላቸው ብዙዎች መሆናቸውን ሲረዳም ሊታደጋቸው ፈለገ።

መጀመርያ ካለበት ሁኔታ ጋር ራሱን ለማስማማትና ተሞክሮውን በተለያዩ ድረ-ገፆች ማካፈል ጀመረ። ቀጥሎም በፊት ቅርፃቸው ምክንያት የሚሰደቡ ሰዎች ችግራቸውን ለፖሊስ የሚያመለክቱበት ሥርዓት ዘረጋ።

ተለዋዋጭ ፊቶች (Changing Faces) በሚል ስለጀመረው ንቅናቄ ሲገልፅ "እኔ ያለፍኩበት ስቃይ ማንም እንዲደርስበት አልፈልግም። ግቤ የቻልኩትን ያህል ሰው መርዳት ነው" ይላል።

ሮይ በልጅነቱ ከደረሰበት የማይረሳው፤ ሰዎች ተሰባስበው ከመሀከላቸው ማን ብዙ እንደሚሰድበው የተወራረዱበትን ግዜ ነው።

"ሰዎች መለወጥ በማይችሉት ተፈጥሯዊ ቅርፃቸው ሊሰደቡ አይገባም። መገለሉ የሚደርስባቸው ሰዎች ችግሩን በአፋጣኝ ለፖሊስ እንዲያመለክቱ እፈልጋለሁ" ይላል።

በበርካታ ሀገሮች ሰዎችን በዘር፣ በሀይማኖት ወይም በሌላ ምክንያት ማንጓጠጥ እንደ ወንጀል ይቆጠራል። ያስቀጣልም። ሮይ እንደሚለው የሰዎችን ቅርፅ የተመረኮዘ ማንቋሸሽም ወንጀል መሆን አለበት።

'ቼንጂንግ ፌስስ' የተሰኘው ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በተሰራ ጥናት መሰረት፤ ወደ 800 የሚሆኑ የተለየ የፊት ቅርፅ ያላቸው ሰዎች ሲሰደቡ ለፖሊስ አያመለክቱም።

ከንቅናቄው አባላት አንዱ ሮብ ሙሬይ "ብዙዎች ሲሰደቡ የማያመለክቱት ፖሲሶች ለውጥ ማምጣት አይችሉም ብለው ስለሚያምኑ ነው" ሲል ሁኔታውን ይገልፃል።

የስኮትላንድ ፓሊስ ኢንስፔክተር ክሌር ሚለር በበኩላቸው "አካላዊም ሆነ ቃላዊ ጥቃት ወንጀል ነው። ሰዎችን በጥላቻ ተነሳስቶ መሳደብን እንኮንናለን። የችግሩ ተጠቂዎችም ማመልከት አለባቸው" ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች