ካለሁበት 32፡ "ኑሮን ፈታኝ የሚያደርገው ባህላቸው ነው"

አብርሐም ታምሩ Image copyright ABRIHAM TAMIRU

አብርሀም ታምሩ ቱርክ ሳካሪያ ነው የሚኖረው። በ2013 የቱርክ መንግሥት የትምህርት እድል ሰጥቶት ነው ወደዚያ የሄደው። የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎችን ከትምህርት ጋር ማስተሳሰር ላይ አተኩሮ እያጠና እንደሆነ አብርሃም ይናገራል።

''ሳካሪያ ከኢስታምቡል 190 ኪሎ ሚትር ትርቃለች'' ይላል ስለሚኖርበት ከተማ ሲናገር። አረንጓዴ ነች፤ መሬት መንቀጥቀጥ ስለሚያጠቃት በከተማዋ ከአምስት ወለል በላይ ያለው ህንፃ መገንባት ስለማይፈቀድ ረዣዥም ሕንፃዎች የሉባትም።

የህዝብ ቁጥሯ ወደ 90ሺህ ያህል የሚጠጋ ሲሆን ግርግር የሌለባት ሰላም የሰፈነባት ለተማሪዎች የምትመች ከተማ ናት ይላል።

አብርሃም ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው። አሁን የሚኖርበትን ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር ሲያነፃፅረው፤ ''አዲስ አበባ ግርግር እና ጫጫታ ስለሚበዛባት ሳካሪያ በዝምታ ውስጥ ሕይወትን የምታጣጥም፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የተቀላጠፈባት ደህንነቷ የተጠበቀ ነው'' ይላል።

Image copyright Xorun Normatov

የሰው ሃገር ሰው

አብርሃም ወደ ሳካሪያ እንደሄደ ለአንድ ዓመት ያህል የሚማረው ቋንቋ ነበር። እናም ከትምህርቱ በኋላ ''ረዘም ያለ የእረፍት ጊዜ ነበረኝ'' የሚለው አብርሃም ለመዝናናትም ሆነ ከሰው ጋር ለመጫወት የከተማዋ ጭር ማለት እና የአዲስ አበባን ግርግር ማጣት በሕይወቱ ላይ በጎም አሉታዊም ተፅእኖ አድርጎ እንደነበር ያስታውሳል።

''መጀመሪያ ላይ ድብታ ተጭኖኝ ነበር'' የሚለው አብርሃም ይህ ሰብዕናው ላይ ለውጥ አምጥቷል ይላል። "በፊት ከጓደኞቼ ጋር መጫወት መዝናናት እወድ ነበር አሁን ግን የበለጠ ነገሮችን በጥልቀት መመለከት እንድችል፣ አንባቢ እንድሆን አድረጎኛል" ይላል።

አብርሃም ከዚህ በፊት የእስልምና እምነት ብቻ የሚከተሉ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ኖሮ አለማወቁ ወደ ሳካሪያ ሲመጣ ትንሽ ግርታ ፈጥሮበት ተቸግሮ አንደነበርም ያስታውሳል።

እርሱ እንደሚለው በአካባቢው ቤተ-ክርስትያን አለመኖሩ እንዲሁም አብረውት ለሚኖሩት ቱርካውያን ክርስትያን እንደሆነ ሲናገር ፊታቸው ላይ የሚያየው ስሜትን ለመልመድ ተቸግሮ ነበር።

ሌላው ነገር ደግሞ ቱርካዊያን ከውጭ ዜጎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ቁጥብ መሆኑንም አስተውሏል። በትምህርት ቤት ከሚያውቃቸው ሴቶች ጋር አብሮ መታየት እና ጥቁር ወንድ ከእነርሱ ሴት ጋር መታየቱ የበርካቶችን ትኩረት እንደሚስብ አስተውሏል።

"ከተማዋ ትንሽም ስለሆነች ከኢስታንቡል ይልቅ ነገሮች እዚህ ይገናሉ።"

''የቱርክ ባህል ኑሯችንን ከባድ አድርጎት ነበር'' ይላል የመጀመሪያዎቹን ዓመታት ሲያስታውስ። ከሌላ ሀገር የመጣን ተማሪዎች በቁጥር ትንሽ ስለሆንን ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ለመቀራቀረብ ብንፈልግም እነርሱ ለውጭ ዜጎች ያላቸው ክፍት አለመሆን ኑሮዬን ከበድ አድርጎታል ይላል።

Image copyright Xorun Normatov

ማን እንደ ሐገር

በሚኖርበት ከተማ ሳካሪያ ኢትዮጵያዊያን ስለማይኖሩ የኢትዮጵያ ምግብ ውል ቢለው ሄዶ የሚመገብበት ስፍራ እንደሌለ የሚናገረው አብርሃም "ከኢትዮጵያ የሚመጡ ተማሪዎች ሲኖሩ ግን እነርሱ ቤት ሰብሰብ ብለን የድርቆሽ ፍርፍርና እንጀራ እንበላለን" ሲል አምሮቱን እንዴት እንደሚቆርጥ ይናገራል።

አብርሃም ሳካሪያን ለትምህርቱም ለኑሮውም ከመረጣት በኋላ መመገብ የሚወደው የቱርክ ምግብ ነው። "ላህማጁን ይባላል። ላህማጁን በስስ ቂጣ ላይ የተፈጨ ስጋ ተደርጎበት ነው የሚዘጋጀው። እዚህ ከተማ ላህማጁን መመገብ በጣም ያስደስተኛል። ክባብ ግን ዘይት ስለሚበዛው አልተመቸኝም።"

የቡና አምሮቱን ለማስታገስ ጎራ ባለባቸው ካፌዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና የሚል ቢያገኝም በጣዕምም ሆነ በሽታ የሃገሩን ያህል እንዳልሆኑለት ይናገራል። ስለዚህ አብርሃም የኢትዮጵያ ቡናን ለመጠጣት ቤቱ ውስጥ ጀበና ያለው። ኢትዮጵያዊ ጓደኛው ዘንድ በመሄድ አፍተልተው እንደሚጠጡም ይናገራል።

ከአገር ቤት ኑሮ ይናፍቀኛል የሚለው አብርሃም "ጓደኞቼ፣ ቤተሰቦቼ ማታ ማታ ቡና ተፈልቶ ተሰብስበን የምንጨዋወተው ነገር ሁሉ ዘወትር በአይኔ ላይ ይሄዳል" ይላል።

Image copyright Abdulaziz Sahin

የሳካሪያ አማላይ ውበት

በሳካሪያ በኖረባቸው ጊዜያት ሁሉ ከመስኮቱ አሻግሮ ሲማትር ሁሌም ልቡን በሐሴት የሚያሸፍተው ሳፓንጄ የተሰኘው ሐይቅ ነው። አዲስ አበባ ሳለ ጀምሮ ለትምህርት ሲያመለክት እና ዩኒቨርስቲውን ሲመርጥ ጀምሮ አይቶ ልቡ ለሐይቁ ሸፍቶለታል።

ሐይቁ የሚገኘው ከአርት ፋኩሊቲ ፊት ለፊት ሲሆን ከፋኩልቲው የመናፈሻ ስፍራ ውስጥ በሚገኙ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጦ በምሽት ፀሐይ ስትጠልቅ ሲመለከት በደስታ የሚያሰክር ስሜት እንዳለው ይናገራል።

ከሐይቁ በፊት የሚገኘው አረንጓዴ ስፍራና ሐይቁ ዳር ዳር የበቀሉ ረዣዥም ሳሮች ውበቱን ያጎሉታል።

''ማለዳ ከሆነ'' ይላል አብርሃም ''በሐይቁ ዳር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች፣ ከርቀት ወደ ኢስታንቡል የሚሄዱ እና ከኢስታንቡል የሚመለሱ መኪናዎችን መመልከት ልዩ ስሜት ይፈጥራል።''

ከመኪኖቹ ጀርባ ተራራ የሚገኝ ሲሆን ተራራው ላይ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች በምሽት መብራታቸው ተራራው ላይ ተረጭቶ ሲታይ ለውበቱ ፈርጥ እንደሆኑትም ይገልፃል። ''ይህንን በምሽት ማየት ሕይወትን በበጎ ጎኑ እንድታይ በር ይከፍታል'' በማለት የፈጠረበትን የደስታ ስሜትንም ያክላል።

Image copyright Xorun Normatov

ከሳካሪያ ወደ አዲስ አበባ

''ሳካሪያ ትንሽ ከተማ ስለሆነች ፅዳቷ በጣም ያስቀናል'' የሚለው አብርሃም ''ነገሮችን የመለወጥ እና በቅፅበት የማድረግ ኃይል ቢኖረኝ የከተማዋን ፅዳት ለአዲስ አበባ ባወርሳት ደስ ይለኛል'' ሲል ምኞቱን ይገልፃል።

ከአዲስ አበባ ደግሞ በተለየ ለፒያሳ የተለየ ናፍቆት እንዳለው የሚናገረው አብርሃም ''አንዳች ኃይል ቢኖረኝ ከሳካሪያ ተነስቼ ፒያሳ ባርፍ ደስ ይለኛል'' ይላል። ፒያሳ የኢትዮጵያን እድገት፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ትግል የሚወክል ስፍራ ስለሆነ እዚያ ስፍራ ብገኝ ደስታዬ ወደር አይኖረውም ይላል።

በመጨረሻም ፒያሳ ላይ ተገኝቼ በእግሬ ብንሸራሸር ከጓደኞቼ ጋር ቡና እየጠጣሁ ባወጋ ደስ ይለኛል ሲል ሃሳቡን ያጠናቅቃል።

ለምንተስኖት ተሾመ እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 33፡ ኑሮን በቴክኖሎጂ ምቹ ያደረገች ሃገር

ካለሁበት 34፡ የሃገሬ ልጆች በሱስ ተጠምደው ሳይ አዝናለሁ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ