ፖምፔዮ የትራምፕና ኪምን ውይይት ለማመቻቸት ፒዮንግያንግ ገብተዋል

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔና የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን Image copyright Reuters

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ታሪካዊውን የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የንግግር መድረክ ለማመቻቸት የሰሜን ኮርያዋ መዲና ፒዮንግያንግ ገብተዋል።

ማይክ ፖምፔዮ ከወር በፊት ከኪም ጋር ከተገናኙ በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ ሲያቀኑ ሁለተኛቸው ነው።

የመጀመርያውን ጉብኝታቸውን ተከትሎ በሰሜን ኮሪያና በአሜሪካ መሀከል "መልካም ወዳጅነት ተፈጥሯል።" ብለዋል። ።

በጉብኝታቸው የኮሪያን ቀጠና ከኒውክሌር ለማፅዳት የሚደረገውን ውይይት ከድምዳሜ የማድረስ እቅድ እንዳላቸው አሳውቀዋል።

በተጨማሪም ጉብኝታቸው ሰሜን ኮሪያ ውስጥ የታሰሩትን ሦስት አሜሪካውያን የማስፈታት ድርድር ጋር እንደሚያያዝ ጭምጭምታዎች አሉ።

ወደ ፒዮንግያንግ ከማምራታቸው በፊት "ሦስቱ እስረኞች እንዲለቀቁ ለ 17 ወራት ጠይቀናል። ሰሜን ኮሪያ እስረኞቹን ትለቃለች ብለንም ተስፋ እናደርጋለን" ማለታቸው ይታወሳል።

አንድ የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣን ዮንሀፕ ለተባለ የዜና ማሰራጫ እንደተናገሩት የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ከመገናኘታቸው በፊት ሶስቱ እስረኞች ነፃ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከፖምፔዮ ጋር ወደ ሰሜን ኮሪያ ያመራው የልኡካን ቡድን ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር ረገድ የአቋም ለውጥ ማድረግ ወይም አለማድረጓን በቅርበት እንደሚከታተሉ አሳውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ፖምፔዮ ወደ ሰሜን ኮሪያ እንደሚሄዱ የተናገሩት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ከኢራን ጋር ያደረጉት የኒውክሌር ድርድር እንዳከተመ ካሳወቁ በኋላ ነበር።

ፕሬዚዳንቱ "ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ መሆኑን እናምናለን" ሲሉ ሁኔታውን ገልፀዋል።

የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ-ኡን የሚያገኙበት ቀን፣ ሰዓትና ቦታ መመረጡንም አክለዋል።

ፕሬዚዳንቱ "ነገሮች እንዴት እንደሚሄዱ እናያለን። ምናልባትም እንዳሰብነው ላይሄድ ይችላል። ቢሆንም ውይይቱ ለሰሜን ኮርያ፣ ለደቡብ ኮርያና ለመላው ዓለምም ታላቅ ነገር ነው።" ብለዋል።

ትራምፕ የሰሜን ኮሪያን ጥሪ ተከትለው ለውውይት ወደ ፒዮንግያንግ ለመሄድ መስማማታቸው ብዙዎችን ያስገረመ ውሳኔ ነበር።

ለውይይት ይመቻሉ ተብለው ከተመረጡት ቦታዎች አንዳቸውም በአሜሪካ ስለማይገኙ፤ ውይይቱ በቅርቡ በሰሜን ኮርያ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

ኪም ጆንግ-ኡን ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር ለመወያየት ወደ ቤጂንግ በሄዱበት ወቅት፤ "የኮሪያን ቀጠና ከኒውክሌር የፀዳ ለማድረግ ጊዜውን የጠበቀና የተቀናጀ እርምጃ ይወሰዳል።" ሲሉ ለቻይና መገናኛ ብዙሀን መናገራቸው ይታወሳል።