"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

ዶክተር አሰፋ ባልቻ

"ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር ስንል እኮ ዝም ብለን እንዲያው በጠመንጃ ብቻ አይደለም። በጠመንጃ የቆሰለውንም፤ በሳንጃ የተወጋውንም የሚያክሙ አዋቂዎች ሀገር ናት" የሚሉት ከግማሽ በላይ ዕድሜያቸውን በባህል መድኃኒት ጥናት ላይ ያሳለፉት ዶክተር አሰፋ ባልቻ ናቸው።

"የኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒትና ሕክምና የምዕተ-ዓመት ጉዞ" ('Acentury of Magico-Religious Healing: The African, Ethiopian case (1900-1980)) በሚለው መፅሀፋቸውም በባህል ህክምና ዘርፍ በፅሁፍ የሰፈሩ ጥንቅሮችን፣ የቁጥርና የፊደላት ማስላት፣ መናፍስት፣ ዕፅዋትን፣ ማዕድናትን እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ፈውስን ማግኘት ኢትዮጵያውያን እንዴት ልቀውበት እንደነበር ዳስሰዋል።

አሁንም ቢሆን ለራስ ህመም ጠንከር አድርጎ ማሰር፣ ለጉንፋን ዝንጅብል በማር፣ ለሆድ ድርቀት ተልባን በጥብጦ መጠጣት ብዙ ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ሆነ ለወዳጆቻቸው ፈውስ ብለው የሚመክሯቸው ናቸው።

በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በከተማም በሽታ ባስ ካለለ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ የተለመደ አይደለም።

"ባህላዊ መድኃኒት ትልቅ ስፍራ ነበረው አሁንም እየተሰራበት ነው። የዘመናዊ ህክምና አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም መወደድ አማራጩን ወደ ባህል መድኃኒት እንዲያዞር አድርጓል" ይላሉ።

ትውልድና እድገታቸው ደሴ ከተማ የሆነው ዶክተር አሰፋ የባህል መድኃኒት ምርምራቸውን በዚችው ከተማ ነው የጀመሩት። ለዚህ ደግሞ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን እውቀት ለመቅሰምና ለባህል ህክምና ቅርብ ከሆኑት ከእናታቸው በላይ ሰው አላገኙም።

በታሪክ መምህርነታቸው በደሴ ወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤት ከፍተኛ ዝናን ያተረፉት ዶክተር አሰፋ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ጥናት እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በባህል መድኃኒት ላይ ሰርተዋል።

"በመንግሥት ፍቃድና ትዕዛዝ እንደ እድል ሆኖ የታሪክ ትምህርት ደረሰኝ እናም እጣ ፈንታዬ ተወሰነ" ይላሉ። በዩኒቨርስቲው ከነበሩት ትልልቅ ምሁራን መካከል ስለ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ አውርተው አይጠግቡም።

የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት ጅማ

የኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት ምርምራቸውን ሲጀምሩ "ታሪክ እንዴት ይፃፋል? እንዴትስ መደምደሚያ ላይ ይደረሳል?" የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ መሰረትም አስይዟቸው ነበር።

የባህል መድኃኒት ውርሳችን ዝም ብሎ በኢትዮጵያዊያን ብቻ የበቀለ ነው? ወይስ ከሌላ ሃገር ተፅእኖ አለበት? እሰከ መቼስ ወደኋላ መውሰድ ይቻላል የሚሉትንም ጥያቄዎችንም ለመመለስ ብዙ ፅሁፎችን ዳስሰዋል።

የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ ከፍተኛ ክፍተት አለበት የሚሉት ዶክተር አሰፋ፤ ያንንም ለመሙላት ፅሁፎቹን ከመዳሰስ በተጨማሪ አዋቂዎቹን በማናገር እንዲሁም ስለእፅዋቶቹ በዝርዝር ማወቅ እንደሚያስፈልግ ዶክተር አሰፋ ይገልፃሉ።

መድኃኒቶቹም ሆነ ዕውቀቱ ይጠበቅበታል የሚባሉት ቤተ-ክርስቲያን እንዲሁም መስጊዶችን ፈትሸዋል።

ኢትዮጵያ በባህል መድኃኒት ረዥም ታሪክ እንዳላት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያደረጉ የተጓዦችን ማስታወሻ እንዲሁም የሪቻርድ ፓንክረስት ፅሁፎችን ያጣቅሳሉ።

"ከቀላል ስብራት ጀምሮ ውስብስብ ተውሳክና እንደ ካንሰር ወይም በተለምዶ መጠሪያው ነቀርሳ የመሳሰሉ የውስጥ በሽታዎችን ማከም ይሞክሩ የነበሩበት አገር ሰዎች መኖሪያ ለመሆኗ፤ በአረብኛ፣ በግዕዝ፣ የማጣቀሻ ፅሁፎችም አሉ" ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የፖለቲካ ታሪኩ ብቻ ነው የሚሉት ዶክተር አሰፋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ውትድርና፣ የሥርዓተ-ፆታና ሌሎች የታሪኮችን መንገር እንዳልተለመደ ያስረዳሉ።

"እኛ የምናውቀው የእፅዋት ስብስቡን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለመድኃኒትነትም ይጠቀሙባቸው የነበሩ የማዕድኖች ስብስብ ነበራቸው" የሚሉት ዶክተር አሰፋ "ከነበረባቸው ተፈጥሯዊ ችግርና ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ረዥም እድሜ ኖረዋል፤ ይህም በመድኃኒት ምን ያህል የላቁ እንደነበር ማሳያ ነው" ይላሉ።

ክፍተቱ እንዴት ተፈጠረ?

ባለፉት ዘመናት የሀገር በቀሉን የመድኃኒት ህክምና ጥበብ በሐገሪቱ ሰፍኖ ከቆየው ከፊል የፊውዳል ሥርዓትና ከጥቁር አስማትና መጥፎ መናፍስት ጋር አያይዞ መመልከት የተለመደ በመሆኑ የባህል መድኃኒትን ታሪክ ጥላሸት እንደቀባው ያወሳሉ።

ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ታሪክ ጋር ተያይዞ የመጣው የዘመናዊነት (ሞደርኒዝም) ታሪክ በባህል መድኃኒት እውቀትም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳሳረፈበት ዶክተር አሰፋ ይናገራሉ።

በተለይም በአፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመሩት ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች በህክምናው ዘርፍም በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ እንደነበር ይናገራሉ።

መጀመሪያ አካባቢም የምዕራቡ ህክምና ተቀባይነት ያገኘው በአፄ ምኒልክና በመሳፍንቱ አካባቢ ቀጥሎም በመኳንንቱ፣ በአጠቃላይ ደግሞ በዋና ከተሞችና በፖለቲካ የሥልጣን ማዕከሎች በሚገኙ ህዝቦች ዘንድ መሆኑንም ሪቻርድ ፓንክረስትን ጠቅሰው ፅፈዋል።

በተለይም የአባላዘር በሽታዎችን ፈውስ ለመፈለግ ከውጭ ሀገር በሚመጡ ሳርሳፓራሊና ካሎሜል ወይም የሜርኩሪ ክሎራይድ መድኃኒቶች መስፋፋትንም ይጠቅሳሉ።

ሆኖም ግን አፄ ምኒልክ የባህል ሐኪሞችን ክህሎት ከመጠቀም ወደ ኋላ እንዳላሉም ጨምረው ይናገራሉ።

ሆኖም ግን በወቅቱ የባህል መድኃኒቶችን መጠቀም በማህበረሰቡ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሰረፀ እንደነበር ይገልፃሉ።

የህዳር በሽታ ተብሎ የሚጠራው ኢንፍሉዌንዛ በተከሰተበት ወቅት የባህር ዛፍ ቅጠልና ነጭ ሽንኩርት እንዲሁም የባህላዊ የአልኮል መጠጦች እንደ መከላከያ ወይም ፈውስ ጥቅም ላይ እንደዋሉ የተለያዩ የታሪክ መዛግብቶች እንደሚያትቱ ይናገራሉ።

የባህል መድኃኒት ከፍተኛ ክፍተት የተፈጠረው ጣልያን አምስት ዓመት ኢትዮጵያን ይዛ በነበረችበት ወቅት እንደሆነ ዶክተር አሰፋ ይናገራሉ።

"ጣልያን የኃገረ-ሰብ መድኃኒትና ህክምና አዋቂዎች ናቸው ባለቻቸውና በተለይም ደግሞ የቤተ-ክህነት ትምህርት በቀሰሙ የመስኩ ባለሙያዎች ላይ በሰነዘረችው ጥቃትና የዘመናዊ ህክምናን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት የተነሳ በቀደሙት ዘመናት የበላይነት የነበረው የባህል ህክምና መዳከመ ጀመረ"ይላሉ።

ከነፃነት በኋላም የባህል መድኃኒቶች ተጠናክረው መውጣት ያልቻሉ ሲሆን በደርግ ጊዜም ከዕምነት ጋር ከተያያዘ ትምህርት ጋር በመጣመሩ የህክምናውን ዕውቀት ያዳበሩ ባለሙያዎች ችግሮች እንደገጠሟቸው ዶክተር አሰፋ ይናገራሉ።

ኢህአዴግም ስልጣን ከያዘ በኋላ የባህል መድኃኒትን ማሳደግ፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም የባህል መድኃኒት አዋቂዎችን መመዝገብና ቀስ በቀስም የባህልና ዘመናዊ የሕክምና መስኮችን ስለማዋሃድ በተመለከተ የ1985 ጤና ፖሊሲው ውስጥ ቢካተትም ምንም ሥራ እንዳልተሰራ ዶክተር አሰፋ ይናገራሉ።

"ይህን የዕውቀት ሃብት እንደማይረባና እንደማይጠቅም አድርገን ነው የምናየው። የእኛን ሀገር የባህል ህክምና ለምን እንደተጠየፍነው አላውቅም፤ ትውልድ በተላለፈ ቁጥር ትልቅ ሃብት እያጣን ነው። በጣም የሚከበሩ አዋቂ ሰዎችን እያጣን ነው። የአንድ በሽታ መድኃኒት ማወቅ ማለት እኮ በአንድ ዩኒቨርስቲ 20 ዓመት የሰለጠነ ሰው ከአንድ አካል በላይ የሚያውቀው የለም'' ይላሉ።

ለስምንት ዓመታት በአትላንታ በሚገኘው በኤምሪ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ማጥናታቸው የኢትዮጵያንም ሆነ የተለያዩ ሀገራትን የባህል መድኃኒቶች በጥልቀት ለማየት እንዳስቻላቸው ይገልፃሉ።

ከአሜሪካ ከተመለሱም በኋላ የጤና ጥበቃን እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚሏቸውን ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው የባህል መድኃኒት ጥናትና ምርምር የሚደረግበትና ቀጣይነቱን የሚያረጋግጥ ተቋም እንዲኖር ቢጎተጉቱም "ከከንፈር መምጠጥ በላይ ምላሽ አልተሰጠኝም" ይላሉ።

"ይህን ያህል ዓመት ተጉዘን አንድ የባህል መድኃኒትን የሚመለከት ተቋም የለም" የሚሉት ዶክተር አሰፋ ያናገሩዋቸው አዋቂዎች በዕድሜ እየገፉ መሆኑና እውቀታቸውን ሳያስተላልፉ እንዳይቀር ስጋት አላቸው።

"አንተ ማዕከሉን ክፈተው እንጂ እኛ ያለንን የመድኃኒት ዕውቀትን በነፃ እንሰጥሀለን ብለውኝ ነበር። እሱንም ማድረግ አልቻልኩም" ይላሉ።

ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር የሚሉት ዶክተር አሰፋ ተመልሰው ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ መምህርነት እንዲሁም በምርምሩ ክፍል ኃላፊነት ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።

በመቀጠልም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በመሆን ሦስት ዓመት ከሰሩ በኋላ ካለው ሥርዓት ጋር ባለመስማማታቸው በፍቃዳቸው ከሥራቸው ለቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በግላቸው ተማሪዎችን ማማከር፣ ምርምሮችን ማድረግ እንዲሁም አዲስ መፅሀፍ ለማሳተም በሂደት ላይ ናቸው።