ግጭቶች፣ መፈናቀልና የፌዴራሉ መንግሥት መልስ

አቶ ምትኩ ካሳ እና አቶ ንጋቱ አብዲሳ
አጭር የምስል መግለጫ አቶ ምትኩ ካሳ እና አቶ ንጋቱ አብዲሳ

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከወራት በፊት የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች የክልሉ መንግሥት የምንስማማበት መፍትሄ ሊሰጠን አልቻለም የሚል ቅሬታቸውን የያዘ ደብዳቤ ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መፃፋቸው ተዘግቧል።

ተፈናቃዮቹ ከክልሉ መንግሥት መሬት እና የማቋቋሚያ ድጋፍ የሚፈልጉ ቢሆንም የቀረቡላቸው አማራጮች ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ ዳግመኛ መመለስ አሊያም በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን መቀላቀል እንደሆነ ይናገራሉ።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ በመሆናቸው ለተፈናቃዮች መሬት እና የማቋቋሚያ ገንዘብን ማደል የተሳሳተ መልዕክት እንዳያስተላልፍ በመፍራት ክልሉ ይሄንን ከማድረግ እንዲቆጠብ ሳያደርገው እንዳልቀረ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች ያስረዳሉ።

ለነገሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት ላፈናቀላቸው ዜጎች መፍትሄ መስጠትን በተመለከተ ተቀዳሚ አማራጩ ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ቀርፎ ተፈናቃዮቹን ወደቀደመ መኖሪያቸው መመለስ እንደሆነ ይገልፃል።

ሆኖም ችግሮቹን መቅረፉም ሆነ ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ማቋቋሙ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀላል ፈተና የሚሆን አይመስልም።

"ስምንት ወር ሙሉ ያለሥራ ነው የተቀመጥነው" የሚሉት የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ሉጁማ መሃመድ ናቸው። ወይዘሮ ሉጁማ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ከቀያቸው ተፈናቅለው በምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ እንዲሰፈሩ ከተደረጉ ዜጎች መካከል አንዷ ናቸው።

"እንደሚቀለብ በሬ እንዲሁ ቁጭ ማለት አስቸጋሪ ነው። እዚህ ምንም ሥራ የለም፤ ኑ እና ይሄንን ሥሩ የሚለን ነው ያጣነው" ይላሉ ።

የግጭት ወለድ ተፈናቃዮች ቁጥር ማደግ

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ከድርቅ እና ከግጭት ጋር በተያያዘ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ገደማ ነው ይላሉ።

የድርቅ ተፈናቃዮች በአብዛኛው ሆን ተብሎ ውሃ አጠር ስፍራዎችን ለቅቀው የተሻለ ውሃ ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍሩ የሚደረግ ሲሆን፤ ከፍተኛውን ቁጥር ግን የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች ግጭት ያፈናቀላቸው ዜጎች ይይዛሉ፤ ይህም ቁጥር ከስምንት መቶ ሺህ ይልቃል።

ከዚያም ውስጥ አንድን ክልል ለቅቀው ወደ ሌላ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች 33 በመቶ ብቻ ናቸው፤ የተቀሩት ክልላቸውን ሳይለቁ ግጭቱን በመፍራት ከቀበሌዎቻቸው የሸሹ እንደሆኑ አቶ ምትኩ ይገልፃሉ።

በሌላ በኩል በቅርቡ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ጉጂ ዞን የተቀሰቀሰ ግጭት በርካቶችን ማፈናቀሉን አቶ ምትኩይናገራሉ።

ለጊዜው የተሟላ መረጃ ስለሌላቸው ትክክለኛውን ቁጥር ለመናገር እንደሚቸግራቸው ለቢቢሲ የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ኗሪዎች መኖሪያቸውን ጥለው ሸሽተው እንደነበር ይገምታሉ። በርካቶች የግጭቱን መርገብ ተከትሎ እንደተመለሱም አክለው ተናግረዋል።

በልዩ ልዩ ምክንያቶች የዜጎች መፈናቀል ለኢትዮጵያ አዲስ ክስተት አይደለም። ድርቅ እና ጎርፍን የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ ረሃብ፣ ጦርነት እና መንግሥታዊ የልማት ውጥኖች በርካቶችን ከኑሯቸው እና ከቀያቸው ሲነቅሏቸው ቆይተዋል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት ግን በቅርብ ጊዜ ባልተለመደ ሁኔታ የብሄር መልክ ያላቸው ግጭቶች እና ጥቃቶች ዐብይ የመፈናቀል ምክንያቶች ይሆኑ ይዘዋል።

እስከ መጋቢት 2008 ዓ.ም ድረስ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከአጠቃላዩ የተፈናቃዮች መጠን ሃያ ስድስት በመቶ ብቻ ይሸፍን እንደነበር ባለፈው ዓመት ለህትመት የበቃ የመሃሪ ታደለ ማሩ ጥናት ያመለካታል።

የሰብዓዊ መብቶች ህግ አጥኝ እና የህዝባዊ አስተዳደር ተመራማሪው መሃሪ በጥናታቸው እንደሚያትቱት ተፈናቃዮች የራሳቸው የሆኑ ልዩ የአደጋ ተጋላጭነቶች እና ፍላጎቶች ያላቸው መሆኑ፣ ኢትዮጵያ ህፃናት እና ስደተኞችን ከመሳሰሉ ሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለየ ተፈናቃዮችን የሚመለከት ግልፅ ህጋዊ ማዕቀፍ ያላበጀች ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ለተፈናቃዮች በቂ ከለላ የማቅረብ ክፍተት እንዲኖር አድርጎታል።

አጭር የምስል መግለጫ ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች

መመለስ እና ማስፈር

የፌዴራል መንግሥት ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ የብሄር መልክ ያላቸው ግጭቶችን፣ በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች ተቀስቅሶ በአካባቢው ከፍ ያለ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከተለውን ግጭት የሚያጣሩ፣ ልዩ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ እና መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን የሚከታተሉ ግብረ ኃይሎችን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ድረስ ያሉ መስሪያ ቤቶችን አካትቶ ማቋቋሙን ይገልፃል።

የፌዴራል እና አርብቶ አደር የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር እነዚህን ሥራዎች ያስተባብራል፣ ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ በሕዝቦች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ያዳብራሉ፣ ቅራኔዎችንም ይቀርፋሉ የተባሉ የሰላም ጉባዔዎችንም ያከናውናል።

በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት አቶ ንጋቱ አብዲሳ ተቀዳሚው የመፍትሄ እርምጃ ግጭቶችን ባሉበት ማስቆሙ በመሆኑ፤ ይህንን ለማሳካት ከፌዴራል ፖሊስ እና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ይናገራሉ።

ተፈናቃዮችን በተመለከተም "ምን ያህል ቀሩ? ምን ያህሉስ ተመለሱ? የሚለውን ተከታትለን መረጃ የምንይዘው እኛ ነን፤ መመለስ የሚፈልጉትን እና የማይፈልጉትምን ለይተን መረጃ ይዘናል" ሲሉ አቶ ንጋቱ ለቢቢሲ ይገልፃሉ።

በመረጃው መሠረት መመለስ የማይፈልጉትን በተመረጡ ቦታዎች የማስፈሩን እና የማቋቋሙን ኃላፊነት የክልል መንግሥታት ይወስዳሉ።

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ እንደሚሉት ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ድንበር አካባቢ ግጭቱን ፈርተው ከሸሹት ተፈናቃዮች መካከል 300 ሺህ ያህሉ ወደቀያቸው ተመልሰዋል። መመለስን ያልፈለጉ ሃያ ሺህ ተፈናቃዮች ደግሞ በተመረጡ ወረዳዎች በተገነቡላቸው "ጊዜያዊ ቤቶች" እንዲሰፍሩ ተደርገዋል።

ለዚሁ ተግባርም በኦሮሚያ ክልል አስራ አንድ በሶማሌ ክልል ደግሞ ስምንት ቦታዎች ተመርጠው የቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ በሄደ ቁጥር ተጨማሪ ቤተሰቦች እንዲገቡባቸው ይደረጋል።

ተፈናቃዮችን የማቋቋሙን ፈታኝ ሥራ የሚያከናውኑትን የክልል መንግሥታት ለመደገፍ የሚውል ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የፌዴራል መንግሥት መመደቡን የሚገልፁት ኮሚሽነሩ፤ ይህም ገንዘብ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉትን ብቻ የሚመለከት ይሆናል ይላሉ።

በሌላ በኩል እርሳቸው የሚመሩት ኮሚሽን ከሌሎች የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ ሆኖ የነፍስ ወከፍ እርዳታ፣ ምግብ እና አልባሳት የመሳሰሉትን ያቀርባል።

ስጋት እና ጥርጣሬ

በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ወሰን የተቀሰቀሰው ግጭት አፈናቅሏቸው በኦሮሚያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ጊዜያዊ ናቸው በተባሉ ቤቶች እንዲሰፍሩ የተደረጉ ዜጎች ኑሯቸውን በዘላቂነት ከሚደግፍ ሥራ እጦት አንስቶ እስከ መኖሪያ ስፍራ አለመመቸት ድረስ ቅሬታ ያሰማሉ።

ተንታኞች እና አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው የአሰፋፈር ሒደቱ በተፈናቃዮች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ማኅበራዊ ውዥንብር ያወሳሉ።

ከቤንሻንጉል ተፈናቅለው ባህር ዳር ከሚገኙ የአማራ ተወላጆች ደግሞ ግጭቶች በመንግሥት አካላት ርብርብ ከበረዱ እንዲሁም የሰላም እና እርቅ ጉባዔዎች ተከናወኑና ሁሉም ነገር የተስተካከለ ከመሰለ ከተወሰነ ጊዜ ቆይታ በኋላ ግጭቶች ዳግም የማገርሸት ልማድ እንዳላቸው ይጠቅሱና፤ በዚህም ምክንያት ወደተፈናቀሉበት አካባቢ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

አቶ ምትኩ ግን ሕግ-መንግሥቱ ለዜጎች የሚያጎናፅፈውን ወደፈለጉበት ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አጣቅሰው፤ ግጭቶች እስከረገቡ ድረስ ተፈናቃዮች በጊዜ ሒደት ወደቀደሙ መኖሪያዎቻቸው የመመለስ ዕድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን ይናገራሌ። ለዚህም ያለፉት ዓመታት ተሞክሯቸውን በአስረጅነት ያነሳሉ።

አገሪቱ ተዋቅራ ያለችበት ብሔርን ያማከለ ፌዴራሊዝም በዜጎች ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚፈጠርን የሥነ-ሕዝብ ለውጥ የሚያበረታታ አይደለም የሚለው ደግሞ የመሃሪ ታደለ ጥናት ነው።

ብዙ ቁጥር ያላቸው የአንድ አካባቢ ወይንም ብሔር ተወላጆች በሌላ አካባቢ በሚኖሩበት ወቅት የሥነ-ሕዝብ እና የፖለቲካዊ ስልጣን ሚዛን መዛባትን የመፈጠር ዕድል አለው። በመሆኑም በተፈጥሮ ኃብት ፉክክር እና በወሰን ይገባኛል ሙግት ግጭቶች የመፈጠራቸውን ያህል፤ ዞን እና ወረዳን የሚያስተዳድሩ ባለስልጣናትም የግጭት ለኳሽ ወይንም አቀጣጣይ ሆነው ቢገኙ አይደንቅም።

ለወትሮው ግጭት ወለድ መፈናቀሎችን በሽፍንፍን ለማለፍ ይሞክራል እየተባለ የሚተቸው መንግሥት አሁን የችግሩ መጠን ሊሸፋፈን ከሚችልበት ደረጃ ያለፈበት ይመስላል። ከታች ያሉ አመራሮችን ለችግሩ ተጠያቂ አድርጎ ጣት ሲቀስረባቸው ተስተውሏል።

የተፈናቃዮች መበራከት እና ከዚሁም ጋር አብረው የሚግተለተሉ ፈተናዎች የክልል መንግሥታትን ጫንቃ ከመፈተንም ባለፈ የፌዴራል መንግሥቱን መላ የሚሹ ሆነዋል።

ተያያዥ ርዕሶች