አመጋገባችን ማረጥን ሊያፋጥን ወይም ሊያዘገይ ይችላል

ምግብ Image copyright Getty Images

ካርቦሃይድሬት የበዛበት ምግብ አብዝቶ መመገብ ማረጥን ያለጊዜው ሊያስከትል እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

የሴቶች የማረጫ እድሜ 51 በሆነባት እንግሊዝ፤ ብዙ ፓስታ እና ሩዝ መመገብ ማረጥን 1 ዓመት ከስድስት ወር ቀደም ብሎ እንዲጀምር ሊያደረገው ይችላል።

በሌላ በኩል የሊድስ ዪኒቨርሲቲ በ914 የእንግሊዝ ሴቶች ላይ ያደረገው ጥናት፤ የአሳ ዘይት የበዛበት ምግብ እና ጥራጥሬዎችን መመገብ የማረጫ ጊዜ ዘግይቶ እንዲጀምር እንደሚያደርገው ያሳያል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ተፈጥሯዊ ዘረ-መልን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮችም የማረጫ ጊዜን ይወስኑታል ይላሉ።

ምግብ ነክ ግኝቶች

በምግባቸው ውስጥ እንደ ባቄላ፣ አተር፣ ምስር እና ሌሎች ጥራጥሬዎች የሚመገቡ ሴቶች የማረጫ ጊዜያቸው 1 ዓመት ከ6 ወር ዘግይቶ እንዲጀምር አድርጎላቸዋል ይላል ጥናቱ።

በተቃራኒው እንደ ፓስታ እና ሩዝን የመሳሰሉ ካርቦሃይድደሬት የበዛባቸው ምግቦችን አብዝተው የሚመገቡ ሴቶች ደግሞ የማረጫ ጊዜያቸው 1 ዓመት ከ6 ወር ቀድሞ እንዲጀምር ሆኗል።

ተመራማሪዎቹ ጥናቱን በሚያካሂዱበት ወቅት ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት ከሚወስኑ ጉዳዮች መካከል የሴቶቹን ክብደት እና የወሊድ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሲሆን፤ ከዘረ-መል አሰራር ጋር የተያያዙ ሂደቶችን ግን ከግምት ውስጥ ማስገባት አልቻሉም።

ጥናቱ ቅኝታዊ በመሆኑ የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ መድረስ ባይቻልም፤ ተመራማሪዎቹ ግን በጉዳዩ ላይ ተቀራራቢ ማብራሪያዎችን አቅርበዋል።

የጤና እክሎች

ከአጥኚዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው ፕሮፌሰር ጃኔት ኬድ እንደምትለው ለአንዳንድ ሴቶች ማረጥ የሚጀምርበት እድሜ ከባድ ለሆነ የጤና እክል ሊዳርጋቸው ይችላል።

ከተፈጥሯዊ ጊዜያቸው ቀድመው ማረጥ የሚጀምሩ ሴቶች ለተለያዩ የአጥንት እና የልብ ችግሮች የሚጋለጡ ሲሆን፤ ዘግይተው ማረት የሚጀምሩት ደግሞ ለጡት፣ ለማህጸን እና ለእንቁልጢ (ኦቫሪ) ካንሰር የተጋለጡ ናቸው።

Image copyright Getty Images

ተያያዥ ርዕሶች