በዝማሬ የተካኑት ዓሳ ነባሪዎች

ድንቅ ዜማን የሚያወጣው ሃምፕባክ የተባለው ዓሳ ነባሪ Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ ድንቅ ዜማን የሚያወጣው ሃምፕባክ የተባለው ዓሳ ነባሪ

'ዝማሬ ለአእዋፍት ብቻ የተሰጠ ፀጋ አይደለም' የሚሉት ዓሳ ነባሪዎች፤ የእንስሳቱ ዓለም ዜመኛ መሆናቸውን ለማስመስከር ከውቅያኖስ በታች ሕብረ ዝማሬ ያስደምጣሉ።

የአርክቲክ ውቅያኖስ የበረዶ ግግርን ጣሪያቸው ያደረጉ ዓሳ ነባሪዎች ሙዚቃ አፍቃሪ መሆናቸው የታወቀው በሚያሰሟቸው የተለያዩ ዜማዎች ነው።

ሀምፕባክ የሚባሉት የዓሳ ነባሪ ዝርያዎች ከቀድሞውም በሙዚቃ ይታወቃሉ። በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚያሳየው ግን ከሀምፕባክ በተጨማሪ ቦውሄድ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ዓሳ ነባሪዎችም ያቀነቅናሉ።

በስቫልባርድ ደሴት የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው ዓሳ ነባሪዎቹ በሙዚቃ ችሎታቸው አእዋፍትን ያስንቃሉ። ይህ ባህሪያቸው ከሌሎች የዓሳ ነባሪ ዝርያዎች ብቻ ሳይሆን ከተቀሩት አጥቢ እንስሳትም ልዩ ያደርገቸዋል።

ፕሮፌሰር ኬት ስታፎርድ የተባለች ተመራማሪ በሰራችው ጥናት መሰረት ባለፉት ሦስት ዓመታት በስፒትስበርገን ደሴት የሚኖሩ ዓሳ ነባሪዎች 184 አይነት ሙዚቃ አሰደምጠዋል።

ዓሳ ነባሪዎቹ በየዓመቱ ክረምት ከገባ በኋላ ለ24 ሰአታት ሙዚቃ ያንቆረቁራሉ።

ፕሮፌሰር ኬት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዓሳ ነባሪዎቹ ሲያዜሙ ከሺህ በላይ ፊደላት አሰምተዋል።

በተመራማሪዋ ገለጻ መሰረት አንድ ዓሳ ነባሪ ከ45 ሰከንዶች እስከ 2 ደቂቃ ያዜማል። "የዓሳ ነባሪዎቹ ሙዚቃ እንደ ክላሲካል ሙዚቃ ነው። ከ20 እስከ 30 ደቂቃዎች ያዜሙትን ይደጋግሙታል" ትላለች።

ሀምፕባክ የዓሳ ነባሪ ዝርያዎች ከዓመት ዓመት የሚያሰሙት ሙዚቃ ተመሳሳይ ነው። በተቃራኒው ቦውሄድ ዓሳ ነባሪዎች ሙዚቃቸውን በቀናት ልዩነት ይለዋውጣሉ። ተመራማሪዎችን ያስገረመውም ይህ የዜማ መለያየት ነው።

አብዛኞቹ አጥቢ እንስሳት ተመሳሳይ ሙዚቃ ደጋግመው ያሰማሉ። አጥኚዋ የዓሳ ነባሪዎቹን ሙዚቃ "ውስብስብና ያልተለመደ" ስትል ትገልጸዋለች።

ተጨማሪ ጥናት ቢያስፈልግም በሚራቡበት ወቅት የሚያዜሙት ወንዶቹ ናቸው። ከሙዚቃ ችሎታቸው ባሻገር ግግር በረዶን በመስበር ብቃታቸው ይታወቃሉ።

ፕሮፌሰር ኬቲ ዓሳ ነባሪዎቹ መኖሪያቸውን ከበረዶ ግግር በታች ማድረጋቸው በስፋት እንዳይጠኑ አግዷል ትላለች። "ስለ ዝርያቸው የምናውቀው ጥቂት ነው" ስትልም የጥናቱን ክፍተት ታስረዳለች።

የዓሳ ነባሪዎቹን ቁጥር በትክክል ማወቅ ባይቻልም 343 ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።

የጥናቱ ቀጣይ ክፍል የሚሆነው የትኛው ዓሳ ነባሪ ምን አይነት ድምጽ ለምን እንደሚያወጣ መመራመር ይሆናል።

ተያያዥ ርዕሶች