የደፈራት ባሏን የገደለችው ሱዳናዊት ሞት ተፈረደባት

ሱዳናዊት ልጃገረድ Image copyright Getty Images

የደፈራትን ባሏን የገደለችው ሱዳናዊት ላይ ሀሙስ የዋለው ችሎት ሞት ፈርዶባታል።

በኦምዱርማን የሚገኙት ዳኛ በኑራ ሁሴን ላይ የሞት ቅጣቱን የጣሉባት የባሏ ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳውን ውድቅ ካደረጉ በኋላ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፍርዱ እንዲቀለበስ ጠይቀዋል።

በ16 ዓመቷ ተገዳ ለትዳር የበቃችው ኑራ ለሦስት ዓመታትም ለማምለጥ ሙከራ አድርጋለች።

ትምህርቷን ጨርሳ መምህር የመሆን ህልም ነበራት።

ጉዳይዋም በመላው ዓለም የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን በትዊተር ድረ-ገፅም ፍትህ ለኑራ በሚልም ሰዎች ዜናውን እየተቀባበሉት ነው።

ግድያው እንዴት ተፈጠረ?

ኑራ አምልጣ አክስቷ ቤት ተጠግታ ትኖር የነበረ ሲሆን ከሦስት ዓመት በኋላም በቤተሰቦቿ ተታልላ ወደ ባሏ እንድትመለስ ተደርጋለች።

ከተመለሰች ከስድስት ቀናት በኋላም የባሏ አጎት ልጆች ጠፍረው ይዘዋት ባልየው እንዲደፍራት ተባብረዋል።

በተከታዩ ቀንም ይህንንኑ ተግባር ሊፈፅም ባለበት ወቅት ቢላ በማውጣት እስኪሞት ወግታዋለች።

አምልጣም ወደ ቤተሰቦቿ ብትሮጥም እነሱ ግን ለፖሊስ አሳልፈው ሰጥተዋታል።

የሸሪዓ ፍርድ ቤቱም ባለፈው ወር በመርፌ ተወግታ እንድትገደል ውሳኔ ቢሰጥም ሀሙስ ዕለት በዋለው ችሎት በስቅላት እንድትቀጣ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

ጠበቃዎቿም ይግባኝ ለማለት 15 ቀናት ብቻ እንዳላቸው ተገልጿል።

"በሸሪዓ ህግ መሰረት የባሏ ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳን ወይም ደግሞ ሞት መጠየቅ ይችላሉ" በማለት የአፍሪካ ወጣቶች እንቅስቃሴ አባል የሆነው የመብት ተሟጋች ባድር ኤልዲን ሳላህ በፍርድ ቤቱ ለተገኘው ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግሯል።

በተጨማሪም "ሞትን ነው የመረጡት፤ የሞት ቅጣቱም ተሰጥቷቸዋል" ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ምን አሉ?

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲቀለበስ እየሰሩ ካሉት መካከል "ኢኳሊቲ ናው" (አሁን እኩልነት) ከተሰኘው ድርጅት የመጣችው ያስሚን ኃሰን ውሳኔው እንዳላስደነቃት ተናግራለች።

"ሱዳን አባታዊ ሥርዓት እንዲሁም የወንድ የበላይነት የሰፈነበት ሀገር ነው። እንደዚህ ዓይነት ባህሎችም ማህበረሰቡ ውስጥ ጠልቀው የሰረፁ ናቸው" በማለት ተናግራለች።

"የ10 ዓመት ህፃናት ሴት ልጆችን ለጋብቻ የሚያስገድድ ባህል ነው። ወንዶች ለሴቶች ጠባቂ የመሆን ሕጋዊ መብት አላቸው" ብላለች።

"ኑራን በተመለከተ ደፋር ልጅ ናት። ትምህርቷን ከሁሉ በላይ በማስቀደም በዓለም ላይ ጥሩ ነገሮችን መስራት የምትፈልግ ልጅ ናት። የሚያሳዝነው በማይሆን ወጥመድ ውስጥ ተተብትባ የሥርዓቱ ሰለባ ሆናለች" ብላለች።

በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚሰራው ዓለም አቀፉ ድርጅት አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ራሷን ለመከላከል ደፋሪዋን ገደለች ብሎ በሞት መቅጣት ማለት ባለሥልጣናቱ የህፃናት ጋብቻን፣ ጠለፋን እንዲሁም በጋብቻ ላይ ያለ መደፈር ላይ ያላቸውን ጉድለት ማሳያ እነደሆነ ገልጿል።

"ኑራ ሁሴን የሥርዓቱ ተጠቂ ናት፤ በእሷ ላይ የተወሰነውም ውሳኔ ከፍተኛ ጭካኔ ነው" በማለት የአምነስቲው ተወካይ ሴይፍ ማጋንጎ ገልፀዋል።

"የሱዳን ባለስልጣናት ፍርደ-ገምድል የሆነውን ውሳኔ በማስተካከል ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ፍትሀዊ ውሳኔ ሊወስኑ ይገባል" ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች