“የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ደመወዝ ለመክፈል አይበደርም”

የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች በገበያ ላይ Image copyright ZACHARIAS ABUBEKER

በፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ በቅርቡ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ባወጣው የአፍሪካ ሃገራት ምጣኔ ሃብታዊ ዘገባ ላይ የእዳ መጠኗ ከፍተኛ እንደሆነ አትቷል።

ኢትዮጵያም የእዳ ጫናዋ መጠን ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርቷ 56.2 በመቶ ድርሻ እንደሆነ ተጠቅሶ ከአገራቱ ተርታ ተመድባለች ።

ምንም እንኳን ተቋሙ ብድሩ አስጊ ደረጃ ላይ እንደሆነ ቢገልፅም በተቃራኒው ብድር እንደ ችግር ሊታይ አይገባም የሚሉት የግብርናና ምጣኔ ሐብት ባለሙያ ዶክተር ደምስ ጫንያለው እንደ ምሳሌነት የሚጠቅሱትም በብድር የምትመራው አሜሪካ መሆኗን ይጠቅሳሉ።

"ብድር መውሰድ የሚያስገርም ነገር አይደለም። ማንኛውም እድገት ከመበደር በነፃ እንቅስቃሴ አይደለም። ዋናው ጥያቄ ለምን ተግባር ይውላል የሚለው ነው" ይላሉ።

"የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ደመወዝ ለመክፈል አይበደርም" ይላሉ ባለሙያው።

ኢትዮጵያ ብድር የምትበደረው ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ደምስ አይኤም ኤፍና የዓለም ባንክ የመሳሰሉ ተቋማት ለአገሪቱ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ብድር እንደማይሰጡም ይገልፃሉ።

"የመንገድ ሥራዎች ለመስራት፣ ግድቦችን ለመገንባት፣ ለመብራት መስፋፋት፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ፣ ለባቡር መስምረ ዝርጋታ እና ለመሳሰሉት ኢትዮጵያ ብድር የምትወስደው ከቻይናና ከህንድ ነው" ይላሉ።

አንድ የብድር መጠን ሊነፃፀር የሚገባው ከመክፈል አቅም ጋር ነው። ብድሩን ተጠቅሞ ገቢ ማግኘትና በወቅቱ መክፈል እስከተቻለ ድረስ ሪፖርቱ እንደሚለው የሚረብሽ ነገር የለውም።

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን ተበደረ የሚል አቋም የላቸውም።

በዚህ ዓመት ለአንዳንድ ላልተጠበቀ የዋጋ ግሽበት ምክንያቱ በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው የኢትዮጵያ መገበያያ የሆነው ብር ከዶላር ጋር ያለው አቅም እንዲቀንስ መደረጉ ሲሆን ይህም በእነዚህ ድርጅቶች ጫና መሆኑን ዶክተር ደምስ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ አሁንም የዋጋ ጭማሪው ምክንያታዊ ባለመሆኑ ነዋሪዎች ያማርራሉ።

"በመሰረታዊ የምግብ ፍጆታችን ላይ የዋጋ ጭማሪ አለ። ችግሩ ከባለፈውም ወር የባሰ ነው። እያንዳንዱ ነገር ላይ ከአራት ብር እስከ ስድስት ብር የዋጋ ጭማሪ አለው። በግንባታ ጥሬ እቃዎችም ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሬ በመኖሩ ኑሯችንን ፈታኝ አድርጎታል" በማለት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰብለ እሸቴ ይናገራሉ።

የውጭ ምንዛሬው ማሻሻያ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተገቢ እንዳልነበረም ዶክተር ደምስ ይናገራሉ።

"ውሳኔው ያልተጠበቀ የዋጋ ግሽበት ጭማሪዎችን እንደሚያስከትል ቀድሞ በመረዳት መንግሥት መጠንቀቅ የነበረበት ቢሆንም አሁንም የሚስተካከልበትን መንገድ እንደሚጠብቁ" ይናገራሉ።

የአይ አም ኤፍ ሪፖርት ጨምሮም ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሠረታዊ ፍጆታ የሚውሉ እቃዎች ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ መጥቷል።

"ሪፖርቱ ከመውጣቱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና ብሄራዊ ባንክ ይህንን አሃዝ ያውቁታል ። ተቋሙ መረጃውን ከእነርሱ ወስዶ ነው የሚያወጣው፤ነገር ግን ይሄንን እንዴት እንቆጣጠረዋለን የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።" ይላሉ።

ሌሎች የክትትልና የቁጥጥር መንገዶች ካሉ መፈተሽ ይገባልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቢሆንም ግን በአገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትም ሌላኛው አማራጭ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሚፈለገው መጠን እንዲገቡና ከገቡ በኋላ አገር ውስጥ ካለው ዋጋ ትርፍ አንፃር የሚሸጥበትን ዋጋ መለየት ያስፈልጋል ሲሉም ያስረዳሉ ።

ከዚህ በተጨማሪም ያለውን ክፍትት በመጠቀም ከዋጋው በላይ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ስላሉ የሚገቡ ምርቶች፣ ከውጭ በድጎማ የሚገቡ ግብዓቶችንና በአገር ውስጥ የምርት ውጤቶችን በመከታተልና በመቆጣጠር መስራት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።

በተለያዩ ደረጃ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ይህንን በማከናወን ላይ ናቸው ሲሉ ሃሳባቸውን ያሳርጋሉ።