5 ሺህ ጉርሻዎች!

የኢትዮጵያ ምግብ

ነገሩ የተለመደ የሙዚቃ ድግስ ነው። ልዩ የሚያደርገው በማጀቢያ ሙዚቃ 5ሺህ ሰዎች ሊጎራረሱ መሆኑ ነው።

ኩነቱን ማሰብ በራሱ ያስቃል።

5ሺህ እንጀራን የጠቀለሉ መዳፎች ወደ 5ሺህ የተከፈቱ አፎች ሲምዘገዘጉ ማሰብ በራሱ ትን ያስብላል...!

የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 4 በጊዮን ሆቴል ነው ይህ እንዲሆን ቀጠሮ የተያዘው።

አሰናጆቹ ክስተቱን ከአንድ ቀን የዘለለ ትርጉም እንዲኖረው ጽኑ ፍላጎት አላቸው።

ለምሳሌ ቋሚ የጉርሻ ቀን መሰየም ይፈልጋሉ። በኢትዮጰያ የማይቋረጥ ዓመታዊ የመጎራረስ ፌስቲቫል እንዲኖር ያልማሉ። ከፍ ሲልም ጉርሻን በማይዳሰስ ቅርስነት የማስመዝገብ የረዥም ጊዜ ትልምን ሰንቀዋል። "ጉርሻ ግን አይዳሰስም እንዴ!?" ብሎ መጠየቅ የተሰነዘረ ጉርሻን ያስከለክል ይሆን?

አዘጋጆቹ የጉርሻ ባሕል በኢትዮጵያ አራት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው ሲሉም ይከራከራሉ።

አንድ የሚያደርገንን ፌስቲቫል ፍለጋ

ኢትዮጵያ ውስጥ ኮስተር ብሎ የሚቆጥር ካለ እያንዳንዱ ቀን በዓል ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ይህ በቋንቋና በባሕል ሀብታም የሆነ አገር ሁሉ ባህሪ ነው።

"እንደ ጉርሻ ግን የሚያግባባን የለም" ይላል ቅዱስ።

"...ጉርሻ እኮ አንዱ ለሌላው የማጉረስ ተግባር ብቻ አይደለም፤ በተጠቀለለው እንጀራ ውስጥ ፍቅር አለ፣ መተሳሰብ አለ፣ አክብሮት አለ...።" ይላል ከአሰናጆቹ ፊታውራሪው ቅዱስ አብረሃም።

ሐሳቡ እንዴት እንደተጠነሰሰ ሲያብራራም የሌሎች አገሮችን ዕውቅ ፌስቲቫሎች ከመመልከት የመጣ "መንፈሳዊ ቅናት የወለደው ነው" ይላል።

"ሕንዶች የቀለም፣ ስፔኖች የቲማቲም፣ ጀርመኖች የቢራ ፌስቲቫል አላቸው። እኛ ግን አውዳመት እንጂ የሚያምነሸንሽ አንድም የጋራ ፌስቲቫል የለንም።"

ሐሳቡን ያመነጩት የሥራ አጋሩ አቶ ዘላለም እናውጋው መሆናቸውን ጨምሮ ያስገነዝብና እንዴት አንድ ቀላል የጉርሻ ተግባር አገርን ወደ አንድነት መንፈስ ሊመራ እንደሚችል ማስረዳቱን ይቀጥላል።

"ጉርሻ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት አልያም የገቢ መጠንን አይጠይቅም። ሁላችንንም የሚያግባባን ባሕል ነው፤ ለዚህ ነው ልዩ የሚያደርገው። ደግሞም የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን አንጡራ ባህል እንጂ የማንም አይደለም" ይላሉ ቅዱስ።

ለዚህ የጉርሻ አገራዊ ፌሽታ ባሕል ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድጋፍ ማድረጋቸውን አሰናጆቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንግሊዝ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደብዳቤ በመጻፍ የጊነስ የድንቃ ድንቅ መዝገብ ዋና ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን እንዲከታተለው ማድረጉን ቅዱስ አብራርቷል።

ጊነስ እና ጉርሻ

ጊነስ እንዲህ ዓይነቶቹን ኩነቶች በማኅደሩ ለማስፈር ከ 7ሺህ እስከ 22ሺህ ፓውንድ ይጠይቃል። እነ ዘላለም ይህን ሂደት በማጠናቀቅ ላይ ነበሩ።

ሁለት የጊነስ የድንቃ ድንቅ መዝገብ ቢሮ ተወካዮች ይህንን የ5ሺህ ሰዎች ጉርሻ ለመታዘብ በቀጣይ ቀናት አዲስ አበባ እንደሚገቡም ይጠበቅ ነበር። ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ጉዟቸው እክል ሳይገጥመው አልቀረም።

"የድጋፍ ደብዳቤዎችን በመላክ ልናሳምናቸው ሞክረን ነበር" ይላል ዘላለም። ሆኖም መልካም ፍቃዳቸው አልሆነም። ይህ ማለት ግን ጊነስ ኩነቱን አይመዘግበውም ማለት እንዳልሆነ ጨምሮ ያብራራል።

"አማራጭ አሠራር አለ። ይኸውም ገለልተኛ ተቋም ቀጥሮ፣ ለ50 ጥንዶች በቡድን አንድ-አንድ ታዛቢ በመመደብ፣ ክስተቱን ያለማቋረጥ በቪዲዮ ቀርጾ በጊነስ መዝገብ ይፋዊ ድረ-ገጽ በማኖር ለዕውቅና ሰርተፍኬት ማመልከት ይቻላል። ይህን ካሟላን ዕውቅናው እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል" ይላል ዘላለም።

የጉርሻ ታዛቢዎች ነገር እንግዳ ነው።

50 ሰዎች ሲጎራረሱ ከፊት ለፊት ቆመው እያንዳንዷን ጉርሻ ይቆጣጠራሉ። ልክ የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ እንደሚቆጣጠር የእግር ኳስ አራጋቢ ዳኛ፤ ከወዳጅ የተቀባበለው ጉርሻ የተቃራኒ ቡድኑን የአፍ መስመር ማለፍ አለማለፏን ይከታተላሉ። ሂደቱ በራሱ የሚያዝናና ይመስላል።

የጉርሻ ክብረወሰን በማን ነው የተያዘው?

"ክብረ ወሰኑ ጃፓኖች ጋር ነው ያለው። 850 ጥንዶች ተጎራርሰው የዓለም ክብረ ወሰንን ይዘውታል። እኛ ይህን ክብረወሰን በዕለቱ በቀላሉ እንሰብረዋለን" ይላል ሌላኛው የኩነቱ አሰናጅ ቅዱስ አብረሃም በሙሉ መተማመን።

እርሱ ራሱ ክብረ ወሰኑ በጃፓኖች ስለመያዙ ለመጀመርያ ጊዜ የሰማው ግን ከጊነስ ሰዎች ነው።

"ይሄ የኛና የኤርትራዊያን ባሕል ነው። እንዴት ጃፓኖች ጋ እንደሄደ አልገባኝም። በ"ስቲክ" ይሁን በእጅ እንዴት እንደተጎራረሱ ራሱ አላውቅም፤ ጊነሶች ናቸው የነገሩኝ" ይላል ቅዱስ፤ ግርምት ከወለደው ፈገግታ ጋር።

የጾም ነው የፍስክ?

ሙዚቃውን፣ ምግቡን፣ ቀኑን፣ ሰዓቱን በጥንቃቄ ስለመምረጣቸው አዘጋጆቹ ደጋግመው ያስገነዝባሉ።

ለምሳሌ በዕለቱ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ጾም እንደማይኖር ማረጋገጣቸውን ይጠቅሳሉ።

"የረመዳን ጾም ከመግባቱ ቀደም ብሎ ፌስቲቫሉን ያደረገውን ለዚህ ነው" ይላል ቅዱስ።

የሸራተን እህት ኩባንያ የሆነው አዲስ ኬተሪንግ ለጉርሻ የሚቀርበውን ምግብ በመከሸን በአጋርነት እንደተሰለፈና ጥብስ፣ ምንቸት፣ ጥብስ ዝልዝል ከምግብ መዘርዝሩ ከፊት የሚሰለፉ የምግብ ዓይነቶች እንደሚሆኑ ተነግሯል።

በፊሽካ ነው በደወል?

ተጎራረሱ! የሚለው ይፋ መልዕክት የሚተላለፈው እንዴት ነው?

ቅዱስ እንደሚለው መድረኩ ላይ የሚሰቀል ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ ግዙፍ ሰዓት አለ። ይህ የጉርሻ ሰዓት ልክ 11፡30 ከመሙላቱ በፊት ከላይ ወደ ታች መቁጠር ይጀምራል። '00:00' ሲል አምስት ሺህ ክንዶች ወደ ተከፈቱ አፎች ይወረወራሉ።

ምግቡን ማወራረጃ የነዘሪቱ፣ የነ አቤል ሙሉጌታ፣ የነኃይሌ ሩትስ ሙዚቃ ተዘጋጅቷል።

ተቃዋሚዎችና መንግሥት ቢጎራረሱስ?

"ጉርሻ የፍቅር፣ የእርቅ፣ የአክብሮት፣ የህሊና ትስስርና የሞራል ልዕልናን በእንጀራ ጠቅልሎ የያዘ ስለመሆኑ ደጋግመው የሚናገሩት የዝግጅቱ አስተባባሪዎች በዕለቱ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተቃዋሚዎች ተገኝተው ቢጎራረሱ፣ ቢዝናኑ፣ ፍቅር ቢለዋወጡ ደስታንን አንችለውም'' ይላሉ።

ለመሆኑ ጉርሻ የማይዳሰስ ቅርስ መሆን ይችላል? ትን የሚያስብል ጥያቄ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች