በፀሐይ የሚሰራው የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባ

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት
አጭር የምስል መግለጫ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት

አካባቢን ሳይበክሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዴት መስጠት ይቻላል? ኢኳዶር ውስጥ ተገልለው የሚኖሩት የአኩአር ነባር ሕዝቦች ሃገር በቀል መፍትሄ አላቸው።

ከሚያዝያ 2017 በጀምሮ በፀሃይ ብርሃን ብቻ የምትንቀሳቀሰው አነስተኛ ጀልባ ከካፓሁኣሪ አስከ 67 ኪሎሜትር የሚረዝመው ፓስታዛ ወንዝ ድረስ በመመላለስ ራሳቸውን አግልለው የሚኖሩትን 9 የአካባዊው ሰፈራዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ታገናኛለች።

በአካባቢው በአፈ ታሪክ በሚታወቀው ኤሌክትሪክ አመንጪ ዓሳ ስም በመነሳት ታፒያትፒያ ተብላ የተሰየመችው ጀልባ ለአማዞን ጫካ የመጀመሪያዋ በፀሃይ የምትሰራ የትራንስፖርት አማራጭ ሆናለች።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በናፍጣ የሚሰሩ ጀልባዎችን ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን፤ ናፍጣ በጣም ውድ ስለሆነ ጀልባዎቹ ያሏቸው ቤተሰቦች ቁጥር ትንሽ ነበር።

የአዲሷን ጀልባ ግልጋሎት ለማግኘት 1 ዶላር ያስከፍላል። በናፍጣ የሚሰሩት ጀልባዎች ግን ከ 5 እስከ 10 ዶላር ነበር የሚያስከፍሉት። ዋጋው አምስት እጥፍ የሆነበት ምክንያት በአካባቢው የመኪና መንገድ ባለመኖሩ ናፍጣው በትንንሽ አውሮፕላኖች ተጭኖ ስለሚመጣ ነው።

የዚህች ጀልባ አገልግሎት መጀመር በዓለማችን በብዝሃ ህይወት ሃብት ትልቁን ቦታ ለሚይዘው የአማዞን ጫካ ትልቅ ፋይዳ አለው።

32 የፀሃይ ብርሃን ኃይል መቀበያዎች በጣራዋ ላይ የያዘችው ጀልባ በአንድ ጊዜ እስከ 18 ተሳፋሪዎችን መሸከም ትችላለች።

የአካባቢው ሽማግሌ እና የጀልባዋ ተቆጣጣሪ ሂላሪዮ ሳንት ይህች አዲስ ግኝት የአካባቢውን ሰዎች ህይወት እየቀየረች ነው ይላል።

የታመሙ ህጻናት ሲኖሩ በቀላሉ ወደ ህክምና መውሰድ ችለናል፤ ህጻናቱን ወደ ትምህርት ቤት ማመላስም ሌላው የጀልባዋ ዋነኛ ሥራ ነው ሲል ያክላል ሂላሪዮ።

በሌላ በኩል ጀልባዋ ምንም አይነት ድምጽ ስለማታወጣ በአካባቢው ያሉ እንሰሳት ያለ ምንም መረበሽ ይንቀሳቀሳሉ። በተለይ ደግሞ የአካባቢው ብርቅዬ እንስሳ የሆኑት ባለ ሮዝ ቀለሞቹ የወንዝ ውስጥ ዶልፊኖችን እንደልብ ማየት ይቻላል።

ሁሊያን ኢሌንስ በኢኳዶር የአኩዋር ህዝቦች ግዛት መሪ ነው፤ እሱም ቢሆን የጀልባዋ ጥቅም ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል።

እነዚህ ህዝቦች በጎረቤት ሃገር ፔሩ ድንበር ላይ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ለዘመናት የቆየ የድንበር ይገባኛል ግጭት አላቸው። የዚህች ጀልባ መምጣት ደግሞ የነዚህን ተቀናቃኝ ህዝቦች ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ወደ ንግድ እና ትብብር ትቀይረዋለች ተብሎ ይታሰባል።

ጀልባዋን በመጠቀም ከእኛ አካባቢ ሙዝ፣ ዶሮ እና ጥራጥሬዎች ይዘንላቸው መሄድ እንችላለን። እነሱ ደግሞ የተለያዩ አልባሳት እና የጎማ ተክል ይሸጡልናል ይላል ሁሊያን።

አጭር የምስል መግለጫ ጀልባዋ በወንዝ ዳር ቆማ

የአኩዋር ህዝቦች እነማን ናቸው?

በአማዞን ጫካ ውስጥ በኢኳዶር እና ፔሩ ድንበር መካከል የሚኖሩ፤ 19ሺህ አባላት ያሉዋቸው ሕዝቦች ናቸው።

ባህላቸው በህልሞች እና ራዕዮች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ የሚኖሩበት ጫካ ደግሞ የራሱ መንፈስ አለው ብለው ያምናሉ።

ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ህይወታቸውን ይመሩ የነበሩ ሲሆን በ1940ዎቹ ከክርስትና መምጣት በኋላ ግን ተሰባስበው በመንደር መኖር ጀምረዋል። በአሁኑ ሰዓት በአደን፣ ዓሳ በማጥመድ እና በቀላል ግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

እነዚህ ነዋሪዎች ከሰለጠነው ዓለም በጣም ርቀው ስለሚኖሩ የድሮውን የኑሮ ዘይቤ እስካሁን ማስቀጠል የቻሉ ሕዝቦች ናቸው።

በኢኳዶር እና ፔሩ ከመንገዶች መገንባት ጋር ተያይዞ ስልጣኔ እየገባ ሲሆን፤ የነዳጅ ዘይት ፍለጋውም አብሮ መጥቷል። ይህ ደግሞ ጫካውን ለጭፍጨፋ እያጋለጠው ነው።

የኢኳዶር መንግሥት ግን የመንገዱ ግንባታ ለአኩዋር ህዝቦች የተሻለ የጤና አገልግሎት እና ትምህርት ለማቅረብ ይረዳል ሲል ይከራከራል። በሌላ በኩል በፀሃይ የምትሰራዋ ጀልባ ደግሞ እነዚህን ነገሮች ሁሉ አካባቢው ተፈጥሮውን ሳይለቅ ማከናወን እንደሚቻል እያሳየች ነው።

ተያያዥ ርዕሶች