በሱዳን እስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ

Image copyright Addisu Arega Facebook

በሱዳን እስር ላይ የነበሩ 1400 ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ።

እስረኞቹ የተለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ጉብኝታቸው ወቅት ለፕሬዚዳንት ኦማር ሀሳን አልበሽር ጥያቄያቸውን ባቀረቡት መሰረት እንደሆነ የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘገቡ።

የጠ/ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጥያቄ የተቀበሉት ፕሬዝዳንት አልበሽርም በሱዳን የታሰሩ ኢትዮጵያን እንዲፈቱ ማዘዛቸው ተገልጿል።

ከሁለት አመታት በፊት በሱዳን ተገኝቶ ኢትዮጵያዊያን እስረኞችን የሚመለከት ዘገባ በመስራት ጉዳዩን ከብዙዎች ጆሮ ያደረሰው ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው እስረኞቹ የነበሩበት ሁኔታ አስከፊ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከካርቱም 12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ ያለው እና በሱዳን ትልቁ የሚባለው ኤል ሁዳ እስር ቤት ተገኝቼ ነበር የሚለው ጋዜጠኛ አንተነህ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን እዚያ እንደሚገኙ ሰምቶ መሄዱን ይናገራል።

በወቅቱ ኢትዮጵያውያኑ የነበሩበት ሁኔታ ለመቋቋም የሚከብድ እና እስር ቤቱም በረሃ ላይ የተሰራ በመሆኑ ሙቀቱ እስከ 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርስ እንደነበር ያስታውሳል።

በእስር ቤቱ የሚጠጣው ውሃ ጨዋማ በመሆኑ አብዛኛዎቹ በኩላሊት በሽታ እየተጠቁ እንደነበር ፤ የታሰሩበት ክፍል በጣም ጠባብ በመሆኑ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንደተጋለጡ እስረኞቹ እንደነገሩትም ይገልፃል።

የሃገሩን መግባቢያ ቋንቋ መናገር ስለማይችሉም ባልሰሩት ወንጀል እስከ 20 አመት የታሰሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም ይናገራል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ቀናት በፊት የተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኬንያ ጉብኝትን ተከትሎ በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑም ተገልጿል።

በኬንያ የኢትዮጰያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በተደረሰው ስምምነት መሰረት በተለያዩ የኬንያ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

''የእያንዳንዱ እስረኛ መረጃ፤ ማለትም የት እንደታሰሩ እና ለምን እንደታሰሩ በአግባቡ ከተጠናቀረ በሁዋላ ምናልባትም በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ እስረኞቹ ሊለቀቁ ይችላሉ'' ብለዋል አምባሳደሩ።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተለያዩ የኬንያ እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ 69 ኢትዮጵያውያን ተፈተው ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

እስረኞቹ ምን ያህል ይሆናሉ የሚለው በውል ባይታወቅም የኬንያ መንግስት አጣርቶ በቅርቡ እስከሚያሳውቅ እየተጠባበቁ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።።