የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ጦስ በሶማሊያ?

Image copyright STRINGER
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል በሶማሊያ

የዛሬ 20 ዓመት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረገው ጦርነት የተደመደመው በ1993 ዓ.ም ነበር። ሀገራቱ ሰላምም እርቅም በሌለበት ፍጥጫ ቢዘልቁም ቅሉ፤ ባለፉት 18 ዓመታት ዳግም ነፍጥ አንስተው የተጋጩበት ጊዜ በቁጥር አነስተኛ ነው።

ሊረግብ ያልቻለው የሁለቱ ሀገራት ውጥረት ከራሳቸው አልፎ የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሶማሊያ ላይ ዘላቂና ስር የሰደደ ተጽዕኖን አሳርፏል።

በ1983 ዓ.ም የሲያድ ባሬ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በአገሪቱ ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖች በየቦታው ተፈጠሩ።

ሱሌማን ሁሴን መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ኤርትራዊ የለውጥ አራማጅና ቀጠናዊ ጉዳዮች ተንታኝ ነው። እንደ እርሱ ዕምነት ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1980ዎቹ ሶማሊያ ውስጥ አወንታዊ ሚና መጫወት ይችሉ ነበር።

ሁለቱ ሀገራት በዚያን ወቅት (ደርግን ካስወገዱ በኋላ) እጅግ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነበራቸው። ሀገራቱ በሶማሊያ ዳግም ሰላም ለማምጣት የወሰዷቸው የተወሰኑ እርምጃዎችም ስኬት እያሳዩ ነበር፤ ሆኖም "የድንበር ይገባኛል" ጦርነቱ ነገሮችን ወደ መጥፎ ቀይሯቸዋል ሲል ይላል።

"የውክልና" ጦርነት

የአዲስ አበባ እና አስመራ መንግሥታት በጋራ ድንበሮቻቸው ጉዳይ የተፈጠረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የደመደሙት በ1993 ዓ.ም ነበር። ሆኖም ደም የሚያደርቅ፣ ወትሮ የነበረውን የሀገራቱን መልካም ግንኙነት የሚመልስ ስምምነት ላይ መደረስ ተስኗቸዋል፡፡

ይልቁንም በሶማሊያ ውስጥ ከሚፋለሙ ኃይሎች ጀርባ በመሰለፍ፣ ሶማሊያን የእጅ አዙር ጦርነት አውድማ (መሳሪያ) ማድረግን መርጠዋል የሚለው ደግሞ የኢትዮጵያ የደህንነት ተንታኝና የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬምብሪጅ የዶክትሬት ዕጩው ጎይቶም ገብረ-ልዑል ምልከታ ነው፡፡

ጎይቶም የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጣልቃ ገብነት የሶማሊያን ሁኔታ እንዴት ወደ ገዘፈ እና እጅግ ውስብስብ ግጭት እንደለወጠው ሲያብራራ፤ "ሶማሊያ ውስጥ ሁለት አይነት ትግሎች ነበሩ እነሱም አካባቢያዊ እና ክልላዊ ናቸው። ሁለቱም እርስ በርስ ተደጋጋፊ ናቸው። ቀድሞውኑ የሶማሊያ ግጭት በሶማሌዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ነው፤ ሆኖም በባዕዳን ተዋናዮች ተሳትፎ ምክንያት ወደ የውክልና ጦርነት አደገ" ይላል።

የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት መቀመጫውን ሞቃዲሾ ያደረገው የሽግግር መንግሥቱ ባላንጣ ቡድን ነበር። እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ይሄ ቡድን አብዛኛውን የሀገሪቱን ደቡባዊ ክፍል ተቆጣጥሮ እንደነበርም ይታወሳል።

በዚያው ዓመትም ኢትዮጵያ ጣልቃ መግባቷን ተከትሎ ነገሮች መልካቸውን መቀየር ጀመሩ። ኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥቱን ለማገዝ የኋላ ኋላም አልሸባብ ወደተባለው ሸማቂ ቡድን የተቀየረውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ሸማቂ ቡድንን ለማፈራረስ ጦሯን አዘመተች። ኤርትራ በበኩሏ ሌላኛውን ወገን መደገፍ እንደያዘች ይነገራል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ እና ሶማሊያ አጣሪ ቡድን በ 2001 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ላይ፤ ኤርትራ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት የተሰኘውን ቡድን እንደምትረዳ "ደርሼበታለሁ" ሲል ይፋ አድርጓል። የኤርትራ መንግሥት ውንጀላውን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጎታል።

ምንም እንኳን አልሸባብ የቀጠናው ስጋት መሆኑ ቢቀጥልም፤ ይኸው ቡድን ኅዳር 2010 ላይ ኤርትራ አሁን ድረስ አልሸባብን መርዳት መቀጠሏን የሚያሳይ መረጃ እንዳላገኘ ይፋ አድርጓል።

የቀጠናው ራስ ምታት

በጎይቶም ዕምነት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግጭት ወደ ሶማሊያ እና ሌሎች ቦታዎች በእጅ አዙር መዛመቱ ‹‹የቀጠናው እጅግ ትልቁ ያለመረጋጋት ምንጭ›› ሆኖ ቀጥሏል።

‹‹በቀዳሚነት በኤርትራ፣ ሶማሊያ በተወሰነ መጠን ደግሞ በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴዎችን አጨናግፏል።››

ተንታኙ አክለው፤ የኦጋዴንን ግዛት ከአትዮጵያ ለመገንጠል ጠመንጃ የጨበጠው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) የሚንቀሳቀስበት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላም አጥቶ እንዲሰነብት ግጭቱ የነበረውን አስተዋጽኦን ጠቅሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ቡድን በ2007 ዓ.ም ሪፖርቱ ኤርትራ የውሳኔ ረቂቅ 1907ን በመጣስ ለኦብነግ የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች ሲል ደምድሟል።

የምር ሰላም ወዴት አለ?

ብዙሃን እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለልዩነታቸው እልባት አግኝተው ፣ብዙ ዓመታት ያስቆጠረውን ቀዝቃዛ ጦርነት እስካልቋጩት ድረስ ቀጠናው የምር ሰላም አያገኝም፡፡

‹‹ሰላም በሁለቱ መካካል ቢያብብ፣ በመላው ቀጠና የሚመጣው መረጋጋት ፈጣን አወንታዊ ተጽዕኖ ያመጣል›› ይላሉ ሱሌማን ሁሴን።

በተቃራኒው ‹‹ሀገራቱ ላለፉት 20 ዓመታት እንዳደረጉት በፍጥጫ የሚዘልቁ ከሆነ፣ ከሌሎች ስፍራዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ወቅት ካለምንም ጥርጣሬ ተቃራኒ ጫፎችን የሙጥኝ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡››

አብዱልራህማን ሰኢድ በእንግሊዝ ሀገር ኬንት ዩኒቨርሲቲ የግጭት አፈታት ትምህርት ያጠኑ ኤርትራዊ ተንታኝ ናቸው።

በአብዱልራህማን ዕምነት ኢትዮጵያ ኤርትራ እንድትገለልና በኤርትራ የሚታገዙ ታጣቂ ቡድኖችን በማዳከም ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች።

‹‹ከሶማሊያ በኩል ካየን ሀገሪቱ ከመንግሥት አልባነት ወደ ጥገኛ ሀገርነት እየተሸጋገረች ነው።›› በማለት አብዱልራህማን ይቀጥላሉ ‹‹እርግጡን ለመናገር የሶማሊያ አስተዳዳር የአዲስ አበባ እና የናይሮቢ መንግሥታት በዘዴ የሚቆጣጠሩት አካል ነው።››

የቢቢሲ አፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ቶሚ ኦላዲፖ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ከሰላም ማስከበር ያለፈ ተጨማሪ ሚና እየተጫወተች እንደሆነ ያምናል።

‹‹ኢትዮጵያ አልሸባብን ሶማሊያ ውስጥ ወደ መከተችበት ጊዜ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል›› የሚለው ኦላዲፖ፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ በጂሃዲስቶች ዘንድ ተፅዕኖ ትፈጥራለች በሚል በወቅቱ ማሰቧ አልረቀም ‹‹ስለዚያም ነው ወታደሮቿን ከሶማሊያ ግዛት ሳታስወጣ ለዓመታት እንዲቆዩ ያደረገችው›› ሲል ያክላል።

በሌላ በኩል ኤርትራ ቢያንስ በይፋ ሶማሊያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ምንም እያደረገች አለመሆኑን ዘጋቢው ያነሳል።

እርቅም ጠብም የሌለበት ፍጥጫ አሁንም ቀጥሏል። ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ ጥቃት ለመፈፀም የሚያበቃ ‹አቅምም ሆነ ፍላጎት አላት!› ብላ እንደምታስብ ኦላዲፖ ይናገራል።

‹‹የሶማሊያ መረጋጋት በኢትዮጵያ ላይም ውጤት አለው። ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ ሰላም ትሆን ዘንድ ማናቸውንም ነገር ታደርጋለች።››

ዕድገትን እያስመዘገበች እንደሆነ የሚነገርላት ወደብ አልባ ሀገር ኢትዮጵያ፤ በቅርቡ የሱዳን፣የጅቡቲ እና የሶማሌላንድ ወደቦች ላይ ያለመችውን ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ ተንቀሳቅሳለች።

ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ለኤርትራ ጥንካሬዋን ለማሳየት የተደረገ እርምጃ ነው። የወደብ ተጠቃሚነት ተረጋገጠ ማለት የኢትዮጵያ ጦር ወደ ባህር ቀጥተኛ መተላላፊያ አገኘ እንደ ማለት ነው።

‹‹ከኤርትራ ጋር ጦርነት የሚኖር (የሚታሰብ) ከሆነ፤ አሁን እያየነው ያለው አስቀድሞ የተገኘን ፈርጣማነት ማሳያ ዘዴ ነው። እርምጃው የራሱ መልዕክት ያለው ይመስለኛል›› ሲል ኦላዲፖ ያስረግጣል።

የሚያዛልቀው መንገድ

የአፍሪቃ ቀንድ ከመቼውም በላይ አለመረጋጋት አርብቦታል።

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ውጥንቅጥ፣ በአባይ ግድብ ሰበብ አጨቃጫቂ መንፈስ የተጠናወተው የኢትዮጵያና የግብጽ ግንኙነት፣ የየመን ውጥረት እና አብሮ የሚነሳው የኤርትራ ከሳውዲ እና የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ጋር መወገን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ መደፍረስ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው።

ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ወደ ሌላ ማማተሩን ገታ አድርጎ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የሚያሳትፍ የተሳካ ውጤት ለማምጣት ቢጥር ‹‹ወቅቱ የተመቸ ነው!›› ሲል ሱሌማን ሃሳብ ያቀርባል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት የአፍሪካ ረዳት ፀሃፊ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ከሰሞኑ ያልተለመደ የአስመራ ጉብኝት አድርገዋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ምናልባትም ለቀጠናው የተሻለ መረጋጋት ምንጭ የሚሆን፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተሻለ ግንኙነትን ይፈጥራሉ የሚል ተስፋም ተሰጥቷቸዋል።

የሶማሊያ ጉዳይ ውስብስብ ነው። የእንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ ውጥረት፣ ጎጠኝነት እና የመሳሰሉት ተንሰራፍተዋል። ‹‹ሆኖም ሶማሊያ የተገኘው ሁሉ እርዳታ ያስፈልጋታል›› የሚለው የቢቢሲው የአፍሪቃ ደህንነት ዘጋቢ ቶሚ ኦላዲፖ ‹‹ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካበሩ -ህብረታቸው በሶማሊያ ላይ አወንታዊ ውጤት ይኖረዋል› ሲል ያክላል።

ኤርትራም የውጪ ግንኙነቷን ካሻሻለች በሶማሊያ ጉዳይ ገንቢ ሚና መጫወት እንደምትችል የጠቆመው ዘጋቢው ‹‹ኤርትራ አሁንም ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ስር ስለሆነች መልካም የሆነ ገጽታ የላትም›› በማለት ያስገነዝባል።

‹‹በርካታ ሰዎች በኤርትራ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ያ ጥርጣሬ ከተነሳ ኤርትራም ሆነ ሶማሊያ ወደፊት እንዲራመዱ ያግዛቸዋል።››