የውድድር ዘመኑ ምርጥ 11

ሞሃመድ ሳላህ (ሊቨርፑል) Image copyright Michael Regan

ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከ10 ወራት ቆይታ በኋላ ሊጠናቀቅ ግድ ሆኗል። የፕሪሚዬር ሊጉን ምርጥ ተጫዋቾች በየሳምንቱ የሚመርጠው ጋርዝ ክሩክስ እነሆ የወድድር ዘመኑን ምርጥ አስራ አንድ ተጫዋቾች እኚህ ናቸው ይላል።

ወርሃ ነሐሴ ላይ የጀመረው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በማንችስተር ሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል። ዌስትብሮም፣ ስቶክና ስዋንሲ ደግሞ ከሊጉ ሲወርዱ፤ አርሴናል ደግሞ ከዌንገር ጋር የነበረው የ22 ዓመታት ቁርኝት ቋጭቷል።

እነዚህ ሁሉ እንዳሉ ሆነው የውድድር ዘመኑ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ መካተት የቻሉት ምርጥ 11 ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

ግብ ጠባቂ

ዳቪድ ዴ ሂያ (ማንቸስተር ዩናይትድ)

Image copyright AFP

ሆዜ ሞሪኖ ዴ ሂያ ወደ ሪያል ማድሪድ ከመሄድ ይልቅ ዩናይትድ እንዲቆይ ያሳመኑት ጊዜ ትልቅ ነገር እንደሰሩ እሙን ነበር።

ዴ ሂያ በዚህ የውድድር ዘመን ያሳየው ብቃት እጅግ ማራኪ ነበር። ምንም እንኳ ሞሪኖ ለዚህ ድንቅ በረኛ የሚመጥን ተከላካይ መስመር ሊሰሩ ባይችሉም።

ትዝ የሚላችሁ ከሆነ ሞሪኖ ከቼልሲ ጋር ዋንጫ ሲያነሱ ፒተር ቼክ በረኛ ነበር፤ ዊሊያም ጋላስ፣ ጆን ቴሪና ሪካርዶ ካርቫልሆ ደግሞ ተከላካዮች። ዴ ሂያ እነዚህን የመሳሰሉ ተከላካዮች ቢኖሩት ኖሮ ዩናይትድ ዋንጫ የማንሳት አቅም ነበረው።

ያም ሆነ ይህ ዴ ሂያ በ18 ጨዋታዎች ምንም ጎል ያልተቆጠረበት ግብ ጠባቂ ሆኖ የወርቅ ጓንቱን መውሰድ ችሏል።

ተከላካይ መስመር

ዎከር፣ ዳንክ፣ ኦታሜንዲ እና ያንግ

Image copyright BBC Sport

ካይል ዋከር (ማንቸስተር ሲቲ) - ፔፕ ጋርዲዮላ ዎከርን ከቶተንሃም በ50 ሚሊየን ዩሮ ሲገዛው ጥርጣሬ ገብቶኝ ነበር። ነገር ግን በመጀመሪያ ጨዋታው ያሳየውን ብቃት ስመለከት ሲቲዎች ለተጫዋቹ ያወጡት ወጭ የማያስቆጭ እንደሆነ ገባኝ። በምርጥ የመከላከል አቋም ላይ በመገኘት ቡድኑ ዋንጫ እንዲያነሳ ከማገዙም በላይ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም ሲያቀብል ነበር።

ሊዊ ዳንክ (ብራይተን) - ይህ ተጫዋች በቻምፒንሺፕ ደረጃ ሲጫወት ተመልክቸዋለሁ፤ በፕሪሚዬር ሊጉ ያየሁት ግን ፍፁም ሌላ ሆኖ ነው። የቶተንሃሙ ጆን ቬርቶኸንን መርጬ መገላገል እችል ነበር፤ ነገር ግን ብራይተብ ጥሩ ይሁንም አይሁን ዳንክ በዚህ ዓመታ ያሳየው ብቃት ያለምንም ጥርጥር ሊያስመርጠው ይገባል። 56 ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ጠራርጎ በማስወጣትም ከሁሉም የላቀ መሆኑን አሳይቷል።

ኒኮላስ ኦታሜንዲ (ማንቸስተር ሲቲ) - ይህ ልጅ አቋሙ የሚዋዥቅ ነበር፤ ነገር ግም በዚህ ዓመት ዘላቂ የሆነ ብቃት አሳይቶናል። ቨንሴንት ኮማፓኒ በተጎዳብት ሰዓትም እጅግ ወሳኝ ተጫዋች ሆኖ መገኘት ችሏል። አልፎም ከማንኛውም የሊጉ ተጫዋች በበለጠ ስኬታማ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ ማቀበል ችሏል።

አሽሊ ያንግ (ማንቸስተር ዩናይትድ) - ያንግ በዩናይትድ ያበቃለት ተጫዋች መስሎኝ ነበር። ከአንቶኒዮ ቫልንሲያ በመቀጠል ከክንፍ ተጫዋችነት ወደ ተመላላሽ ተከላካይነት የተቀየረ መሆንም ችሏል። በዚህ የወድድር ዘመን ባሳየው ብቃትም በ32 ዓመቱ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እንዲጠራ ሆኗል።

አማካዮች

ደ ብረይን፣ ፈርናንዲኖ እና ሲልቫ

Image copyright BBC Sport

ኬቭን ዴ ብረይን (ማንቸስተር ሲቲ) - በዚህ የውድድር ዘመን ካየኋቸው ተጫዋቾች ሁላ እንደ ኬቭን አንጀቴን ያራሰው የለም። እንደው ሞሃመድ ሳላህ የሚገርም ብቃት ላይ መገኘቱ እንጂ የውድድር ዘመኑ ምርጥ መሆን ይገባው የነበረ ልጅ ነው። እንግዲህ እግር ኳስ እንዲህ ነው። ይህን ተጫዋች የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጫዋቾች መሃል ከማካተት ያለፈ ነገር ማድረግ ብችል አደርግ ነበር።

ፈርናንዲንሆ (ማንቸስተር ሲቲ) - ክሎውድ ማኬሌሌ ከሪያል ማድሪድ፤ ጋርካምቢያሶ ደግሞ ከኢንተር ጋር መሰል ድል መጋራት ችለዋል። ፈርናንዲኖ ደግሞ ከሲቲ ጋር ስኬትን ማጣጣም ችሏል። እኒህ ተጫዋቾች ራሳቸውን ከእነ ዚነዲን ዚዳን እኩል ባይመድቡም ለቡድናቸው ድል የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም።

ዳቪድ ሲልቫ (ማንቸስተር ሲቲ) - ሲልቫ ለሲቲ በጣም ለየት ያለ ግልጋሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ተጫዋች ነው። ዘጠኝ ጎል አስቆጥሮ 11 ማቀበልም የቻለ ተጫዋች ነው ሲልቫ።

አጥቂዎች

ሳላህ፣ ኬን እና አጉዌሮ

Image copyright BBC Sport

ሞሃመድ ሳላህ (ሊቨርፑል) - ይህ ግብፃዊ ለሃገሩም ሆነ ለቡድኑ እያደረገ ያለው በቃላት ሊገለፅ የማይችል ነው። የዚህ ውድድር ዘመን ብቃቱ ደግሞ በአግራሞት አፍ የሚያስከድን ነው። የሊቨርፑል ደጋፊዎች ሞ ሳላህ...ሞ ሳላህ እያሉ ቢዘምሩ የሚገርም አይደለም። በ32 ጎሎችም በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ያገባ የሚለውን ክበረ-ወሰን መስበር ችሏል።

ሃሪ ኬን (ቶተንሃም) - አነሆ ሌላ ድንቅ የውድድር ዘመን ለሃሪ ኬን። አኔ ይህ እንግሊዛዊ ሌሎች የሃገሩ ልጆች በየቦታው ዋንጫ ሲያነሱ እያየ እዛው ቶተንሃም መቆየት እስከመቼ እንደሚቆይ አላውቅም። በሁሉም የወድድር ዓይነቶች 42 ጎሎች በማስቆጠር የክለቡን ክብረ-ወሰን መስበርም ችሏል።

ሰርጂዮ አጉዌሮ (ማንቸስተር ሲቲ) - የየሳምንቱን ምርጥ አስራ አንድ የሚከታተሉ ሰዎች መቼም ለአጉዌሮ ያለኝን አድናቆት ያውቃሉ። ሲቲ ዋንጫውን እንዲበላ የአጉዌሮ ጎሎች ትልቅ ሚና መጫወታቸው ሊዘነጋ አይገባም። የሲቲ የምን ጊዜም ጎል አግቢ ክብረ-ወሰነንም መጨበጥ ችሏል።

የወድድር ዘመኑ ምርጥ አሰልጣኝ

ራፋኤል ቤኒቴዝ - ኒውካስል ዩናይትድ

Image copyright Reuters

የውድድር ዘመኑ ምርጥ ሶስት አሰልጣኞች እንነማ ናቸው ተብዬ በተጠይቅኩ ጊዜ ያለማንገራገር ራፋ ቤኒቴዝ፣ ሾን ዳይሽ እና ክሩስ ሑቶን ብዬ ነበር።

በርንሌይ ለአውሮፓ ሊግ ይበቃል፤ ብራይተን በሊጉ ይቆያል፤ ኒውካስል ደግሞ 44 ነጥብ መሰብሰብ ይችላል የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበረኝም።

ቤኒቴዝ ኒውካስልን ለቻምፒዮንሺፕ ዋንጫ ከማብቃታቸውም ባሻገር ሊጉን የሚመጥን ቡድን አድርገውታል። ልጆቹን ለሽንፈት እምቢ እንዲሉ አድርጎም ቀርጿቸዋል።