ኢቦላ ለምን አገረሸ?

የጤና ባለሙያዎች በ ሞንሮቪያ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 Image copyright Getty Images

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ አገርሸቷል። ነገር ግን በሽታው መቼ እና እንዴት በድጋሚ ሊከሰት ይችላል የሚለውን ለመገመት አዳጋች ነው። የተጋረጠውን አደጋ እንዴት መከላከል እንደምንችል እናውቃለን።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የምትገኘው ቢኮሮ ከተማ የታየው የቫይረሱ ማገርሸት ከዚህ ቀድሞ የተከሰተውንና በምዕራብ አፍሪካ አስራ አንድ ሺህ ሰዎች ህይወት መቀጠፍን እንዲሁም ሃያ ስምንት ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙበትን አስደንጋጭና አስፈሪ ጊዜ ያስታውሰናል።

በያዝነው ዓመት ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምንም እንኳን ከሟቾቹ ሁለቱ ብቻ በቫይረሱ መያዛቸው ቢረጋገጥም የሞቱትን አሰራ ሰምንት ሰዎችን ጨምሮ ሰላሳ የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ተገኝተዋል።

ኢቦላ ለምን አገረሸ? ባለፈው ዓመት የተከሰተው አሳዛኝ አጋጣሚ ድጋሚ እንዳያንሰራራ ምን እየተሰራ ነው? የሚለው መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ኢቦላ ለምን ከቁጥጥር ውጭ ሆነ?

ኢቦላ በቫይረስ ከተያዘው ሰው ሰውነት በሚወጣ በጣም አነስተኛ መጠን ባለው ፈሳሽ ሳይቀር በመተላለፉና ያልተለመዱ ምልክቶች ስላሉት ችግሩን ከቁጥጥር ውጭ ያደርገዋል።

በቅርቡ ኢቦላ ያገረሸባት- ቢኮሮ የንግድ ከተማ በመሆኗ፣ በዋና ዋና ወንዞች መከበቧ እንዲሁም ድንበር አካባቢ በመገኘቷ ትኩረትን እንድታገኝ አድርጓል።

ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች የሚገኛኙበት፣ የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና እንቅስቃሴዎች የሚዘወተሩበት በመሆኑ ቫይረሱ የሚዛመትበትን እድል ስለሚያፋጥነው ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ 2014-2016 በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ኢቦላ መነሻው ጊኒ ውስጥ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ሲሆን፤ መጀመሪያ በቫይረሱ የተያዘውም እደሜው ሁለት ዓመት የሚሆነው ህፃን ነበር።

በሽታው በጊኒ እንዲሁም በጎረቤቶቿ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ በተለይ በከተሞች አካባቢ በፍጥነት ተሰራጭቶ ነበር። ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከእነዚህ አገራት በብዙ ሺህ ማይል ርቀት ብትገኝም ልታመልጥ ግን አልቻለችም።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካጋጠማት አሳዛኝ አጋጣሚ በ2017 የተከሰተው የኢቦላ ማገርሸት አንዱ ነው።

ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ሰዎች

ቫይረሱ ስር ሰዶ ከማንሰራራቱ በፊት ሰዎች እንዳይያዙና እንዳይዛመት ማድረግ ይቻላል። በተፋጠናና በተቀናጀ መልኩ መስራት ከተቻለ ከመጀመሪያው የበሽታውን ስእረጭት መግታት ይቻላል።

የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የዓለም ጤና ድርጅትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች ቫይረሱ ያገረሸበት አካባቢ የመጀመሪያ ምላሻቸውን እየሰጡ ነው። ቫይረሱ የሚተላለፍባቸውን መንገዶች መለየትን ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይ ሲሆን በተቻላቸው አቅም ማንም ሰው በቫይረሱ እንዳይያዝ ተግተው እየሰሩ ነው።

ኢቦላ ተገኘባቸው የተባሉ ሰዎችም በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ጭምብል በማድረግ፣ የእጅ ጓንቶችን በመጠቀም፣ ጋዎን በመልበስ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲያገኝና ኢቦላን በተመለከተ ምላሽ ከሚሰጡ ቡድኖች ጋር መረጃዎችን መለዋወጥ ያስፈልጋል።

የህሙማን ደም ናሙና ለምርመራ ኪንሻሳ የሚገኘው ብሄራዊ ላቦራቶሪ እንደተላከም ተገልጿል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በአውሮፓውያኑ ከ2014-16 በምዕራብ አፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢቦላ ህይወታቸውን አጥተዋል

ክትባቱስ?

እስካሁን ኢቦላ ተገኝቶባቸዋል የተባሉ አምስት ቀጠናዎች የተለዩ ሲሆን የሞቱት ዜር በተሰኘው ቀጠና ነው። በእነዚህ ቀጠናዎች ለመጠባበቂያ የተዘጋጀው ክትባት ለድንገተኛ ክስተቶች ይውላል።

በእንግሊዝና በኖርዌይ መንግሥት ድጋፍ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ክትባቱ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም ለሰዎች እንዲሰጥ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ፈቃድ አልተገኘም። ይሁን እንጂ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ለማዋል ለመጠባበቂ 300ሺህ የሚሆኑ ክትባቶች ተዘጋጅተዋል።

ክትባቱ ቫይረሱ ይኖርባቸዋል ተብለው ለተጠረጠሩ ህሙማን፣ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎች መሰጠት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጤና ሚኒስቴር ውሳኔ ብቸኛው አማራጭ ነው።

በእርግጥ በቅርቡ ላገረሸው ኢቦላ የአገሪቷ መንግሥት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ያሳየ ቢሆንም ብቻውን ግን ምን ማድረግ አይችልም። ዓለም አቀፍ እርዳታ፣ አፋጣኝና የተቀላጠፈ ምላሽ ከሁሉም ይጠበቃል።

ኢቦላ በቀላሉ ሊጠፋ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ የሚያጋጥሙትን እያንዳንዱን ጥቃቅን ችግሮች በመፍታት ችግሩ ስር ሳይሰድ አሁን ባለበት ደረጃ ማስቀረት ይቻላል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።