"የናንዬ ሕይወት" የአይዳ ዕደማርያም ምስል ከሳች መፀሐፍ

"የናንዬ ሕይወት. . .የአያቴ እና የሃገሬ ታሪክ" Image copyright FOURTH ESTATE

ማንደጃው ላይ የተጣዱ አራት ፍሬ ከሰሎች ወርቃማ ቀለም ያለው እሣት ይተፋሉ፤ አያቴ ከዕጣኑ ቆንጠር በማድረግ እፍሙ ላይ ብታኖረው ጊዜ ደስ የሚል ሽታ አካባቢውን ያውደው ጀመር። መቁያው ላይ እሣት እየመታው ካለው ቡና ጋር ሲቀላቀል ደግሞ መዐዛው እንደው ልብ የሚሰውር ሆነ፤ ቤቱ በሽታ ቀለማት ተውቦ ሞቅ ብሎ ሳለ ውጭው ግና በጳጉሜ ዝናብ እና ብርድ ይንቀጠቀጥ ነበር. . .

«በዕለተ ሩፋኤል ዝናብ ከጣለ ውሃው የተቀደሰ ነው» ትል ነበር አያቴ። «ልጅ እያለን የቅዱስ ውሃው በረከት ያገኘን ዘንድ ልብሳችንን አውልቀን በዝማሬ በመታጀብ ጭቃው ላይ እንቦርቅ ነበር። ቀስተ ደመናው ተሩቅ የሚታየን ከሆነ ደግሞ ማርያም መቀነቷን ሰማዩ ወገብ ላይ አስራ ስላለች ይበልጥ ደስ ይለን ነበር. . .»

የናንዬ ሕይወት. . .

ከአንድ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ አንዲት ልጅ በሰሜን ኢትዮጵያዊቷ የጎንደር ከተማ ተወለደች። ገና 8 ዓመቷ ሳለ በሁለት አስርት ዓመታት ከሚበልጣት ሰው ጋር ትዳር እንድትመሠርት ሆነ። በርካታ ልጆችንም አፈራች። የጣልያን ዳግም ወረራ፣ የቦምብ ናዳ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አልፋ እና ኦሜጋ፣ አብዮት እና የእርስ በርስ ጦርነት ይህች ሴት በዚህች ምድር በቆየችባቸው 95 ዓመታት ውስጥ ያስተናገደቻቸው ክስተቶች ናቸው።

'The Wife's Tale' ወይንም በግርድፍ ትርጉሙ 'የሚስት ትረካ' በሚል ደራሲና ጋዜጠኛ አይዳ ዕደማርያም የፃፈችው መፅሐፍ በእነዚህ 95 ዓመታት አያቷ የተመኙ ያሳለፉትን አስደናቂ የሕይወት ውጣ ውረዶች የሚዳስስ ጠርቃ ያለ ጥራዝ ነው።

ኮራ ጀነን ያሉ ቀሳውስት፣ ሃገር ወዳድ ወታደሮች፣ የባለቤቷ እሥርና እንግልት፣ ፍትህን ፍለጋ፣ እመበለትነት. . .ብቻ ከልጅነት እስከ እውቀት የተመኙ ያየችውን ቆጥሮ መዝለቅ ውሃ እንደ መፍጨት ነው።

አፄውና እቴጌይቱ፣ ምሁራንና መነኩሳት፣ የማርክስ አብዮተኝነት አቀንቃኞች እንዲሁም ባንዳዎች አይዳ 'ናንዬ' ብላ በምትጠራት አያቷ ሕይወት መስኮት የሚቃኙ የእውነተኛው ዓለም ገፀ-ባህርያት ናቸው።

'ዘ ዋይፍስ ቴል' የአንዲት አትዮጵያዊት ሴት የክፍለ ዘመን ትረካ ብቻ ሳይሆን የሃገሯ ታሪክ የክፈለ ዘመን ትውስታም ነው" ትላለች አይዳ ስለመፅሃፉ መናገር ስትጀምር።

"ትዝ ይለኛል የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነበር የናንዬን ሕይወት መመዝገብ የጀመረኩት፤ ቢሆንም እንዲህ ወደ ታሪክ ገላጭ ጥራዝ እቀይረዋለሁ የሚል እሣቤ አልነበረኝም" በማለት የመፅሐፉን መፀነስ ታወሳለች አይዳ።

"ብዙ ጊዜ ታሪክ ነጋሪ ሆነው የምናያቸው በጦርነት አውድማ የተሳተፉ አሊያም ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን ታሪክ ሊታይ የሚገባው በተለምዶ ተራ ሰው ብለን ከምንጠራው ግለሰብ ዓይን ነው" ስትል ትከራከራለች። "የናንዬ ሕይወት የሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሕይወት ነው፤ ለዚህም ነው ታሪክ ያለው ብዙም እውቅና ካለገኙ ግለሰቦች ጓዳ ነው ብዬ የምለው። መነገርም ያለበት በእነዚህ ሰዎች አንደበት ነው።"

ጎንደር

ስለኢትዮጵያ ታሪክ በተወሳ ቁጥር ስሟ ይነሳል፤ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንድ መዘክር ሆናም ትጠቀሳለች። የሃገሪቱ ርዕሰ-መዲና ሆናም አገልግላለች፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣት ቦታ ናት፤ ጎንደር።

የየተመኙ ውልደት ጎንደር እንደመሆኑ 'ዘ ዋይፍስ ቴል' ጉምቱውን የታሪክ መቼት ያደረገው በዚህች ታሪካዊ ከተማ ነው። በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችው ጎንደር የጥራዙ ትልቅ አካል መሆኗ መፅሐፉ በታሪክ፣ እምነት እንዲሁም ቀለማት ድምቆ የተዋበ እንዲሆን ረድተውታል ትላለች አይዳ።

"እርግጥ ነው አዲስ አበባም የናንዬ ሕይወት ትልቅ አካል ናት፤ ቢሆንም ግማሽ ያህል ሕይወቷን ያሳለፈችው ጎንደር ነው። እትብቷ የተቀበረውም እዚያው ጎንደር ነው" የምትለው አይዳ መፅሐፉ በታሪክ የበለፀገ ሆኖ አገኘው ዘንድ ጥናት ለማድረግ ጎንደር ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ ስትልም ትዘክራለች።

ጉዞ ወደ አዲስ አበባ

«እኔ ምለውን ትደግሚያለሽ» ቄሱ ተናገሩ። «ቢታመም»...ቢታመም፤ «ቢጎሳቆል»...ቢጎሳቆል፤ «ክፉ ቢገጥመው፣ ቢደኸይ፣ ቢሞት እንኳ...አልክደውም»...አልክደውም። የተመኙ በ20 ዓመታት ከሚበልጣት፤ ከገጣሚና መንፈሰ ብርቱ የቤተስኪያን ሰው ሊቀ ካህናት አለቃ ፀጋ ተሻለ ጋር ጎጆ ትቅለስ ዘንድ ሆነ።

ከፍርግርጉ በስተጀርባ ያለ ባሏን ለመጠየቅ በሄደች ጊዜ እጅግ ከፍቶት አገኘችው፤ «ወይኔ ልቤን፤ አይዞህ...እሽ እኔ ምን ላድርግ? ወይ አዲሳባ ተሚሉት ሃገር ልሂድ እንዴ?» አለቃ ፀጋ ሃሳቡን አላወገዘውም። «ወደ አዲሳባ ሂጂ፤ እከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ እንጉሱ ጋር ሄደሽ መበደሌን ንገርሊኝ፤ ነፃ አውጭኝ።» የሕይወት ምዕራፍ ወዳላሰቡት ሆነና የተመኙ ለእሥር የተዳረገ ባልተቤቷን ነፃ ለማውጣት አዲሳባ ከሚሉት የማታውቀው ዓለም መሄድ ግድ የሆነባት።

ሰው በሰው ላይ የሚሄድበት ምድር. . .. መኪና ከየት መጣ ሳይሉት ጥሩንባውን እየነፋ የሚክለፈልፍበት ሃገር. . .አዲስ አበባ። የየተመኙ ወደ አዲሳባ ማቅናት ጉዳይ ስለባሏ ፍትህ ለመጮህ ቢሆንም ተቆጥሮ የማያልቅ ጉድ አይታበታለች። የገበያው ግርግር፣ የተማሪ ጥድፍያ፣ የዘመድ ዓይን. . .ኧረ የቱ ተነግሮ የቱ ይተዋል?

Image copyright FOURTH ESTATE

ማርያም ማርያም. . .

1930 ዓ.ም ጎንደር ከተማ፤ የተመኙ ምጡ ቢጠናባት ጊዜ እንደ ሃገሬ እና ሃገሯ እናቶች ማርያምን አጥብቃ ትለማመን ጀመር። ባለቤቷ ሊቀ ካህናት አለቃ ፀጋ ተሻለ ልጃቸውንም የልጃቸውንም እናት እንዳያጡ ስጋት ቢገባቸው ወደአምላካቸው ቀና ብለው አጥብቀው ይጸልዩ ነበር።

የአካባቢው ሰው የአለቃን ቤት ሞልቶታል፤ ሁሉም ተጨንቋል። በቤቱ የተገኙ ቀሳውስትም ከድርሳነ ሩፋኤልና ተዓምረ ማርያም ላይ ጸሎት ያሰሙ ይዘዋል። የተመኙ እንዲህ የምጥ ጭንቅ ውስጥ ሆና ሁለት ቀናት አለፉ።

ሦስተኛም ቀን ሆነ፤ የተመኙ እንቅልፍ ወሰድ መለስ ያደርጋት ይዟል። ሦስተኛውም ቀን እንዲሁ ባለ ስሜት ካለፈ በኋላ ሌሊት ላይ ወንድ ልጅ ተገላገለች።

መጀመሪያ ጨቅላው አልንቀሳቀስ አልላወስ ይልና የሁሉም ልብ በድንጋጤና ጭንቀት ይዋጣል፤ አዋቂዋ አዋልጅ ግን አልደነገጡም። በንጡህ ጨርቅ አርገው ጨቅላውን በውሃ ሲያብሱት አንቀላፍቶ የነበረው እንደው ንቅት ይልና ጣቱን መጥባት ተያያዘው፤ ቤቱም በደስታ ተሞላ።

ልጁም እደማርያም ተብሎ ይጠራ ተባለ፤ የማርያም እድ (እጅ) እንዳማለት። ፕሮፌሰር እደማርያም ፀጋ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሕክምና ታሪክ ሉዓላዊ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ጠበብት ሐኪሞች አንዱ ነበሩ። እርሣቸው ደግሞ አይዳን ወለዱ።

'ዘ ጋርዲያን' ለተሰኘው ጋዜጣ የምትሰራው አይዳ ስለ አያቷ አውርታ የምትጠግብም አትመስል። "ምንም እንኳ አብዛኛውን የሕይወቴን ክፍል የኖርኩት በምዕራባዊው ምድር ቢሆንም ከአያቴ ጉያ መጥፋት አልሻም ነበር" ትላለች።

"ቢያንስ ደውዬ ሳናግራት ደስታ ይወረኛል። ኢትዮጵያ እያለሁ ቤታችን ስትመጣ እንደው አካባቢው አንዳች ኃይል ይላበሳል። በቡና መዓዛ የታወደ መሳጭ ታሪክ መስማትን የመሰለ ነገር የለም።"

"ምንም እንኳ የናንዬ ታሪክ ልብ በሚሰብሩ ኹነቶች የተሞላ ቢሆንም ውጣ ውረዱን አልፋ አስደናቂ ሕይወት መምራት ችላለች፤ የልቧን ደስታም ሳትሸሽገው ኖራለች። ይገርምሃል ልብ በጣም ንፁህ ነው፤ ባህርይዋ ደግሞ በአስደናቂ ድርጊቶች የተሞላ። ደግሞ መደነስ ትወድም ትችልም ነበር። በሚያስለቅሰው ታለቅሳለች፤ በሚያስቀው ትፈነድቃለች። ሕይወት በሙሉ ለመኖር ሰስታ፤ ስሜቷን ለመግለፅ ፈርታ አታውቅም።"

'ዘ ዋይፍስ ቴል' በበርካቶች ዘንድ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን የሚታይ ታሪክ ያዘለ ተብሎ ተደንቋል። እኔም መፅሓፉን አነበብኩት፤ ኧረ እንድያውም ተመለከትኩት። እንደው ቃላቶችሽ እንዴት ቢካኑ ነው እንዲህ ውብ ቀለም የተላበሱት ስልም ጠየቅኳት አይዳን።

''ዕድሜ ለአያቴ'' አለችኝ። ''ታሪክ ስትነግረኝ እንደምትስልልኝ ሁሉ እመለከተው ነበር፤ እኖረውም ነበር። መንገዱ፣ ገበያው፣ ልዩ ምልክቱ፣ ሳሩ ቅጠሉ ጤዛው. . .ብርት ብሎ ይታየኛል። እኔም ቁጭ ብዬ እሷን በመመሰጥ ማድመጥና በመቅረፀ-ድምፄ ማስቀረት የዕለተለት ሥራዬ ሆነ።''

"ናንዬ እኮ ታሪክን በመናገር ብቻ የተካነች አይደለችም፤ በመኖርም ጭምር እንጂ። ነገሮችን ሁሉ በአግባቡ ስታከናውን አያት ነበር። ምንም እንኳ የእኔም ቃላትን ገላጭ አድርጎ የመግለፅ ክህሎት ቢኖርበትም የእርሷ አገላለፅ ግን ከድርጊት እኩል ነበር።"

"አያቴ የከወነቻቸውን ነገሮች ለመከወን ሞክሬያለሁ፤ በሄደችበት መንገድ ሄጃለሁ፣ የሳመችውን ቤተስኪያን ስምያለሁ፣ የገበየችውን ገብይቻለሁ፣ እኒህን ነገሮች ያደረግኩት ከአያቴ ሕይወት ጋር በምናብ ለመገናኘት ነው" ትላለች አይዳ።

'ዘ ዋይፍስ ቴል' የአይዳ አያት ድንቅ ሕይወት፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የአንድ ምዕተ ዓመት ነፀብራቅ፤ የገጠሩና የከተማው ትዕይንተ-ሕይወት ማሳያ አቡጀዲ ጨርቅ፤ ኃይማኖታዊና ዓለማዊ ትርክት ነው።