ለአፍሪካውያን ስደተኛ ልጆች አደገኛ የሆነው መጠለያ

የእስራኤል ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ከሃገራቸው እንዲወጡ ይፈልጋሉ
አጭር የምስል መግለጫ የእስራኤል ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ከሃገራቸው እንዲወጡ ይፈልጋሉ

በደቡብ ቴል አቪቭ በሚገኘው አንድ አነስተኛ ቤት ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ሌላዋ ደግሞ ሴት ምግብ ታዘጋጃለች። 20 የሚሆኑ ህጻናት በቤቱ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጠዋል።

አዲስ ሰው ሲያዩ "ሻሎም" ብለው በሂብሩ ሰላምታ ይሰጣሉ። ሰው እንደሚናፍቃቸው ከሰላምታ አሰጣጣቸው መረዳት ይቻላል።

ከሴቶቹ አንዷ ህጻናቱን መቆጣጠር ከባድ መሆኑን ትናገራለች። በአካባቢው ይህን የመሰሉ 90 መኖሪያዎች አሉ።

ቤቶቹ የአፍሪካውያን ስደተኞች ልጆች ማቆያ ናቸው። የህጻናት ማቆያዎቹ ህጋዊ ፍቃድ የላቸውም። እስራኤል ውስጥ ወደ 37,000 ሺህ የሚጠጉ አፍሪካውያን ስደተኞች አሉ።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ ስደተኞች ወዴት እንደሚሄዱ ግራ ተጋብተዋል።

የእስራኤል መንግስት ወደ ሀገራቸው ሊመልሳቸው ይፈልጋል። በቅርቡ ይህ የመንግስት ውሳኔ በፍርድ ቤት መቀልበሱ ይታወሳል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ልጆቻቸውን የሚያስቀምጡት በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ነው። ቤቶቹ ለህጻናት ምቹ ባይሆኑም ስደተኞቹ አማራጭ የላቸውም።

ልጆቹ በማቆያ ውስጥ ተገቢውን እንክብካቤ አያገኙም። እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 በጠባቂዎች ቸልተኛነት አምስት ህጻናት ሞቷዋል።

ኤሊፍሌት የተራድኦ ድርጅት የምትሰራው ሶፊያ የስደተኞች ልጆች አማራጭ እንደሌላቸው ትናገራለች። "መንግስት ወደ ሀገራችን ሊመልሰን ይችላል ብለው የፈሩ ወላጆች ገንዘብ ለማጠራቀም ብዙ ስለሚሰሩ ልጆቻቸውን በርካሽ ማቆያ ውስጥ ያስቀምጣሉ።"ትላለች።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ 2006 እስከ 2016 በእግር ጉዞ ቴል አቪቭ የገቡ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን በርካታ ናቸው። ከስደተኞቹ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉት ጥገኝነት ቢጠይቁም ፍቃድ የተሰጠው ለአስራ ሁለቱ ብቻ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ በርካታ አፍሪካዊያን የሚገኙበት በደቡባዊ ቴልአቪቭ የሚገኘው የሃቲግቫ ገበያ

እስራኤል ለስደተኞቹ 3,500 ዶላርና የአውሮፕላን ትኬት ሰጥታ ወደ ሀገራቸው የመመለስ እቅዷን ያሳወቀችው ከወራት በፊት ነበር። ከሀገሪቱ ያልወጡ ስደተኞች ለእስርና እንግልት ተዳራገዋል።

"እስራኤል ለህጋዊ ስደተኞች መጠለያ ትሆናለች። ህገ ወጦችን ግን አትቀበልም። ህገ ወጥ ስደተኞች ላይ እርምጃ እንወስዳለን።" ሲሉ ፕሬዘዳንት ቤንጃሚን ናታኒያሁ ተናግረው ነበር።

ልጆቻውን በማቆያዎቹ ትተው የሚሄዱ ቤተሰቦች ዘወትር ጭንቀት ላይ ናቸው። ከእነዚህ የስድስት ወር ልጇን በማቆያው አስቀምጣ ወደ ስራ የምትሄደው ኤርትራዊት ትጠቀሳለች።

"ልጄን ለማሳደግ ቀኑን ሙሉ ሳጸዳ ነው የምውለው።" በማለት ከህጻናት ማቆያው ውጪ አማራጭ እንደሌላት ትናገራለች።

ሶፍያ እንደምትለው የህጻናት ማቆያዎቹ በህጻናቱ እድገትም ተጽእኖ አላቸው። "ልጆቹ ከጭንቀት ባሻገር ትምህርት በፍጥነት ያለመረዳት ችግርም ይገጥማቸዋል።" ትላለች።

አብዛኞቹ ስደተኞች በሚኖሩበት የቴል አቪቭ ክፍል የሚኖሩ እስራኤላውያን ስለ ስደተኞቹ ደንታ የላቸውም፥። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ የሚደግፉም ብዙ ናቸው።

በሌላ በኩል አፍሪካውያኑ እየደረሰባቸው ካለው እንግልት ጀርባ ዘረኝነት አለ የሚሉም አሉ። የ 31 አመቱ ነጋዴ ዛየን ስደተኞቹን በግድ ወደየሀገራቸው መመለስ አግባብ አይደለም ብሎ ያምናል።

ከሱ ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ ያላቸው 2,500 እስራኤላውያን በቴል አቪቭ ሮቢን አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር።

ሚክላት እስራኤል የተባለ ለስደተኞች ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም ያቋቋሙት ራባይ ሱዛን ሲልቨርማን "የሒብሩ ሀይማኖት እንግዶችን እንድንቀበል ያዛል።" ይላሉ።

ኤርትራውያንና ሱዳናውያን ስደተኞች የመንግስትን ውሳኔ በፍርድ ቤት አስለውጠዋል። የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ ከስደተኞቹ መሀከል በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ ምዕራባውያኑ ሀገራት የመውሰድ ሀሳብ አቅርቧል።

በድርድሩ የእስራኤል መንግስት ለተቀሩት ስደተኞች መጠለያ እንድትሰጥ ጠይቋል።

"የፍርድ ቤቱ ውሳኔና የአልም አቀፉ ማህበረሰብ ጥያቄ ቢኖርም ህገ ወጦችን ለማስወጣት ሌሎች አማራጮች እንጠቀማለን።" ይላሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር።

ስደተኞቹ አሁንም ግራ መጋባት ውስጥ ናቸው። ልጆቻቸውን በህገ ወጥ ማቆያዎች የሚያስቀምጡት ቤተሰቦችም እንዲሁ።

ተያያዥ ርዕሶች